በሶማሊያዋ ፑንትላንድ ግዛት ውስጥ ሃያ አንድ የአልሻባብ አባላት በሞት ተቀጡ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሶማሊያ ከፊል ራስገዝ አስተዳደር በሆነችው የፑንትላንድ ግዛት የታጣቂው የእስላማዊው ቡድን አልሻባብ አባላት ናቸው ያለቻቸውን ሃያ አንድ ሰዎችን በሞት ቀጣች።
ካልካዮ ውስጥ በሚገኝ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ቀርበው ሞት ከተፈረደባቸው በኋላ ነው የተረሸኑት የታጣቂው ቡድን አባላት ሁሉም ወንዶች ናቸው።
የክልሉ አስተዳደር ሬዲዮ ጣቢያ እንደዘገበው ከተገደሉት 18 የታጣቂው ቡድን አባላት መካከል 18ቱ ከአስር ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ ግድያዎችንና የቦምብ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል።
በእነዚህ ግለሰቦች ላይ የሞት ቅጣቱ ሲፈጸም ቡድኑ በሌላ የሶማሊያ ግዛት ውስጥ ጥቃት ፈጽሞ በርካታ ወታደሮችን መግደሉ ተዘግቧል።
ተመሳሳይ የሞት ቅጣት በሌላ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ በሚገኝ አንድ ፍርድ ቤት የተላላፈ ሲሆን፤ ፑንትላንድ ውስጥ የተፈጸመው ይህ የሞት ቅጣት ግን ከዚህ በፊት በአልሻባብ አባላት ላይ ተግባራዊ ከሆኑት ሁሉ በቁጥር የበለጠው ነው።
የፑንትላንድ ባለሥልጣናት ማንኛውም የዚህ ታጣቂ ቡድን አባል የሆነ ወይም ቡድኑን ሲደግፍ የተገኘ ሰውን ለፍርድ አቅርበው እንደሚያስቀጡ አስጠንቅቀዋል።
ይህ ታጣቂ እስላማዊ ቡድን አልሻባብ በአሁኑ ጊዜ በሶማሊያ ውስጥ ዋነኛው ያለመረጋጋት ምንጭና የደኅንነት ስጋት መሆኑ ይነገራል።
አልሻባብ በርካታ ቦታዎችን የሚቆጣጠር ሲሆን በዚህም አብዛኞቹ የሶማሊያን ደቡባዊና ማዕከላዊ ግዛቶች በእጁ ስር ሲሆኑ፤ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ሂራል የተባለ ተቋም ያደረገው ጥናት እንዳመለከተው ታጣቂ ቡድኑ ከአገሪቱ መንግሥት የበለጠ ገንዘብ ይሰበስባል።
ቡድኑ በተለያዩ ጊዜያት የበርካታ ሰዎችን ህይወት ያጠፉ ከባድ ጥቃቶችን በመፈጸም ይኣወቃል።
ይህ በፑንትላንድ ግዛት ውስጥ የተሰጠው የሞት ፍርድ ተግባራዊ ሲሆንም የአልሻባብ ተዋጊዎች ሙዱግ በሚባለው ክልል ውስጥ በምትገኝ ዊሲል በተባለች ከተማ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።
በዚህም በሶማሊያ ሠራዊት ጦር ሰፍር ላይ በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ 20 ወታደሮችን ሳይገድሉ እንዳልቀሩ ከስፍራው የወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።












