ኮሮናቫይረስ፡ አሜሪካ 60 ሚሊዮን የሚጠጋ የኮቪድ-19 ክትባት ለተለያዩ አገራት ልትሰጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ወደ 60 ሚሊዮን የሚጠጋ የአስትራዜኒካ ክትባት ለሌሎች አገራት ልትሰጥ እንደሆነ ዋይት ሐውስ አስታወቀ።
ክትባቶቹ አስተማማኝነታቸው ተረጋግጦ በቀጣይ ወራት ወደተለያዩ አገራት እንደሚላኩ ተገልጿል።
የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ገና ፍቃድ ያልሰጣቸው በርካታ ክትባቶች አሜሪካ ውስጥ ተከማችተው ይገኛሉ።
የተለያዩ አገራት በቂ ክትባት ማግኘት ባይችሉም የአሜሪካ መንግሥት ግን ከሚያስፈልገው በላይ ክትባት እያከማቸ ነው በሚል ሲተች ቆይቷል።
ባለፈው ወር ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አራት ሚሊዮን የአስትራዜኒካ ክትባት ለሜክሲኮ እና ለካናዳ ለመስጠት ቃል ገብተው ነበር።
በሕንድ የኮሮናቫይረስ ስርጭት እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ተከትሎ፤ አሜሪካ ያከማቸችውን ክትባት እንድትለግስ ጫና እየተደረገባት ነው።
አሜሪካ ለክትባት ምርት የሚውሉ ግብዓቶችን ለሕንድ ለመለገስም ቃል ገብታለች።
ከጠቅላይ ሚንስትር ንሬንድራ ሞዲ ጋር የስልክ ውይይት ያደረጉት ፕሬዝዳንት ባይደን፤ ኦክስጅን፣ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ መሣሪያ፣ ክትባትና ሌሎችም ምርቶችን ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር በቀጣይ ሳምንታት የክትባቶቹን ደኅንነት ፈትሾ ፍቃድ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዋይት ሐውስ መግለጫ ይጠቁማል።
ከዚያም ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ የአስትራዜኒካ ክትባት ወደተለያዩ አገራት ይላካል። ለአገራት ይከፋፈላል የተባለው የተቀረው 50 ሚሊዮን ክትባት በተለያየ የምርት ደረጃ ላይ ነው።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ እንዳሉት የትኞቹ አገራት ክትባቱን እንደሚያገኙ በቀጣይ ይገለጻል።
የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ተቆጣጣሪ እስካሁን ፍቃድ የሰጠው ለፋይዘር ባዮንቴክ፣ ለሞደርና እና ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ነው።
እነዚህ ክትባቶች ለአገሪቱ ዜጎች በቂ ስለሚሆኑ ተጨማሪ የአስትራዜኒካ ክትባት እንደማያስፈልግ ተንታኞች ይናገራሉ።
እስካሁን በአሜሪካ ከ53 በመቶ በላይ የሚሆኑ አዋቂዎች የመጀመሪያ ዙር ክትባት አግኝተዋል።
የባይደን አስተዳደር ወደ 60 ሚሊዮን የሚጠጋ ክትባት ለመለገስ ውሳኔ ማሳለፉ "የክትባት ዲፕሎማሲ" ሲሉ ተንታኞች ገልጸውታል።












