ኮሮናቫይረስ፡ በኦክስጂን እጥረት በርካቶች በሚሞቱባት ሕንድ ሆስፒታል ላይ በተነሳ እሳት 13 ህሙማን ሞቱ

የኦክስጂን መተንፈሻ ጋን የሚጠቀም ህመምተኛ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የኦክስጂን መተንፈሻ ጋን የሚጠቀም ህመምተኛ

ዛሬ አርብ በሕንዷ ከተማ ሙምባይ አቅራቢያ ባለ ኮቪድ-19 ህክምና ሆስፒታል ላይ በተነሳ ቢያንስ 13 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ።

አርብ ጠዋት የተቀሰቀሰው እሳት ለበርካቶች ሞት ምክንያት ከሆነ በኋላ በቁጥጥር ሰር የዋለ ሲሆን ከአደጋው ተረፉት ህሙማን በአቅራቢያ ወደሚገኝ ሆስፒታል ተዘዋውረዋል።

በርካታ ሰዎች በወረርሽኙ እየተያዙባት ባለችው ሕንድ በዛሬው ዕለት ብቻ 332,730 ሰዎች ላይ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን ይህም በዓለም በአንድ ቀን የተመዘገበው የህሙማን ቁጥር ነው ተብሏል።

በበሽታው ሰበብ ህይወታቸው ሚያልፍ ሰዎች አሃዝም እጅግ ከፍተኛ ሲሆን ባለፉት 24 ሰዓታት 2,263 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።

በሕንድ ለሁለተኛ ጊዜ የተከሰተውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ በዋና ከተማዋ ኒው ደልሂ ያሉ ሆስፒታሎች ከፍተኛ የኦክስጂን እጥረት አጋጥሟቸዋል።

በዚህም ኦክስጂን በመጠባበቅ ላይ የነበሩ ታማሚዎች ህይወት እያለፈ መሆኑን እና በሕንድ ምርጥ የተባለ የጤና መሰረተ ልማት ባያላት ኒው ደልሂ ከተማ ለጽኑ ህሙማን የሚሆኑ አልጋዎች ሞልተዋል ተብሏል።

እስከ አሁን ድረስ 16 ሚሊዮን ዜጎቿ በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ሕንድ አረጋግጣለች። ትናንት ሐሙስ ይፋ የተደረገው የ24 ሰዓታት የምርመራ ውጤት ብቻ ከ314 ሺህ በላይ ሰዎች በአንድ ቀን በወረርሽኙ መያዛቸውን እና ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን ያሳያል።

በህሙማን በተጨናነቁት የደልሂ ከተማ ሆስፒታሎ አልጋ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, በህሙማን በተጨናነቁት የደልሂ ከተማ ሆስፒታሎ አልጋ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል

የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ናሬንድራ ሞዲም በቫይረሱ ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸው ግዛቶች መሪዎች እና ከኦክስጂን አምራቾች ጋር ዛሬ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከኒው ደልሂ ውጪ ጉጃራት፣ ኡታር ፕራዴሽ እና ሃርያና የተሰኙት ግዛቶች ተመሳሳይ የኦክስጂን እጥረት ገጥሟቸዋል።

ግዛቶች የኦክስጂን መያዣ ጋኖች ወደ ሌሎች ግዛቶች እንዳይዘዋወሩ በማገድ ላይ ሲሆኑ፤ የተወሰኑ ተቋማት ምርቶቻቸውን ማከማቸት መጀመራቸውን የደልሂ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

በኮቪድ-19 ተይዞ በህክምና ላይ ያለው የሕንድ ፖለቲከኛ ሳውራህ ባራድዋጅ በትዊተር ገጹ የተገጠመለት ኦክስጂን ሊያልቅ የቀረው ሦስት ሰዓታት ብቻ መሆኑን አጋርቶ ነበር።

"ብዙ ሰዎች በኦክስጅን ላይ ጥገኛ ሆነው ነው ያሉት። የተገጠመላቸው ኦክስጂን ሲጠናቀቅ ህይወታቸው ያልፋል። ይህ ጊዜ በጋራ ተባብረን የምንሰራበት ነው" ሲል ተማፅኗል።

በበሽታው ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ በሕንድ ባህል መሰረት የሞቱ ሰዎች አስከሬንን ለማቃጠል ከፍተኛ ወረፋ መኖሩን ቤተሰቦች ገልጸዋል።

አንድ ሐኪም በሆስፒታ ውስጥ ተራ የሚጠብቁ በርካታ አስከሬኖች መኖራቸውንም ገልጿል።