የዩናይትድ ኪንግደም ጤና ሚኒስትር የኮቪድ-19ን ደንብ በመተላለፋቸው ከሥራ ለቀቁ

ማት ሃንኮክ (ከቀኝ) ጊና ኮላዳነጌሎን (ከግራ)

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, ማት ሃንኮክ (ከቀኝ) ጊና ኮላዳነጌሎን (ከግራ) መሳማቸውን የሚያሳይ ፎቶ በጋዜጣ ላይ ከወጣ በኋላ ነው ሥራቸውን የለቀቁት

የዩናይትድ ኪንግደም ጤና ሚኒስትር ማት ሃንኮክ የኮቪድ-19 መመሪያ መጣሳቸውን ተከትሎ ከሥራቸው ለቀቁ። ሚኒስትሩ የአካላዊ ርቀትን ደንብ በመተላለፍ የሥራ ባልደረባቸውን መሳማቸውን ተከትሎ ነው ከሥራ የለቀቀቁት።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦሪስ ጆንሰን በፃፉት ደብዳቤ መንግሥት "በዚህ ወረርሽኝ ላይ መስዋዕትነት ለከፈሉ የማኅበረሰቡ ክፍሎች እኛም ስናጠፋ ተጠያቂ መሆናችንን ማሳየት አለብን" በማለት አስፍረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የሚኒስትሩን መልቀቂያ መቀበላቸው እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል።

ተሰናባቹን የጤና ሚኒስትርን በመተካት የቀድሞ የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ሳጂድ ጃቪድ የተሾሙ ሲሆን ለዚህ የሚኒስትርነት ቦታ በመመረጣቸው የተሰማቸውን ክብር ገልፀዋል።

ማት ሃንኮክ ከረዳታቸው ጋር እየተሳሳሙ የሚያሳይ ቪዲዮ ሰን በተባለው ጋዜጣ ላይ መውጣቱን ተከትሎ ነው በርካቶች ኃላፊነታቸውን እንዲለቁ ግፊት ሲያደርጉባቸው የነበረው። ሁለቱም ያገቡና የሦስት ልጆች ወላጆች ናቸው።

ጋዜጣው አክሎ እንደዘገበው ሁለቱንም ግለሰቦች ፎቶግራፉ የተነሳው ባለፈው የግንቦት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ላይ እዚያው የጤና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ውስጥ ነው።

ይህንንም ተከትሎ ሚኒስትሩ ለ15 ዓመታት በጋብቻ ከቆዩት ባለቤታቸው ጋር ተፋትተዋል። የሳሟት የሥራ ባልደረባቸው ጋር ያላቸው የፍቅር ግንኙነትም የጠነከረ እንደሆነ ተገልጿል።

በርካታ የፓርላማ አባላት፣ የሠራተኛ፣ ማኅበራዊ ጉዳይና በኮቪድ-19 ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች የተቋቋመው የፍትህ ቡድን ሚኒስትሩ ከሥራ እንዲባረሩ ሲጠይቁ ነበር። እንዲሁም የፓርላማ አባላቱ ሚኒስትሩ ከሥራቸው እንዲለቁም መምከራቸውን ቢቢሲ ከአንዳንድ የፓርላማ አባላት ሰምቷል።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥራቸው እንዲለቁ ባይፈልጉም ሚኒስትሩ በራሳቸው ፈቃድ መልቀቃቸውን የቢቢሲ የፖለቲካ ዘጋቢ ላውራ ኩንስበርግ ዘግባለች። ከዚህም በተጨማሪ የሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ጂና ኮላዳንጌሎም እንዲሁ ከሥራቸው መልቀቃቸው ተዘግቧል።