ኮሮናቫይረስ፡ በጥብቅ ተግባራዊ የሚሆነው የኮቪድ-19 መመሪያ ምን ይዟል?

ኮቪድ-19

የፎቶው ባለመብት, Alexander Sanchez

ባለፈው መስከረም ወር ላይ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እየጨመረ የመጣውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና የሚያስከትለው ጉዳት ለመቀነስ በሚል የተለያዩ ክልከላዎች እና ግዴታዎች የያዘ መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል።

ነገር ግን ተግባራዊነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ችላ ተብሎ ቆይቶ ከመረሳት ደረጃ ላይ ደርሷል። ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ግን ወረርሽኙ በአሳሳቢ ደረጃ እየተስፋፋ በመምጣቱ መመሪያውን በተገቢው መንገድ በጥብቅ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት በጤና ሚኒስቴር፣ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና በፌደራል ፖሊስ ተወስኗል።

ይህ "የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጣር የወጣ መመሪያ ቁጥር 30/2013" የሚባል ሲሆን ከመጋቢት 20/2013 ዓ.ም ጀምሮ በጥበቅ መተግበር እንደሚጀምርና ተላልፈው የሚገኙ ሰዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገልጿል።

ለመሆኑ በዚህ መመሪያ ውስጥ የተከለከሉ ተግባራት ምንድናቸው?

  • ማንኛውም ኮቪድ-19 ያለበት ሰው ቫይረሱ እንዳለበት እያወቀ ወደ አገር ውስጥ መግባት፣ ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀል ወይም ቫይረሱ ወደ ሌሎች ሰዎች ሊተላለፍ በሚችልበት ሁኔታ ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘትን ይከለክላል።
  • በእጅ መጨባበጥ እና አካላዊ ንክኪ ማድረግ የተከለከለ ነው።
  • የጤና እክል ካለባቸው እና እድሜያቸው ከ6 ዓመት በታች ከሆኑ ታዳጊዎች ውጪ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።
  • በማናቸውም ተቋማት ውስጥ ሠራተኞች አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው መስራት አለባቸው። ተገልጋዮችም አገልግሎት ማግኘት የሚችሉት የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ሲያደርጉ ብቻ ነው።
  • የትኛውም የትምህርት ተቋምም የጤና መመሪያዎችን ሳይከተል አገልግሎት መስጠት አይችልም።

የተጣሉ ግዴታዎች

  • ኮቪድ-19 በሽታ አለብኝ ብሎ ራሱን የሚጠረጥር ሰው ምርምራ የማድረግ እና ቫይረሱ ወደ ሌሎች እንዳይተላፍ አስፈላጊውን ጥንቃቄ የማድረግ ኃላፊነት አለበት።
  • በሽታው አለበት ተብሎ የሚጠረጠር ሰው ስለመኖሩ የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ለሚመለከተው አካል የማሳወቅ ግዴታ አለበት።
  • ማንኛውም የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ላላደረጉ ሰዎችን አገልግሎት መስጠት የለበትም።
  • መንግሥታዊ እና የግል ተቋም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የጥንቃቄ እርምጃዎች የማክበር እና የማስከበር ግዴታ አለባቸው።
ኮቪድ-19

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

በቤት ውስጥ ማቆያ እክብካቤ ወቅት መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ

መመሪያው ማንኛውም ቀላል ወይም ምንም አይነት የኮቪድ-19 ምልክት የሌለበት ታማሚ በቤት ውስጥ የኮቪድ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ይደረጋል ይላል።

የኮቪድ 19 ታማሚ ወይም በኮቪድ-19 በሽታ ተይዟል ተብሎ የተጠረጠረ ሰው ተለይቶ በተዘጋጀ በቂ የአየር ዝውውር ባለው ክፍል ውስጥ ለ14 ተከታታይ ቀናት መቆየት አለበት።

በቤት ውስጥ ራሱን ለይቶ ያለ ሰው የኮቪድ-19 በሽታ ምልክቶቹ ከተባባሱ ወዲያውኑ ለሚመለከተው ተቋም በስልክ ሪፖርት ማድረግ ይኖርበታል።

