ለዓመታት ሲፈለግ የነበረው የማፊያ ቡድን አባል ዩቲዩብ ላይ በለቀቀው ቪዲዮ ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለሰባት ዓመታት በፖሊስ ሲፈለግ የነበረ ወንጀለኛ የማፍያ ቡድን አባል በዩቲዩብ ላይ በጫነው ቪዲዮ ላይ ከታየ በኋላ በቁጥጥር ስር ዋለ።
የጣሊያን ፖሊስ የ53 ዓመቱን ማርክ ፌረን ክላውድ ቢያርትንን ለመያዝ የቻለው ግለሰቡ አገር ሰላም ብሎ ምግብ እያዘጋጀ የተቀረጸውን የራሱን ቪዲዮ ዩቲዩብ ላይ ከጫነ በኋላ ነው።
ተፈላጊው ግለሰብ ይህንን ቪዲዮ ሲያዘጋጅ ማንነቱ እንዳይለይ ጥንቃቄ አድርጎ ነበር። በዚህም ቪዲዮው ላይ ፊቱ እንዳይታይ ቢያደርግም ሰውነቱ ላይ ያለው ንቅሳት ግን ፖሊስ እጅ ላይ ጥሎታል።
ቢያርት ራሱን ደብቆ የምግብ አዘገጃጀትን የሚያሳይ ቪዲዮውን በቀረጸበት ጊዜ በሌላው አካሉ ላይ የነበረው ንቅሳት ለዓመታት ሲፈልጉት ለነበሩት ለንቁዎቹ ፖሊሶች የግለሰቡን ማንነት አመላካች ነበር።
በዚህም ግለሰቡ የተደበቀበትን ስፍራ በመለየት ከእጃቸው አስገብተውታል።
ግለሰቡ ንድራንጌታ የታባለው የወንጀል ቡድን አባል እንደሆነ የተነገረ ሲሆን ባለፈው ረቡዕ የተያዘውም ከሚፈለግበት አገር ርቃ በምትገኘው በዶሚኒካን ሪፐብሊክ ውስጥ ነው።
አሁን ለዓመታት ስትፈልገው ለነበረችው ለጣሊያን ተላልፎ ተሰጥቷል።
ፖሊስ የደረሰበትን ለማወቅ ተቸግሮ የነበረው ቢያርት ራሱን ደብቆ ትኩረት ሳይስብ መኖሩን ፖሊስ ገልጿል።
ግለሰቡ አባል በሆነበት የንድራጌታ የማፊያ ቡድን አማካኝነት የኮኬይን ዕጽ ወደ ኔዘርላንድ በማስገባት ወንጀል ምክንያት ላለፉት ሰባት ዓመታት በፖሊስ ሲፈለግ ቆይቷል።
ጣሊያን ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ይህ ማፊያ ቡድን በዓለም ላይ ካሉ የተደራጁ የወንጀለኞች ቡድን ውስጥ ኃያሉ ሲሆን ወደ አውሮፓ የሚገባውን አብዛኛውን ኮኬይን ዕጽ የሚቆጣጠር ቡድን ነው።
የንድራጌታ ማፊያ ቡድንን ይመራዋል የሚባለው የ66 ዓመቱ ሉዊጂ ማንኩሶ "አጎትየው" በመባል ይታወቃል። ሌሎቹም የቡድኑ አባላት በተለያዩ ቅጽል ስሞች ይታወቃሉ።
የቡድኑ መሪዎች እና አባላት በፖሊስ እየታደኑ ፍርድ ቤት እየቀረቡ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የበርካታ አባላቱ ፍርድ ሂደት ጣሊያን ውስጥ እየተካሄደ ነው።
በዚህም 355 የወንጀለኛ ቡድኑ አባላትና ከቡድኑ ጋር ባላቸው ግንኙነት በሙስና የተያዙ ባለስልጣናት ረጅም ጊዜን ከጠየቀ ምርመራ በኋላ ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ክሱ መሰማት በተጀመረበት ወቅት የተከሳሾቹን የስም ዝርዝር ለመጥራት ከሦስት ሰዓት በላይ እንደፈጀ በወቅቱ ኤኤፍፒ ዘግቦ ነበር። ፈጽመውታል የተባለው ወንጀልም ግድያን፣ የዕጽ ዝውውርን፣ በማስገደድ ገንዘብ መቀበልና በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ ማድረግን ይምራል።
ባለፈው ጥር ወር ላይ በተጀመረው በዚህ የፍርድ ሂደት ከ900 በላይ ምስክሮች ለፍርድ ቤቱ ማስረጃዎችን ያቀርባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ውሳኔ ሰጥቶ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመታትን ይፈልጋል ተብሏል።













