ናይኪ የሰው ደም ጠብታ ያረፈበት "የሰይጣን ጫማ" ላይ ክስ መሰረተ

የፎቶው ባለመብት, MSCHF
ናይክ ብሩክሊን የጥበብ ሥራዎችን ሰብሳቢ የሆነው ኤምኤስሲኤችኤፍ (MSCHF) ያመረተው ጫማ ላይ ክስ መሰረተ።
በዚህ አወዛጋቢ ጫማ ሶል ላይ እውነተኛ የሰው ደም ጠብታ ያረፈበት ሲሆን "የሰይጣን ጫማ" በመባል ይታወቃል።
1,018 ዶላር ዋጋ የተተመነለት ይህ ጫማ የተገለበጠ መስቀል፣ አምስት ጫፍ ያለው ኮከብ እንዲሁም ሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ቁጥር 18 የሚል የሰፈረበት ሲሆን የተሰራው ናይኪ ኤይር ማክስ 97ን በማስመሰል ነው።
ኤምኤስሲኤችኤፍ (MSCHF) 666ን ጫማን ሰኞ ዕለት ከራፐር ሊል ናስ ኤክስ ጋር በመሆን ለገበያ ያቀረበው ሲሆን በደቂቃ ውስጥ ተሸጦ ማለቁ ተነግሯል።
ናይክ የንግድ ምልክት ጥሰት በማለት ክስ መስርቷል።
በኤምኤስሲኤችኤፍ (MSCHF) ለገበያ የቀረበው ይህ ጥቁሩና ቀይ ጫማ አርብ ዕለት ከራፐር ሊል ናስ ኤክስ ከለቀቀው "ኮል ሚ ባይ ዩር ኔም" ከሚሰኘው የሙዘቃ ሥራ ጋር ተገጣጥሟል።
በሙዚቃ ቪዲዮው ላይ ራፐሩ ከመንግሥተ ሰማያት ወደ ሲኦል ይህንን ጫማ ተጫምቶ ተንሸራትቶ ሲወርድ ይታያል።
በሙዚቃ ቪዲዮ ላይ የቀረበው ምሰላ እና ጫማው ላይ የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ከቁጥር 18 "ሰይጣንን ከሰማይ እንደመብረቅ ሲወድቅ አየሁ" የሚለውን ጥቅስ ለማስታወስ ነው።
እያንዳንዱ ጫማ የናይኪን ሶል የያዘ ሲሆን 60 ኪዮቢክ ሴንቲሜትር ቀይ ቀለም እና ከጥበብ ሥራዎችን ከሚሰበስበው ድርጅት አባላት የተወሰደ ጠብታ የሰው ደም አለበት።
የስፖርት ጫማ አምራቹ ናይኪ ኒውዮርክ ለሚገኝ ፍርድ ቤት ባስገባው ክስ ላይ ይህንን ተመሳስሎ የተሰራ 'የሰይጣን ጫማ' እንዲመረት አልፈቀድኩም ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, MSCHF
ናይኪ ለችሎቱ ኤምኤስሲኤችኤፍ (MSCHF) ጫማውን መሸጥ እንዲታገድ እንዲሁም ዝነኛ የሆነውን የንግድ ምልክታቸውን እንዳይጠቀም እንዲከለከል ጠይቋል።
ግዙፉ ጫማ አምራቹ በክሱ ላይ"ኤምኤስሲኤችኤፍ (MSCHF) እና ፈቃድ ያላገኘው የሴጣን ጫማው ግርታን፣ ናይኪን ከኤምኤስሲኤችኤፍ (MSCHF) ጋር የተሳሳተ ዝምድና እንዲፈጠር ያደርጋሉ" ብሏል ።
የኤምኤስሲኤችኤፍ (MSCHF) ሰይጣን ጫማ ለገበያ ከቀረበ በኋላ ናይኪ ምርቱን አጽድቆ ለገበያ ያቀረበው የመሰላቸው ደንበኞች የናይኪን ምርት ላለመግዛት ዘመቻ መክፈታቸውን በመጥቀስ ግርታ መኖሩን ማሳያ መሆኑን አመልክቷል።
ወግ አጥባቂ የሆኑ አሜሪካውያን ራፐሩን እና ጫማውን በመቃወም በትዊተር ላይ መልዕክታቸውን አስፍረዋል።