ውሸባ እና የድንበር ላይ ጤና ቁጥጥርን በተመለከተ

ከትራንዚት መንገደኛ በስተቀር በአየር ማረፊያ በኩል የሚገባ ከ 10 ዓመት ዕድሜ በላይ የሆነ ማንኛውም ተጓዥ ከመጣበት አገር ከ120 ሰዓት በላይ ያልሆነው የተረጋገጠ ምርመራ ነጻ መሀኑን የሚያሳይ ማስረጃ ይዞ መምጣት አለበት ይላል።

ወደ አገር የሚመጡ ከስደት ተመላሾች ከ120 ሰዓት በላይ ያልሆነው የተረጋገጠ ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ይዘው ካልመጡ፣ ለምርመራ ናሙና ተወስዶ በአድራሻቸው ተመዝግቦ ውጤቱ እስኪመጣ ድረስ በቤታቸው ራሳቸውን ለይተው የማቆየት ግዴታ አለባቸው።

የቀብር ት፣ የአስሬንማጓጓዝ እና የሀዘን በተመለከተ

የሟች ቤተሰብ አስከሬን ከጤና ተቋም ወይንም ከውጭ አገር በሚረከቡበት ጊዜ ከአስከሬኑም ሆነ ከሳጥኑ ጋር ማንኛውም አይነት ንክኪ ያለማድረግ ኃላፊነት አለባቸው።

ከጤና ተቋም ውጪ ሞት ሲከሰት በአስከሬን ግነዛ ሂደት የሚደረግ እንቅስቃሴ ሁለት የአዋቂ እርምጃ ርቀትን በጠበቀ መልኩ መሆን አለበት።

አስከሬን የሚያስተካክሉና የሚገንዙ ሰዎች የእጅ ጓንት፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ፣ ከፕላስቲክ የተሠራ ጋዋን እና እንደ አስፈላጊነቱም የአይን መከላከያ ወይም መነጽር መልበስ አለባቸው።

የሟች ቤተሰብ ሟች በታመመበት ወቅት ተኝቶ የነበረበት አልጋ፣ ሲገለገልባቸው ወይም በዙሪያ የነበሩ እቃዎች፣ የቤቱን ወለልና ሌሎች ከሟች ጋር ንክኪ የነበራቸውን ቁሳቁሶች በጸረ ተህዋሲያን ውህድ እንዲፀዳ የማድረግ ግዴታ አለባቸው።

በለቅሶ ቦታ የተገኘ ማንኛውም ሰው፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ የማድረግ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች የመተግበር ግዴታ አለበት። በቀብር ላይ ከ50 ያልበለጠ ሰው ብቻ መገኘት ይኖርበታል።

ቀብርን በተመለከተ ቤተሰብ አስከሬን ከተገነዘ በኋላ ሟች በ24 ሰዓት ውስጥ እንዲቀበር የማድረግ ኃላፊነት አለበት። በጤና ተቋማት ሞት ከተከሰተ ወይም አስከሬን ከውጭ አገር የሚገባ ከሆነ የሟች ቤተሰቦች አስክሬን ከተቀበሉ በኋላ ወደ ቤት ሳይወስዱ በቀጥታ ወደ ቀብር ቦታ የመውሰድ ግዴታም አለባቸው።

ማንኛውም ለቅሶ ሊደርስ የሚመጣ ሰው የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ የማድረግ፣ ለቅሶ ቤት ከመግባቱ በፊትና ሲወጣ እጅን በውሃና በሳሙና የመታጠብ ወይም በሳኒታይዘር የማፅዳት ግዴታ አለበት።

ኮቪድ-19

የፎቶው ባለመብት, AMANUEL SILESHI

ይማኖታዊ ርዓት እና የአደባባይ በዓላት አከባበርን በተመለከተ

በሐይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ የሚሳተፉ ሰዎች የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ የማድረግ ግዴታ አለባቸው።

