የአፍሪካ አገራት ግዜው ያለፈበት የኮቪድ ክትባትን እንዳያስወግዱ ተጠየቁ

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለም ጤና ድርጅት የመጠቀሚያ ግዜያቸው ያለፈ የኮሮናቫይረስ ክትባት በእጃቸው የሚገኝ የአፍሪካ አገራት ክትባቱን ከማስወገድ እንዲቆጠቡ አሳሰበ።

አገራቱ ቀጣይ መመሪያዎች እስኪሰጡ ድረስ የመጠቀሚያ ግዜያቸው ያለፈባቸውን ክትባቶችን ይዘው እንዲያቆዩ ተጠይቀዋል።

ማላዊ እና ደቡብ ሱዳን በሚያዚያ ወር አጋመሽ ላይ 70 ሺህ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ክትባቶችን ለማስወገድ ማሰባቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው የዓለም የጤና ድርጅት ይህን ማሳሰቢያ የሰጠው።

ማላዊ 16 ሺህ የአስትራ ዜኔካ ብልቃጦችን፤ ደቡብ ሱዳን ደግሞ 59 ሺህ ተመሳሳይ ብልቃጦችን ለማስወገድ አስበዋል።

የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ (ሲዲሲ) ግን ምንም እንኳን ክትባቶቹን ለመጠቀም የተቀመጠው ግዜ ቢያልፍም ክትባቶቹ ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችሉ ገልጾ ነበር።

በዓለማችን ያሉ ሌሎች ክትባቶች ከተመረቱ ጀምሮ እስከ 36 ወር ድረስ ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን የኮቪድ ክትባት ግን አዲስ መሆኑን ተከትሎ ነው ለምን ያህል ግዜ ውጤታማ ሆኖ መቆየት እንደሚችል ገና ያልተለየው።

እነዚህ ግዜያቸው ያለፈባቸውን ክትባቶች ጥቅም ላይ የማዋል ውሳኔ የሚሰጠው በብሔራዊ የመድሃኒት ተቆጣጣሪዎች እንደሆነ የቢቢሲ የጤና ጉዳዮች ዘጋቢ ርሆዳ ኦዲያምቦ ታብራራለች።

የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ዋና ዳይሬክተር ማክሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫቸው ላይ፤ "ለአባል አገራት የማቀርበው ጥሪ ቢኖር፤ እኛ ክትባቱን አስተባብረን ለማቅረብ የራሳችንን ድርሻ እየተወጣን ነው፤ እናንተም ክትባቶቹን በመጠቀም የድርሻችሁን ተወጡ" ሲሉ ተማጽነዋል።

የኮሮናቫይረስ ክትባትን በአፍሪካ በሚፈለገው ፍጥነት እስካሁን ማድረስ ያልተቻለ ሲሆን፤ ለዚህም የአቅርቦት እጥረት እንዲሁም ስለ ክትባቱ ጥርጣሬዎች መኖራቸው እንደ ምክንያት ይነሳሉ።