ሱዳን የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትን በተመለከተ በኢትዮጵያ የቀረበውን ሐሳብ ተቃወመች

የፎቶው ባለመብት, Maxar Technologies via Reuters
ሱዳን እየተገነባ ያለውን ግዙፉን የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ሁለተኛ ዙር ሙሌት ለማከናወን ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ሐሳብ ተቃወመች።
ሮይተርስ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የግድቡን የውሃ ሙሌት ለማካሄድ ያቀረበችው ሐሳብ "ተጨባጭ ያለሆነ" እና "ጊዜ ለመግዛት የቀረበ" ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
ጨምረውም እንዲህ አይነቱ ሐሳብ መቅረብ ያለበት ሁሉንም ወገኖች ባካተተ ሁኔታ በአፍሪካ ሕብረት የድርድር ጥላ ስር መሆን እንደነበረበት ተናግረዋል።
በስም ያልተጠቀሱት ባለሥልጣኑ ለሮይተርስ እንዳሉት ኢትዮጵያ የውሃ ድርሻን በተመለከተ "ሊሆን የማይችሉ ቅደመ ሁኔታዎችን" ያቀረበች ሲሆን ሱዳን ይህንን ሐሳብ ከድርድር ማዕቀፍ ውጪ ነው ብላ እንደምታስብ ገልጸዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ ምላሽ ለማግኘት ሮይተርስ የዜና ወኪል ለኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር. ኢንጂነር) ጥያቄ ቢያርብም ምላሽ እንዳላገኘ አመልክቷል።
ባለፈው ሳምንት የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም አል ማሐዲ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በተከሰተው አለመግባባት ውስጥ ጣልቃ እንዲገባና ኢትዮጵያ "በተናጠል" ግድቡን በውሃ ከመሙላት እንድትታቀብ እንዲያደረግ በደብዳቤ መጠየቃቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ያከናወነችውን የመጀመሪያውን ውሃ ሙሌት ተከትሎ በዚህ ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ለማካሄድ ያቀደችውን ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ሊያስቆም የሚችል ምንም አይነት ምክንያት እንደሌለ ስትገልጽ ቆይታለች።
ሁለተኛው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት በዚህ ዓመት የክረምት ወራት ውስጥ ካልተከናወነ ከባድ ኪሳራን ሊያስከትልባት እንደሚችል የገለጸችው ኢትዮጵያ ድርድሩ እየተካሄደ ውሃ የመሙላት ሥራውን እንደምትቀጥል በተደጋጋሚ አሳውቃለች።
ከሳምንት በፊት የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ያሲር አባስ አንዳንድ ሁኔታዎች ከተሟሉ ሱዳን በግድቡ ዙሪያ ባሉ ጉዳዮች ላይ ከፊል ጊዜያዊ ስምምነት ለመፈራረም ዝግጁ መሆኗን አስታወቀው ነበር።
በዚህም ሱዳን ሦስት ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርባ የነበረ ሲሆን በሐምሌ ወር ለማካሄድ ዕቅድ ከተያዘለት ሁለተኛ ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት በኋላም ድርድሩ እንደሚቀጥል ማረጋገጫ ኢትዮጵያ እንድትሰጥ ከተሰጠ፣ እስካሁን በተደረጉ ድርድሮች ስምምነት የተደረሰባቸው ሁሉም ጉዳዮች ላይ አገራቱ የመጨረሻ ፊርማቸውን እንዲያኖሩ እና ድርድሮች የሚካሄዱበት ግልጽ የጊዜ ሰሌዳ እንዲኖር የሚሉ ነበሩ።
ይህም ሱዳንና ግብጽ ሕጋዊና አስገዳጅ ስምምነት ሳይፈረም ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት እንዳታካሂድ አጥብቀው ሲቃወሙ ከመቆየታቸው አንጻር የሱዳን ሐሳም የአቋም ለውጥ እንደሆነ ተገልጾ ነበር።
ቀደም ሲል ሱዳንና ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ሲያደርጉት በነበረው ድርድር ላይ አጥብቀው ሲያነሱ የነበረው በግድቡ ዙሪያ ሕጋዊና አሳሪ ስምምነት እንዲደረግ የነበረ ሲሆን ይህም ለድርድሩ ውጤታማ አለመሆን የራሱ አስተዋጽኦ ነበረው።
አገራቱ ለዓመታት ሲያደርጉት በነበረው ድርድር በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደርሰው የነበረ ሲሆን ሁሉን አቀፍ ስምምነት እንዲደረግ በሚል መቋጫ ሳያገኝ ቆይቶ ነበር።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ግንባታው ከተጀመረ አስር ዓመታት በሞላው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ጥቅማቸውን ለማስከበር ድርድር ሲያደርጉ ቢቆዩም ሁሉን የሚያስማማ ውጤት ላይ ለመድረስ ሳይችሉ ቆይተዋል።
ሱዳንና ግብጽ ቀደም ሲል በድርድሩ ላይ ሌሎችም አካላት በአሸማጋይነት እንዲሳተፉ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ኢትዮጵያ የተጀመረው ሂደት በአፍሪካ ሕብረት በኩል መቋጫ እንዲያገኝ በመግፋት ሳትቀበለው ቀርታለች።
ሱዳን የሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በተመለከተ መለሳለስ ማሳየቷና ጊዜያዊ ስምምነት እንዲደረግ ከጠየቀች በኋላ በጉዳዩ ላይ ፍላጎቷን ለማስጠበቅ ጠንካራ አቋም ከያዘችው ከግብጽ በኩል አስካሁን የተሰማ ነገር የለም።
የአፍሪካ ሕብረትና አሜሪካ በተለያዩ ወቅቶች ሦስቱን አገራት ለማሸማገል ለተራዘመ ጊዜ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም በየትኛውም ድርድር ሁሉንም ከሚያስማማ ውጤት ላይ ለመድረስ አልቻሉም።
ግብጽና ሱዳን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የምናገኘውን የውሃ መጠን ይቀንሰዋል በሚል ተደጋጋሚ ተቃውሞ ሲያቀርቡ የቆዩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ግን የግድቡን ውሃ ለ65 ሚሊዮን ዜጎቿ የኤሌትሪክ ኃይል ለማቅረብ የምጠቀምበት በመሆኑ ችግር አይፈጥርም በማለት ስጋታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ስትገልጽ ቆይታለች።
ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታው እየተካሄደ ያለውና ግንባታው ከተጀመረ አስር ዓመት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከአፍሪካ ትልቁ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን፣ ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል አቅም ያለው ግዙፍ ግድብ ነው።
የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ የተከናወነ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ደግሞ በመጪው የሐምሌ ወር እንደሚከናወን ኢትዮጵያ ያስታወቀች ሲሆን፤ በሚጥለው ዓመት በተወሰነ ደረጃ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ይጠበቃል።















