ኮሮናቫይረስ፡ በኢትዮጵያ ኮቪድ-19 የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከሩብ ሚሊዮን አለፈ

የኮሮናቫይረስ ህመምተኛ

የፎቶው ባለመብት, AMANUEL SILESHI

በኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ከተረጋገጠ በኋላ ቫይረሱ እንዳለባቸው በምርመራ የተረጋገጠባቸው ሰዎች ቁጥር ከሩብ ሚሊዮን በላይ ሆነ።

ወረርሽኙ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገሪቱ መገኘቱ የተረጋገጠው ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ የነበረ ሲሆን እነሆ ከአንድ ዓመት ከአንድ ወር በኋላ የኮቪድ-19 ቫይረስ የተገኘባቸው አጠቃላይ ሰዎች ቁጥር ከ250 ሺህ ማለፉ ታውቋል።

የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት በየዕለቱ ስለበሽታው አጠቃላይ ሁኔታ የሚያወጡት ሪፖርት ቅዳሜ ሚያዝያ 16/2013 ዓ.ም ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ በሽታው የተገኘባቸው አጠቃላይ ሰዎችን አሃዝ 250,955 ደርሷል።

በኢትዮ በወረርሽኙ የተያዘ የመጀመሪያው ሰው መገኘቱ ይፋ የተደረገው መጋቢት 04/2012 ዓ.ም ሲሆን ከዚያ በኋላ በነበሩት ቀናት ውስጥ በተደረጉ ምርመራዎች የተለያዩ ቁጥሮች ያላቸው ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ሲገኙ ቆይቶ እነሆ ከዓመት በኋላ አሃዙ ከ250 ሺህ ተሻግሯል።

በዚህ መሠረት ከመጋቢት 04/2012 ዓ.ም አስከ ሚያዝያ 16/2013 ዓ.ም ድረስ ባሉት 408 ቀናት ውስጥ በእያንዳንዱ ቀን በአማካይ ከ615 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሲሆን ይህ ቁጥር አሁን ከሩብ ሚሊዮን በላይ ሆኗል።

ይህ ቫይረሱ ያለባቸው አጠቃላይ ሰዎች አሃዝ የተገኘው በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 2 ሚሊዮን 544 ሺህ 095 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ካደረጉት ላይ ነው።

ከእነዚህ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የኮቪድ-19 ቫይረስ ያለባቸው ሰዎች 57 ሺህ 409 ሲሆኑ አብዛኞቹ ወይም 190 ሺህ 013 የሚሆኑት ከበሽታው ማገገማቸውን የአገሪቱ ጤና ጉዳዮች ተቋማት ያወጡት መረጃ አመለክቷል።

ከዚህ ውጪ በወረርሽኙ በአሁኑ ጊዜ በጽኑ ታመው ህክምና እየተደረገላቸው ያሉ ሰዎች ቁጥር 987 ሲሆን አስከ ሚያዝያ 16/2013 ዓ.ም ድረስ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 3 ሺህ 531 ደርሷል።

ይህ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ኮቪድ-19 የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከሩብ ሚሊዮን ማለፉ በአፍሪካ ወረርሽኙ የተገኘባቸው በርካታ ሰዎች ካሉባቸው አገራት ከቀዳሚዎቹ ውስጥ እንድትገኝ አድርጓታል።

የአፍሪካ በሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል መረጃ እንደሚያመለክተው ከደቡብ አፍሪካ፣ ከሞሮኮ፣ ከቱኒዚያ ቀጥሎ ኢትዮጵያ በርካታ ቫይረሱ የተገኘባት አራተኛ አገር ሆናለች።

በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ በአጠቃላይ 4 ሚሊዮን 488 ሺህ 320 ሰዎች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የተመዘገበ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 4 ሚሊዮን 29 ሺህ 494 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።

በአህጉሪቱ ውስጥ በሽታው ከተከሰተ በኋላ 119,645 የሚሆኑ ሰዎች በወረርሽኙ ምክንያት ለሞት መዳረጋቸውን የማዕከሉ መረጃ ያመለክታል።

አስካሁን በዓለም ዙሪያ 146 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በወረርሽኙ ሳቢያ ህይወታቸው ማለፉን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ያመለክታል።