ኮሎምቢያ የፕሬዝዳንቷ ሄሊኮፕተር ላይ ጥቃት የሰነዘረውን ለጠቆመ ከፍተኛ ገንዘብ እሸልማለሁ አለች

ሄሊኮፕተር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኮሎምቢያ የፕሬዝዳንቷ ሄሊኮፕተር ላይ የደረሰውን ጥቃት በተመለከተ መረጃ ለሚሰጥ ሰው ወደ 800 ሺህ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እሸልማለሁ አለች።

ባለፈው አርብ የኮሎምቢያው ፕሬዚዳንት ሄሊኮፕተር ላይ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ ጥቃቱን በተመለከተ መረጃ ለሚሰጥ ሰው ሀገሪቱ ሦስት ቢሊዮን ፔሶ [የኮሎምቢያ ገንዘብ ነው] ወይም 796 ሺህ ዶላር ሽልማት አቅርባለች፡፡

ባለፈው አርብ ፕሬዝዳንቱ ኢቫን ዱኬ ሀገረራቸው ከቬንዙዌላ ጋር በሚዋሰነው ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያ ሲቃረብ ነበር ሄሊኮፕተራቸው ላይ ተኩስ የተከፈተው።

ከጥቃቱ በኋላ የተሰራጩ ፎቶዎች የፕሬዝዳንቱ ሄሊኮፕተር የተለያዩ ክፍሎች በጥይት ተነድለው አስመልክተዋል።

በሄሊኮፕተሩ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱ የታወቀ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ፣ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ጥቃቱን አውግዘውታል።

ጥቃት በደረሰበት መጓጓዣ ከፕሬዝዳንቱ ጋር አብረው ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት የመከላከያ ሚኒስትሩ ዲያጎ ሞላኖ የጥቃት አድራሾቹን ዱካ ለማግኘት የሚረዳ ማንኛውም መረጃን ለሚያቀብል ሰው ሽልማት ማቅረባቸው ተሰምቷል።

በሌላ በኩል የሀገሪቱ ፖሊስ ጥቃቱ በደረሰበት አቅራቢያ በሚገኝ መንደር ሄሊኮፕተሩን ለማጥቃት የዋሉ ናቸው ያሏቸውን ሁለት የተለያዩ መለያ ያላቸውን መሳሪያዎች ማግኘቱን አስታውቋል።

ጥቃት ለማድረስ ጥቅም ላይ ከዋሉት መሳሪያዎች አንዱ "የቬንዙዌላ የጦር ኃይል የሚጠቀምበት" ነው ሲሉ የፖሊስ አዛዥ ጄኔራል ጆርጅ ቫርጋስ ተናግረዋል።

ጥቃቱን ማን እንዳደረገው እስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም የፖሊስ አዛዡ ግን አጥፊዎቹን "እስክንይዛቸው ድረስ ተስፍ አንቆርጥም" ሲሉም በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

የፕሬዝዳንቱ ሄሊኮፕተራቸው ላይ ጥቃት ከመድረሱ በፊት በካታቱምቦ ግዛት ውስጥ በነበረ ዝግጅት ላይ ታድመው ነበር ፡፡ ኮሎምቢያና ቬንዙዌላ ድንበር የሚጋሩበት አካባቢው ሲሆን ኮኬይን ለመቀመም ጥቅም ላይ ከሚውሉ ወሳኝ ንጥረ ነገሮች አንዱ የሆነው 'ኮካ' በስፋት ከሚገኙባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዱ ነው ፡፡

ኮሎምቢያ ከዚህ ቀደም ቬንዙዌላን አማጽያንን ታስጠልላቸች ስትል ትወንጅላለች - ምንም እንኳን ቬንዜዌላ ክሱን ብታስተባብልም፡፡ ታዲያ ከቀናት በፊት ሄሊኮፕተራቸው ላይ ጥቃት የደረሰባቸው ፕሬዝዳንቱ እንደ አውሮፓውያኑ 2018 ወደ ስልጣን ሲመጡ ከቬንዚዌላ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋርጠዋል።