ሱዳን የጸጥታው ምክር ቤት በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ስብሰባ እንዲጠራ ጠየቀች

የሕዳሴ ግድብ በግንባታ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በተከሰተው አለመግባባት ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ ጠየቀ።

ሱዳን በጽሁፍ ባቀረበችው ጥያቄ ላይ ምክር ቤቱ ተሰብስቦ ግድቡ "በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ደኅንነት ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ" እንዲወያይ ጠይቃለች።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ማሪያም አል ማሐዲ አማካይነት ለጸጥታው ምክር ቤት ኃላፊ በተጻፈው ደብዳቤ፤ ኢትዮጵያ "በተናጠል" ግድቡን በውሃ ከመሙላት እንድትታቀብ እንዲጠይቁ ሐሳብ ሰንዝረዋል።

በአፍሪካ ሕብረት አሸማጋይነት ሲካሄድ የነበረው ድርድር ምንም ውጤት ሳያስገኝ በመቅረቱ በአገራቱ መካከል በግድቡ የውሃ አሞላል ዙሪያ ያለው ውዝግብ ቀጥሏል።

ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ግዙፍ ግድብ ከ60 ሚሊየን በላይ ለሚሆነው ሕዝቧ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ለልማቷ እጅግ አስፈላጊ ፕሮጀክት መሆኑን በመግለጽ ግንባታውን ቀጥላለች።

ሱዳንና ግብጽ ደግሞ በግድቡ የውሃ ሙሌትና ቀጣይ ሥራ ላይ አሳሪ ሕጋዊ ስምምነት ካልተድሰ ከአባይ ወንዝ በምናገኘው ውሃ ላይ ተጽእኖ ስለሚፈጠር ግድቡ ሕዝባችንን ለችግር ያጋልጠዋል በማለት ሲቃወሙ ቆይተዋል።

የአባይ ወንዝ መነሻ በሆነችው በኢትዮጵያና በመዳረሻው በግብጽ መካከል የምትገኘው ሱዳን፤ መፍትሔ ያላገኙ ጉዳዮች ሳይቋጩ የግድቡን ውሃ ሙሌት ማከናወን ለብሔራዊ ደኅንነቴ አደጋ ነው ስትል ቆይታለች።

ከመመሪያዎች ይልቅ ግድቡ በሚይዘው የውሃ መጠንና ግድቡን ለመሙላት በሚያስፈልገው የጊዜ ሰሌዳ ላይ ሱዳን ኢትዮጵያ ሕጋዊና አሳሪ ስምምነት እንድትፈርም ትፈልጋለች።

የአፍሪካ ሕብረትና አሜሪካ በተለያዩ ወቅቶች ሦስቱን አገራት ለማሸማገል ለተራዘመ ጊዜ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም በየትኛውም ድርድር ሁሉንም ከሚያስማማ ውጤት ላይ ለመድረስ አልተቻለም።

ግብጽና ሱዳን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የምናገኘውን የውሃ መጠን ይቀንሰዋል በሚል ተደጋጋሚ ተቃውሞ ሲያቀርቡ የቆዩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ግን የግድቡን ውሃ የኤሌትሪክ ኃይል ለማመንጨት እንደምትጠቀምበት በመግለጽ ስጋታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ስትገልጽ ቆይታለች።

ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታው እየተካሄደ ያለውና ግንባታው ከተጀመረ አስር ዓመት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከአፍሪካ ትልቁ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን፣ ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል አቅም ያለው ግዙፍ ግድብ ነው።

የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ የተከናወነ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ደግሞ በመጪው የሐምሌ ወር እንደሚከናወን ኢትዮጵያ ያስታወቀች ሲሆን፤ በሚጥለው ዓመት በተወሰነ ደረጃ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ይጠበቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሱዳን ከደቡብ ሱዳን ጋር በምትወዛገብበት የድንበር አካባቢ አቢዬ በተባበሩት መንግሥታት ስር ተሰማርቶ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሠራዊት እንዲወጣ በድጋሚ መጠየቋን የአገሪቱ ዜና ወኪል ሱና ዘገበ።

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም አል መሐዲ ስለኢትዮጵያ ወታደሮች መውጣት በድጋሚ ሐሳብ ያቀረቡት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣን ግርሃም ሚትላንድ ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ እንደሆነ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ለጥያቄያቸው ያቀረቡት ምክንያት "ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ወቅታዊ ግንኙነት በመቀየሩና ለተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ አስፈላጊ የሆነው የወታደሮቹ ገለልተኝነት አጠያያቂ በመሆኑ ነው" ብለዋል።

በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ካለው አለመግባባት በተጨማሪ በጥቅምት ወር መጨረሻ በትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የሱዳን ወታደሮች በኢትዮጵያ ተይዞብናል ያሏቸውን ቦታዎች በመያዛቸው በአገራቱ መካከል ውዝግብ መከሰቱ ይታወሳል።

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት በሱዳን የተሰማራውን ሠላም አስከባሪ ኃይል ከአስር ዓመት በፊት ያሰማራ ሲሆን የኢትዮጵያ ወታደሮችም የቡድኑ አባላት ሆነው ቆይተዋል።

በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል የምትገኘው የአብዬ ግዛት ሁለቱ አገራት ትገባናለች የሚሏት ግዛት ስትሆን፤ በሱዳን መንግሥትና በሱዳን ነጻነት ሠራዊት መካከል ሲካሄድ የነበረው እርስ በርስ ጦርነት ሲያበቃ ግዛቲቱ "ልዩ የአስተዳደር መብት" ተሰጥቷት ነበር።

ሁለቱ አገራት በፈረሙት የአብዬ ፕሮቶኮል ስር በጊዜያዊነት ግዛቲቱ የሁለቱም አገራት አካል እንድትሆን ተስማምተዋል።

በአብዬ የተሰማራው የተባበሩት መንግሥታት ሠላም አስከባሪ ኃይል ግዛቲቱን ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ እንድትሆን የሚያደርግና ጸጥታን የማስከበር ኃላፊነት ተሰጥቶታል።