ማንኛውም ሐይማኖታዊ ሥርዓት ከሁለት የአዋቂ እርምጃዎች በታች ተጠጋግቶ መፈጸም የለበትም። ቦታው ሊይዝ ከሚችለው ሰው ብዛት ከአንድ አራተኛው በማይበልጥ ሰው ሥርዓቱን መካሄድ ይኖርበታል።

መመሪያው ሕዝብን በብዛት የሚያሳትፉ የአደባባይ ላይ በዓላት ባይደረጉ ይመከራል ይላል። በዓሉን ማክበር ግድ ከሆነ በዓላቱ የሚታደምም ሆነ አከባበሩን የሚያስተባበር ሰው፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ የማድረግ እና በአከባበርም ወቅት ሁለት ሜትር ርቀትን ጠብቆ የመቆምና መቀመጥ ግዴታ አለበት።

በዓላት የሚከበሩባቸው አደባባዮች የሚሸፍኑትን ጠቅላላ ቦታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ቦታው ሊይዝ ከሚችለው ሰው ብዛት ከአንድ አራተኛውን የማይበልጥ ሰው በመያዝ ሥርዓቱን መካሄዱን ማረጋገጥ ይገባል።

በስብሰባ ወቅት መወሰድ ስላለባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች

የጤና መመሪያውን በተከተለ መልኩ ያለተጨማሪ ፈቃድ እስከ 50 ሰው ሆኖ መሰብሰብ ይቻላል።

ከ50 ሰው በላይ መሰብሰብ ግዴታ ሆኖ ከተገኘ ስብሰባው ሊደረግበት የታሰበው አዳራሽን ስፋት ከግምት ውስጥ በማስገባት ቦታው ሊይዝ ከሚችለው ሰው ብዛት ከአንድ አራተኛው በማይበልጥ ሰው ልዩ ፈቃድ ከሰላም ሚኒስቴር እና በተዋረድ ካሉ የሰላም እና ፀጥታ መዋቅሮች አስቀድሞ ማግኘት አስፈላጊ ነው።

ስብሰባውን የጠራው አካል እና ተሳታፊዎች የጤና መመሪያውን የመከተል ግዴታ አለባቸው።

መዝናኛ እና መስተንግዶ ስፍራዎች የሚደረጉ የጥንቃቄ እርምጃዎች

ካፌዎች፣ ባርና ሬስቶራንቶች እንዲሁም መጠጥ ቤቶች በአንድ ጠረጴዛ ከሦስት ሰው በላይ ማስተናገድ የተከለከለ ሲሆን በእያንዳንዱ ጠረጴዛ መካከል የሁለት ሜትር ርቀት ሊጠበቅ ይገባል።

በእነዚህ ስፍራዎች ተገልጋዮች ከሚመገቡበት እና ከሚጠጡበት ወቅት ውጪ እንዲሁም አገልግሎትን የሚሰጡ ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛን የማድረግ ግዴታ አለባቸው።

ተቋማቱ ተገልጋዮቻቸው የሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶችን ከእያንዳንዱ አገልግሎት በኋላ በጸረ ተህዋሲያን ውህድ የማጽዳት ኃላፊነት አለባቸው።

ተጋላጭ የሆኑ የብረተሰብ ክፍሎችን ሚገኙባቸው ተቋማት

የአረጋዊያን መጦሪያዎች እና የማገገሚያ ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በአካል መጠየቅ የተከለከለ ነው።

በማረሚያ ቤቶች ላይ የሚደረግ የታራሚን በአካል የመጎብኘት ሂደት በታራሚው እና በጠያቂው መካከል ሁለት የአዋቂ እርምጃ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ አለባቸው።

ታራሚውም ሆነ ጠያቂው የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ በማስደረግ፣ ጠያቂው ወደ ማረሚያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ከመግባቱም በፊት እና ሲወጣ እጁን በውሃ እና ሳሙና እንዲታጠብ ወይንም በሳኒታይዘር እንዲያጸዳ መደረግ አለበት።

በዚህ መመሪያ የተደነገጉ ክልከላዎችን እና ግዴታዎችን የተላለፈ ማንኛውም ሰው አግባብነት ባለው የወንጀል ሕግ መሰረት ተጠያቂ ይሆናል።