ዩናይትድ ኪንግደም ከሙስና ጋር በተያያዘ በደቡብ ሱዳንና በደቡብ አፍሪካ ባለሀብቶች ላይ ማዕቀብ ጣለች

ሕንዳውያኑ ነጋዴዎች አጃይ እና አቱል ጉብ

የፎቶው ባለመብት, Gallo Images

የምስሉ መግለጫ, ሕንዳውያኑ ነጋዴዎች አጃይ እና አቱል ጉብታ ከወንድማቸው ራጂሽ ጋር ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከተፈፈመ ሙስና ጋር በተያያዘ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል

ዩናይትድ ኪንግደም ግዙፍ ሙስናን ይፈጽማሉ፣ ያስፈጽማሉ፣ ያሳልጣሉ ባለቻቸው ሃያ ሁለት የተለያየ አገር ዜግነት ባላቸው ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ ጣለች።

ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አስራ አራቱ ሩሲያውያን ናቸው።

ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ይህንን ማዕቀብ የጣለችው በአዲስ የጸረ ሙስና ሕጓ ላይ ተመሥርታ ነው።

ማዕቀቡ የተጣለባቸው ግለሰቦች ከሩሲያውያኑ ሌላ በደቡብ አፍሪካ፣ በደቡብ ሱዳንና በላቲን አሜሪካ የሚገኙ ባለሀብቶች ይገኙበታል።

ማዕቀቡ ሀብታቸው እንዳይንቀሳቀስ ማድረግና የጉዞ ዕግድ መጣልን ያካተተ ነው።

የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶምኒክ ራብ ለፓርላማው እንደተናገሩት አገራቸው በዓለም አቀፉ የጸረ ሙስና ትግል ውስጥ ትልቅ ሚናን መጫወት ትችላለች።

ጨምረውም አገራቸው ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ሙሰኞች ምቹ መናኸሪያ ሆና ቆይታለች ብለዋል።

በአዲሱ የዩኬ የጸረ ሙስና ሕግ መሠረት በዓለም አቀፉ የሙስና መረብ ውስጥ የገቡ ከባድ ሚዛን ሙሰኞች ገንዘባቸውን በአገሪቱ ባንኮች በኩል ማስተላልፍም ሆነ ማስቀመጥ አይችሉም። እንዲሁም ወደ ግዛቷ መግባትም አይፈቀድላቸውም።

አሁን ማዕቀቡ ከተጣለባቸው ውስጥ በጠበቃ ሰርጌይ ማግኔትስኪ የተጋለጡ 14 ግዙፍ የሩሲያ ባለሃብቶች ይገኙበታል። ጠበቃው በእስር ሳለ መሞታቸው ይታወሳል።

በደቡብ አፍሪካ ስማቸው ከውስብስብ ሙስና ጋር የሚነሳው ቢሊየነሮቹ አጃይ፣ አቱል እና ራጄሽ ጉብታም ማዕቀቡ ተጥሎባቸዋል።

በደቡብ ሱዳን በሙስና የሚታሙት ሱዳናዊው አሽራፍ ሰኢድ አህመድ ሑሴን አሊ ወይም በቅጽል ስማቸው አል ካርዲናል ማዕቀቡ ነክቷቸዋል።

ሌሎቹ በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ደግሞ በላቲን አሜሪካ ውስጥ በሚገኙት በሆንዱራስ፣ ኒካራጉዋ እና ጓቲማላ የሚገኙ ሦስት ሚሊየነሮች ናቸው።

ዩናይትድ ኪንግደም ዓለም አቀፍ የሙስና ሰንሰለትን ለመበጣጠስ በግሏ ማዕቀብ ስትጥል ይህ የመጀመርያዋ ነው።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊነከን የዩኬን እርምጃ አድንቀው አገራቸውም ይህን አርአያ እንደምትከተል ቃል ገብተዋል።