በአረብ ሊግ ጉባኤ ዋዜማ የሱዳን የስምምነት ጥሪ የአቋም ለውጥ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, @seleshi_b_a
ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ልታከናውን በተቃረበችበት ጊዜ አንዳንድ ሁኔታዎች ከተሟሉ ሱዳን በግድቡ ዙሪያ ባሉ ጉዳዮች ላይ ከፊል ጊዜያዊ ስምምነት ለመፈራረም ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች።
ሱዳንና ግብጽ ሕጋዊና አስገዳጅ ስምምነት ሳይፈረም ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት እንዳታካሂድ አጥብቀው ሲቃወሙ ከመቆየታቸው አንጻር ይህ የሱዳን ጥሪ የአቋም ለውጥ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ያሲር አባስ ሰኞ ዕለት ካርቱም ውስጥ እንደተናገሩት ጊዜያዊ ስምምነቱ የሚፈረመው ሦስት ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል።
በዚህም መሠረት በቅድመ ሁኔታነት የቀረቡት ጉዳዮች በሐምሌ ወር ለማካሄድ ዕቅድ ከተያዘለት ሁለተኛ ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት በኋላም ድርድሩ እንደሚቀጥል ማረጋገጫ ከተሰጠ፣ እስካሁን በተደረጉ ድርድሮች ስምምነት የተደረሰባቸው ሁሉም ጉዳዮች ላይ አገራቱ የመጨረሻ ፊርማቸውን እንዲያኖሩ እና ድርድሮች የሚካሄዱበት ግልጽ የጊዜ ሰሌዳ እንዲኖር የሚሉ ናቸው።
ቀደም ሲል ሱዳንና ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ሲያደርጉት በነበረው ድርድር ላይ አጥብቀው ሲያነሱ የነበረው በግድቡ ዙሪያ ሕጋዊና አሳሪ ስምምነት እንዲደረግ የነበረ ሲሆን ይህም ለድርድሩ ውጤታማ አለመሆን የራሱ አስተዋጽኦ ነበረው።
አገራቱ ለዓመታት ሲያደርጉት በነበረው ድርድር በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደርሰው የነበረ ሲሆን ሁሉን አቀፍ ስምምነት እንዲደረግ በሚል መቋጫ ሳያገኝ ቆይቶ ነበር።
ሮይተርስ እንዳለውም አሁን በመስኖ ሚኒስትሯ በኩል ሱዳን ያቀረበችው ሃሳብ ቀደም ሲል ሲራመድ ከነበረው አቋም የተለየ ነው።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ግንባታው ከተጀመረ አስር ዓመታት በሞላው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ጥቅማቸውን ለማስከበር ድርድር ሲያደርጉ ቢቆዩም ሁሉን የሚያስማማ ውጤት ላይ ለመድረስ ሳይችሉ ቆይተዋል።
ውዝግብና መካሰስ ባልተለየው ሂደት ውስጥ አገራቱ ወደ ወታደራዊ ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ የሚል ስጋት በበርካቶች ዘንድ ተፈጥሮ ነበር።
የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር ያሲር አባስ አማራጭ ሃሳብ ባቀረቡበት በሰኞው መግለጫቸው ላይ አገራቸው የግድቡን ውዝግብ ለመፍታት ወታደራዊ ግጭትን ፈጽሞ እንደአማራጭ እንደማታየው መናገራቸውን የሱዳን ዜና ወኪል ሱና ዘግቧል።
ከዚያ ይልቅ ሱዳን ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎች የመፍትሔ መንገዶችን እንደምትጠቀም አመልክተዋል። በዚህም በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት፣ በወዳጅ አገራትንና በሌሎች በሚመለከታቸው ወገኖች አማካይነት ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ እንደምትሻ ገልጸዋል።
ከዚህ በተቃራኒ ለአረብ ሊግ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ኳታር የሚገኙት የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ለአልጀዚራ እንደተናገሩት የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ አገራቸው ጥቅሟን ለማስከበር ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው ብለዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይን እንደ አጀንዳ የሚመለከተው የአረብ ሊግ ጉባኤ ግብጽና ሱዳን ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የሚካሄድ ነው። ሳሜ ሽኩሪ እንዳሉትም "የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ስብሰባ ለኢትዮጵያ ጠንካራ ፖለቲካዊ መልዕክት የሚተላለፍበት ይሆናል" ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
ዛሬ በሚካሄደው የአረብ ሊግ ስብሰባ ላይ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ መወያያ እንዲሆን ሱዳንና ግብጽ የጠየቁ ሲሆን በዚሁ ስበሰባ ላይ የማኅበሩ አገራት ከጎናቸው እንዲሆኑ ለማድረግ የታለመ እንደሆነ ተነግሯል።
ያሲር አባስ ይህንን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ጉዳዩን ወደ አረብ ሊግ መውሰድ ጉዳዩን የአረብ አገራት ከአፍሪካ አገራት ጋር የሚደረግ ውዝግብ ለማድረግ ሳይሆን የሱዳንን አቋም ለአባል አገራቱ ለማስረዳት ነው ብለዋል።
ጨምረውም ሱዳን በአፍሪካ ሕብረት ላይ ያላት አቋም አለመቀየሩን አመልክተው፤ ነገር ግን የአፍሪካ ሕብረት ብቻውን ለጉዳዩ መፍትሔ ሊያመጣ ስለማይችል ሌሎች አካላትም እንዲሳተፉበት ለማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሱዳንና ግብጽ ቀደም ሲል በድርድሩ ላይ ሌሎችም አካላት በአሸማጋይነት እንዲሳተፉ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ኢትዮጵያ የተጀመረው ሂደት በአፍሪካ ሕብረት በኩል መቋጫ እንዲያገኝ በመግፋት ሳትቀበለው ቀርታለች።
ሱዳን የሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በተመለከተ መለሳለስ ማሳየቷና ጊዜያዊ ስምምነት እንዲደረግ ከጠየቀች በኋላ በጉዳዩ ላይ ፍላጎቷን ለማስጠበቅ ጠንካራ አቋም ከያዘችው ከግብጽ በኩል አስካሁን የተሰማ ነገር የለም።
የአፍሪካ ሕብረትና አሜሪካ በተለያዩ ወቅቶች ሦስቱን አገራት ለማሸማገል ለተራዘመ ጊዜ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም በየትኛውም ድርድር ሁሉንም ከሚያስማማ ውጤት ላይ ለመድረስ አልቻሉም።
ግብጽና ሱዳን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የምናገኘውን የውሃ መጠን ይቀንሰዋል በሚል ተደጋጋሚ ተቃውሞ ሲያቀርቡ የቆዩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ግን የግድቡን ውሃ ለ65 ሚሊዮን ዜጎቿ የኤሌትሪክ ኃይል ለማቅረብ የምጠቀምበት በመሆኑ ችግር አይፈጥርም በማለት ስጋታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ስትገልጽ ቆይታለች።
ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታው እየተካሄደ ያለውና ግንባታው ከተጀመረ አስር ዓመት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከአፍሪካ ትልቁ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን፣ ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል አቅም ያለው ግዙፍ ግድብ ነው።
የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ የተከናወነ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ደግሞ በመጪው የሐምሌ ወር እንደሚከናወን ኢትዮጵያ ያስታወቀች ሲሆን፤ በሚጥለው ዓመት በተወሰነ ደረጃ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ይጠበቃል።
















