ጥቁሮችን መርጦ የገደለው የፒኤችዲ ምሩቅ ነጭ አክራሪ እንደነበረ ፖሊስ አስታወቀ

ገዳዩ ናታን አለን

የፎቶው ባለመብት, Suffolk County District Attorney's Office

ባለፈው ቅዳሜ ከሰዓት በአሜሪካ ማሳቹሴትስ አንድ ወጣት ሁለት ጥቁሮችን ተኩሶ ገደለ፡፡

ነጭ አሜሪካዊው ናታን አለን ባለፈው ቅዳሜ ከአንድ የቧንቧ ሥራ ተቋራጭ ኩባንያ ከባድ ተሸከርካሪ በመስረቅ ተሸከርካሪውን ከአንድ መኖርያ ቤት ጋር በማላተም ቤቱን ካፈረሰ በኋላ ነበር ወደ አነጣጥሮ የመግደል ተግባር የገባው፡፡

ናታን የ28 ዓመት ነጭ አሜሪካዊ ሲሆን፣ ባለትዳርና የፒኤችዲ ምሩቅ ነበር፡፡

በታሪኩም አንድም ጊዜ ቢሆን በወንጀል ተግባር ተሳትፎም አያውቅም፡፡

ናታን የሰረቀውን ከባድ መኪና እየነዳ በአንድ መኖርያ ቤት ጋር ካላተመ በኋላ ከከባድ መኪናው ወርዶ ሌላ መኪና ለመስረቅ ሞክሮ አልተሳካለትም፡፡

ከዚህ በኋላ በተረጋጋ ሁኔታ በእግሩ መሄድ ይጀምራል፡፡

በያዘው መሣሪያ ለመግደል የፈቀደው ግን ጥቁሮችን ብቻ ነበር፡፡

ዴቭ ግሪን እና ራሞና ኩፐር የተባሉ ጥቁሮችንም ተኩሶ ገድሏቸዋል፡፡

መጀመርያ የ60 ዓመቷን የአየር ኃይል ባልደረባ ራሞና ኩፐርን ከጀርባዋ በተከታታይ በመተኮስ የገደላት ሲሆን ከዚያ በኋላ ደግሞ የ68 ዓመቱን ዴቭ ግሪንን አከታትሎ በመተኮስ ገድሏል፡፡

በእግር በሚጓዝበት ጊዜ በርካታ ነጮች እግረ መንገዱን ያገኘ ሲሆን አንዳቸውንም ለመግደል አልሞከረም፡፡

ሁለት ጥቁሮችን ተኩሶ የገደለውም ጥቁር በመሆናቸው ነበር፡፡

በኋላ ላይ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የፒኤችዲ ምሩቁና ዘረኛው ናታን ተገድሏል፡፡

ይህን ተከትሎ ምርመራ ያደረገው የማሳቹሴት ፖሊስ ናታን አለን የለየለት ዘረኛ በነጭ ዘር የበላይነት አማኝ እንደነበር ደርሶበታል፡፡

የተገደሉት ጥቁሮች

የፎቶው ባለመብት, Suffolk County District Attorney's Office

በኋላ ላይ የተገኙ ማስታወሻዎቹ ላይ ናታን አለን ነጮች የሰው ዘር የበላይ እንደሆኑ የሚያትት ጽሑፎችን መጻፉ ተደርሶበታል፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን ናታን አይሁድ ጠልና ጸረ ጥቁር ዘር እንደነበረም በገዛ የእጅ ጽሑፉ አስፍሯል፡፡ በማታወሻ ደብተሮቹም የናዚ አርማ የሆነውን ስዋስቲካን ነድፏል፡፡

ናታን አለን ባለትዳር፣ ባለሥራ እንዲሁም ባለ ፒኤችዲ እንደነበረም ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የማሳቹሴት ገዥ ቻርሊ ቤከር ድርጊቱን አስነዋሪ ሲሉ አውግዘውታል፡፡