የሶሪያ ስደተኛ ነኝ ብሎ 'ያጭበረበረው' ጀርመናዊ ወታደር ለፍርድ ቀረበ

የፎቶው ባለመብት, EPA/Boris Roessler/Pool
ከሰሞኑ አንድ ጀርመን ወታደር በሽብር ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቧል።
ወታደሩ ራሱን የሶሪያ ስደተኛ ነኝ በሚል ሃሰተኛ ሽፋን ተጠቅሞ በፖለቲከኞች ላይ ጥቃት ሊፈፅም ሲያቅድ ነበር ተብሏል።
ፍራንኮ ኤ የተባለው ወታደር ነዋሪነቱን ፈረንሳይ ያደረገ ሲሆን ሁለት ህይወት ይመራም ነበር ተብሏል።
በሌላ መልኩ ዴቪድ ቤንጃሚን በሚል ስደተኛ ስምም ተመዝግቦ ተገኝቷል።
የግለሰቡ ሁለት ህይወት መምራት የተጋለጠው የእጅ ጣት አሻራ በመጠቀም ነው። በስራትስቦርግ ተቀማጭነቱን ያደረገው ይህ ወታደር ክርስቲያን የሶሪያ ስደተኛ ነኝ በሚልም መመዝገቡን ተከትሎ የጣት አሻራቸው ተመሳሳይ መሆኑም ታውቋል።
አቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ መሰረት የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄይኮ ማስ፣ የፓርላማው ምክትል አፈ ጉባኤና አንድ የአይሁድ የመብት ታጋይ ግለሰቡ ኢላማ ካደረጋቸው ፖለቲከኞች ዝርዝር መካከል ተጠቅሰዋል።
ይህንን ለማስፈፀም በሚል ግለሰቡ ሃሰተኛ የሩሲያ ስደተኛ ማንነትን በመላበስና ጥቃት ሊያቀነባብር ነበር በማለት ወንጅሎታል።
ወታደሩ የሩሲያ ስደተኛ ማንነትን የተላበሰው በጥቃቱ ስደተኞች ጥፋተኛ ተብለው እንዲወነጀሉና ፀረ-እስልምና ሁኔታዎች ተጠናክረው እንዲወጡ ነው በማለት አቃቤ ህግ ክሱን አቅርቧል።
በግለሰቡ ቤተሰቦች የዕቃ ማስቀመጫ ክፍል ውስጥ ተቀጣጣይ ፈንጆች እንዲሁም የቦምብ መስሪያ ቁሳቁሶች ተገኝቷል።
እንዲሁም በተደረገው ፍተሻ ሂትለርን የሚያወድሱ ፅሁፎችና የድምፅ ቅጅዎች መገኛታቸውም ይፋ ተደርጓል።
ይህ ጉዳይ የጀርመን ጦር አባላት ከጀርመን ቀኝ ክንፍ ፅንፈኞች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ካሳዩት በርካታ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ነው ተብሏል።
ወታደሩ የተያዘው በአውሮፓውያኑ 2017 ሲሆን በቪየና አየር ማረፊያ ላይ በመፀዳኛ ቤት የተገኘ ሽጉጥን ለማውጣት ሲሞክር ነበር ተብሏል።
ግለሰቡ ከተያዘም በኋላ በጀርመን የተከለከለው የናዚ አርማ በቤቱም ሳሎን ቤት እንደተገኘም ተገልጿል።
ወታደሩ የቀኝ ክንፍ ፅንፈኛ ነው ቢባልም እሱ በበኩሉ ግን ፅንፈኛ እንዳልሆነና ምንም አይነት ጥቃት አልፈፀምኩም በማለቱ ፀንቷል።
በጀርመን የግል መረጃን መጠበቅ መረጃ ጋር በተያያዘ በወንጀል ተጠርጥረው የቀረቡ ሰዎች የአባታቸው ወይም (የቤተሰባቸው ስም) ለህዝብ ይፋ አይሆንም።












