ተመድ በዘረኝነት ተጠቂ ለሆኑ ካሳ ሊከፈል ይገባል አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ዘረኝነትን ለመዋጋት አለም አቀፋዊ እርምጃ እንደሚያስፈልግ ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።
ጉባኤው እርምጃ ብሎ ከጠቀሳቸው ውስጥ በተለያዩ አገራት መቀመጫቸውን ላደረጉ ጥቁሮች ካሳ መክፈል ነው።
ሪፖርቱ በ60 አገራት ዩናይትድ ኪንግደም፣ ቤልጂየም፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳ፣ ብራዚልና ኮሎምቢያ የመሳሰሉ አገራት ጥቁሮች የሚደርስባቸውን ዘረኝነት ዳስዷል።
ጥናቱ የተጀመረው በአሜሪካዊ ፖሊስ እጅ ጆርጅ ፍሎይድ መገደሉን ተከትሎ ነው።
የጆርጅ ፍሎይድ ሞትና ያስከተለው ቁጣ በመቀጠልም ፖሊሱ ለእስር መዳረጉ "ዘረኝነትን ለመዋጋት ከሚደረጉ መሰረታዊ ነገሮች እንደ አንዱ ይታያል" ብሏል።
የተመድ ሪፖርት መሰረት ያደረገው 300 የሚጠጉ ባለሙያዎችን እንዲሁም የአፍሪካ ዝርያ ያላቸውን ሲሆን አገራት ዘረኝነትን ለመዋጋት እርምጃ እንዲወስዱም ያበረታታል።
በሰሜን አሜሪካ፣ በላቲን አሜሪካና በአውሮፓ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ ዘርን መሰረት ያደረገ እስር፣ ያልተገባ ኃይል በፖሊስ እንደሚፈፀም ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካውያንን በባርነት ባጋዙ አገራት ላይ ዘረኝነት አሁንም ዋነኛ ችግር እንደሆነ ሪፖርቱ ተመልክቷል።
እነዚህን መረጃዎች ካጤነ በኋላ በነዚህ ሃገራት ላይ የዘር ፍትህን ለማስፈን "ለአስርት አመታት ያደረሱትን ጭካኔና መድልዎ ለማስተካከል ይፋዊ የሆነ እውቅናና ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል። እነዚህ አገራት እውነት ከመናገር በተጨማሪ በተለያዩ ሂደቶች ካሳ ሊከፍሉ ይገባል" ብሏል ሪፖርቱ በማጠቃለያው
ለጥቁሮች መብት የሚታገለውን 'ብላክ ላይቭስ ማተር' እንቅስቃሴ ያደነቀው ይህ ሪፖርት የገንዘብ ድጋፍን ጨምሮ እውቅና ሊሰጥም እንደሚገባ ጠቁሟል።
በትናንትናው ዕለት የተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኃላፊ ሚሸል ባችሌት "ሁሉም አገራት በሃገራቸው እየተፈፀመ ያለውን ዘረኝነት መካድ እንዲያቆሙና ለመግታትም መስራት አለባቸው" ብለዋል።
ኃላፊዋ አክለውም አፍሪካዊ ዝርያ ያላቸውን ህዝቦቻቸውን መስማት እንደሚያስፈልግም ማሳሰሰቢያ ሰጥተዋል።
ሚሸል ባችሌት እንዳሉት ካሳው ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ኢ-ፍትሃዊነት እንዳይከሰት ዋስትና አገራቱ ሊሰጡ እንደሚገባም መክረዋል።












