የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር መወያየታቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በአሁኑ ጊዜ በትግራይና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች እየተከሰተ ያለው አገራቸውን እንደሚያሳስባት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለፁ።
ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ትናንት ሰኞ በስልክ ባደረጉት ውይይት ትግራይ ውስጥ ስላለው የሰብአዊ ሁኔታና በሌሎች አካባቢዎች እየተከሰተ ስላለው የደኅንነት ስጋት ማንሳታቸው ተገልጿል።
ቃል አቀባያቸው ኔድ ፕራይስ ውይይቱን በተመለከተ ባወጡት አጭር መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት የውጭ ጉዳይ ኃላፊው በኢትዮጵያ ውስጥ እየተባባሰ ያለው የሰብአዊ ጉዳዮችና የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አሜሪካንን እንደሚያሳስባት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል ብለዋል።
በተጨማሪም በትግራይ ክልል እያደገ የመጣው የረሃብ ስጋትና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ያለው የደኅንነት ሁኔታም ከሚያሳስቧቸው ጉዳዮች መካከል ውስጥ እንደሚገኙ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐቢይ እንዳነሱላቸው ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ጨምረውም ኢትዮጵያና ኤርትራ በደረሱት ስምምነት መሠረት የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል የሚወጡበት ውሳኔ በአስቸኳይ፣ ሙሉ ለሙሉና ሊረጋገጥ በሚችል ሁኔታ እንዲፈጸም አጥብቀው መጠየቃቸውም ተነግሯል።
ከስድስት ወራት በፊት በትግራይ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ አሜሪካና የተለያዩ አገራት የኤርትራ ሠራዊት በጦርነቱ ተሳታፊ እንደሆነ በመግለጽ እንዲወጣ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
በተከታታይ ግጭቱን አስመለክቶ በሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶችና በሌሎችም በሚወጡ ዘገባዎች የኤርትራ ወታደሮች ጾታዊ ጥቃትን፣ ግድያንና የንብረት ውድመትን ጨምሮ በትግራይ ክልል ውስጥ በተፈጸሙ በደሎች ሲከስሱ ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ መንግሥታት ክሱን ሲያስተባብሉ ቆይተው ባለፈው መጋቢት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኤርትራ በህወሓት ኃይሎች በተሰነዘሩባት የሮኬት ጥቃቶች ተገፍታ "የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት" ስለነበራት ወታደሮቿን በድንበር ማስፈሯን መግለጻቸው ይታወሳል።
ከዚህም በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ አሥመራ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር ከተወያዩ በኋላ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ግዛት ለቅቀው እንዲወጡ ከስምምነት መድረሳቸው ቢገለጽም እስካሁን ተግባራዊ መሆኑን የሚያረጋግጥ መረጃ አልወጣም።
አሜሪካ በተደጋጋሚ ከትግራይ እንዲወጡ ስትጠይቅ የቆየችው የኤርትራ ኃይሎችን ብቻ ሳይሆን፣ የአማራ ልዩ ኃይል አባላትን ጭምር ነው።
አሁንም ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ "የኤርትራ እና የአማራ ክልል ኃይሎች በትግራይ ውስጥ እየጨመሩ ባለው ሰብአዊ አደጋ እንዲሁም ለሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አስተዋጽኦ አላቸው" ማለታቸውን የቃል አቀባያቸው መግለጫ አመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የአማራ ክልል ኃይሎችን በተመለከተ አሜሪካን ያነሳችው ጥያቄ "በሉአላዊ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው" ሲሉ አጠንክረው መተቸታቸው ይታወሰል።
ለዚህም በሰጡት ምላሽ የኢትዮጵያ መንግሥት በሉአላዊ ግዛቱ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የጸጥታ ኃይሎችን ስምሪት በተመለከተ የመወሰን ሥልጣን ስላለው አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ የሚፈልገውን ኃይል ጸጥታና ሕግን ለማስከበር የማሰማራት መብት አለው ብሎ ነበር።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በነበራቸው ውይይት፤ በትግራይ ክልል ውስጥ እየተካሄደ ባለው ግጭት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች "ግጭቱን በአስቸኳይ" የማቆማቸውን ነገር አጽንኦት መስጠታቸው ተገልጿል።
መንግሥት በትግራይ ክልል ውስጥ አካሄድኩ ያለው ሕግን የማስከበር ዘመቻ በሦስት ሳምንት ውስጥ የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራሉ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ስትገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ግጭቱ ማብቃቱን ተናግረው ነበር።
ነገር ግን በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች በአንዳንድ አካባቢዎች ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ከመግለጻቸው ባሻገር የአገሪቱ ጦር ሠራዊትም የቀሩ የህወሓት ኃይሎችን ለመደምሰስ ዘመቻዎችን እያካሄደ መሆኑን በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል።
ከዚህ ባሻገርም ብሊንከን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ትግራይ ውስጥ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በጋራ እንዲመረምሩ መወሰኑን በመልካምነቱ አንስተዋል።
ጨምረውም "በደሎችን የፈጸሙ ተጠያቂ ሆነው ለፍርድ እንዲቀርቡ" ማድረግ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደተናገሩት ከግጭቱ ጋር ተያይዞ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን አምነው፤ ምርመራ ተደርጎ በሚገኘው ውጤት መሠረት ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘን ማንኛውንም ወገን መንግሥታቸው ተጠያቂ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።
በቅርቡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ አገራት አሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን በመጪዎቹ ቀናት ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚሄዱም ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የአሜሪካ ምክር ቤት አባሉ ክሩስ ኩንስ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ከሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተው ነበር።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በትግራይ ውስጥ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ትናንት ሰኞ ዕለት አደረጉት ከተባለው ውይይት በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።













