ሃማስ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት አደረጉ

ፍልስጥኤማውያን ደስታቸውን በጋዛ እየገለፁ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

በእስራኤል መንግሥት እና በፍልስጥኤሙ ታጣቂ ቡድን ሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከዛሬ አርብ ጀምሮ ተግባራዊ ተደረገ።

ተኩስ አቁሙ ከተተገበረ በኋላ በርካታ ፍልስጥኤማዊያን በጋዛ ጎዳናዎች ላይ ደስታቸውን ለመግለፅ የወጡ ሲሆን አንድ የሃማስ ባለስልጣን ‹‹አሁንም ጥይታችንን እንዳቀባበልን ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል።

ከመስጊዶች የሚሰሙ የድምፅ ማጉያዎች ‹‹ በእየሩሳሌሙ ሰይፍ› ውጊያ ትግላችን ድል አስገኝቷል›› የሚሉ መልክቶችን አስተጋብተዋል።

ሁለቱም አካላት በፍልሚያው አሸናፊነታቸውን አውጀዋል። የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን የተኩስ አቁሙ ‹‹ለለውጥ ሃቀኛ እድል የሚሰጥ ነው›› ሲሉም ስምምነቱን ገልፀውታል።

ለ11 ቀናት የቆየው ይህ ግጭት እስካሁን የ240 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን አብዛኛው ህልፈት የተመዘገበው በጋዛ ነው።

በግጭቱ 100 ሴቶች እና ህፃናትን ጨምሮ 232 ሰዎች በጋዛ ህይወታቸውን አጥተዋል። እስራኤል ከዚህ ውስጥ ቢያንስ 150 ያህሉ ተዋጊዎች ናቸው ብላለች። ሃማስ እስካሁን ድረስ የሞቱ ተዋጊዎቹን ቁጥር ይፋ አላደረገም።

ትላንት ሃሙስ ብቻ እስራኤል 100 የሚጠጉ የአየር ጥቃቶችን በተለይም በሰሜናዊ ጋዛ ያሉ ሃማስ ይጠቀምባቸዋል ባለቻቸው መሰረተ ልማቶች ላይ የፈፀመች ሲሆን ሃማስ በአፀፋው ሮኬት ተኩሷል።

በእስራኤል በተያዙ ምስራቃዊ የኢየሩሳሌም አካባቢዎች ለሳምንታት እየጋለ የሄደው ውጥረት ከ11 ቀናት በፊት ወደ ውጊያ ማደጉ ይታወሳል።

የእስራኤል የፖለቲካ ካቢኔ የተኩስ አቁሙን ሃሳብ በሙሉ ድምፅ ማፅደቁን ገልጿል። አክሎም ‹‹ የፖለቲካ ክፍላችን የዘመቻው ቀጣይነት የሚወሰነው በመሬት ላይ ባለው ሁኔታ ነው ሲል አፅንኦት ሰጥቷል›› ሲልም አክሏል።

የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስቴር ቢኒ ጋንትስ የጋዛው ጥቃት ‹‹ያልተጠበቁ ትርፎችን አስገኝቶልናል›› ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

አንድ የሃማስ ባስልጣን ለአሶሺየትድ ፕረስ እንደገለፁት እስራኤል የተኩስ አቁም ማድረጓ እንደትልቅ ድል የሚቆጠር እና ይህም ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒናሁ ሽንፈት ነው ብለዋል።

ነገር ግን በሃማስ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክር ቤት አባል የሆኑት ባሴም ናይም ስለተኩስ አቁሙ ዘላቂነት ጥርጣሬ እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል ።

‹‹ለፍልስጥኤማዊያን ፍትህ ሳይመጣ፣ እስራኤልን ወረራዋን እና በእየሩሳሌም በሕዝባችን ላይ የምትፈፅመውን የጭካኔ ተግባር ሳታቆም የሚደረግ የተኩስ አቁም ጠንካራ መሰረት አይኖረውም›› ብለዋል።

የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ አባል ኢዛት አል-ረሺቅ ለእስራኤል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

"እርግጥ ነው ውጊያው ዛሬ ቆሟል። ነገር ግን ኔታኒያሁ እና መላው ዓለም እጃችን በተቀባበለው ጠብመንጃችን ላይ መሆኑን እና ትግላችንም ተጠናክሮ እደሚቀጥል ማወቅ አለባቸው›› ሲሉ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል ።

‹‹ለኔታኒያሁ እና ለሰራዊቱ መግለፅ የምንፈልገው ከተመለሳችሁ እኛም እንደምንመለስ እወቁ ›› ሲሉ አክለዋል።