አሜሪካ ኢራቅ እና ሶሪያ ውስጥ የአየር ድብደባ መፈጸሟን አስታወቀች

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

አሜሪካ በኢራን የሚደገፉ ሚሊሻዎችን ዒላማ ያደረገ የአየር ድብደባ በኢራቅ እና በሶሪያ ውስጥ መፈጸሟን የመከላከያ መሥሪያ ቤቷ ፔንታገን አስታወቀ።

ጥቃቱ ሚሊሻዎቹ በአሜሪካ ወታደሮች በሰው አልባ አውሮፕላን ላይ ለፈጸሙት ጥቃት ምላሽ "በጦር መምሪያ እና በጦር መሣሪያ ማከማቻ ተቋማታቸው ላይ" የተፈጸመ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

"ፕሬዝዳንት ባይደን የአሜሪካን ወታደሮችን ለመጠበቅ እርምጃ እንደሚወስዱ ግልጽ ነው" ብሏል ፔንታገን።

ጆ ባይደን ስልጣን ከያዙ ወዲህ በኢራን በሚደገፉ ሚሊሻዎች ላይ የአየር ድብደባ እንዲፈጸም ሲፈቅዱ ይህ ሁለተኛው ነው።

ባለፉት ጥቂት ወራት መቀመጫቸውን ኢራቅ ባደረገው የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ላይ በሰው አልባ አውሮፕላን ተደጋጋሚ ጥቃቶች ተሰንዝሮባቸዋል። ኢራን በጥቃቶቹ እጇ እንደሌለበት ገልጻለች።

ሁለት ሺህ አምስት መቶ የሚጠጉ የአሜሪካ ወታደሮች ጂሃዳዊውን እስላማዊ መንግሥትን (አይ ኤስ) የሚዋጋ ዓለም አቀፍ ጥምረት አካል ሆነው ኢራቅ ውስጥ ይገኛሉ።

በፔንታገን መግለጫ መሠረት "በመከላከያ ዒላማቸውን በጠበቁ የአየር ጥቃቶች" በሶሪያ ውስጥ ሁለት አንድ ደግሞ በኢራቅ ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎች ተመተዋል፡፡ ካታብ ሂዝቦላህ እና ካታይብ ሰይድ አል ሹሃዳን ጨምሮ በኢራን የሚደገፉ የሚሊሺያ ቡድኖች ዒላማ የተደረትን ተቋማት ይጠቀሙባቸዋል ተብሏል።

አሜሪካ እአአ ከ2009 ጀምሮ ካታይብ ሂዝቦላህ የኢራቅን ሠላምና መረጋጋት አደጋ ላይ ጥሏል በሚል በሽብርተኛነት ፈርጃለች።

መግለጫው አሜሪካ ራሷን በመከላከል እርምጃ ወስዳለች ብሏል። አደጋ ለመገደብ የታቀደ "አስፈላጊ፣ ተገቢ እና ሆን ተብሎ የተወሰደ እርምጃን ወስዳለች። ግልጽ እና ግልጽ ያልሆነ መልዕክት ለመማስተላለፍም ነው" ብሏል።

በፔንታገን በጥቃቱ የሞተ ወይም የቆሰለ ሰው ስለመኖሩን አልገለጸም። ነገር ግን ሶሪያን ኦብዘርቫቶሪ ፎር ሒውማን ራይትስን ጠቅሶ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው አምስት ሚሊሻዎች ሶሪያ ውስጥ "በአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች ጥቃት" እንደተገደሉ ገልጿል።

የሶርያ የመንግሥት የዜና ወኪል ሳና በበኩሉ አንድ ህጻን መሞቱን እና ቢያንስ ሦስት ሰዎች መቁሰላቸውን ዘግቧል ሲል ኤኤፍፒ ይፋ አድርጓል።

እአአ በ2013 በአሜሪካ መሪነት ሳዳም ሁሴን ከስልጣን ከተወገዱ ጀምሮ ኢራን በኢራቅ የውስጥ ጉዳይ ላይ የምታሳድረው ተጽዕኖ ያለማቋረጥ አድጓል።

ጥቃቶቹ የተሰነዘሩት ኢራን የኒውክሌር ሥራዋን በማስቆም በመንግሥት ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ለማስነሳት የ2015 የኒውክሌር ስምምነትን እንደገና ለማደስ አሜሪካንን ጨምሮ ከዓለም ኃያላን ጋር እየተነጋገረች ባለችበት ወቅት ነው።

እስራኤልን ጨምሮ አንዳንድ አገራት ኢራን የኒውክሌር ቦምብ ለመገንባት እየሞከረች እንደሆነ ቢያምኑም ኢራን ይህንን ታስተባብላለች።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እአአ በ2018 በተናጠል አሜሪካን ከኢራን ጋር ከተደረገው ስምምነት አስወጥተው አገሪቱ ላይ ማዕቀብ በድጋሚ ጥለዋል።