ኮሮናቫይረስ፡ የአውሮፓ አገራት በአስትራዜኒካ ክትባት ጉዳይ ለሁለት ተከፍለዋል

ጀርመን ውስጥ የአስትራዜኒካ ክትባት ሲሰጥ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, 13 አውሮጳ አገራት ክትባቱን መስጠት አቁመዋል

የአውሮፓ አገራት አስትራዜኒካ ክትባትን ለሕዝባቸው በማደልና ባለማደል ጉዳይ ለሁለት እንደተከፈሉ ናቸው፡፡

ኦክስፎርድ አስትራዜኒካ ክትባት የደም መርጋትን አስከትሏል የሚለው መረጃ ነው አገራቱን እያወዛገባቸው ያለው፡፡

የተወሰኑ አገራት ክትባቱን መስጠት እንደቀጠሉ ሲሆን አንዳንድ አገራት ግን ነገሮች እስኪጠሩ በሚል ያዝ አድርገውታል፡፡

ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ስፔንና ጣሊያን የአውሮፓ ኅብረት ክትባቱን ፈትሾ ችግር የለውም የሚል ሪፖርት ካልሰጠን ለሕዝባችን አናድልም ብለው አቋም ወስደዋል፡፡

ነገር ግን እነ ፖላንድና ቤልጂየም ክትባቱን ለሕዝባቸው መስጠታቸውን እንደቀጠሉ ናቸው፡፡

የአውሮፓ ሜዲካል ኤጀንሲ አስትራዜኒካ ክትባት በእርግጥም የደም መርጋት ያስከትላል ወይ የሚለውን እየመረመረ ሲሆን ነገ ሐሙስ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ትናንት ማክሰኞ የአውሮፓ ሜዲካል ኤጀንሲ በሰጠው መግለጫ ክትባቱ የከፋ የጎንዮሽ ጉዳት እንደሌለው እና ክትባቱን ካለመውሰድ፣ መውሰዱ የተሻለ እንደሆነ እንደሚያምን ተናግሮ ነበር፡፡

የኤጀንሲው ኃላፊ ኤመር ኩክ እንዳሉት የደም መርጋት የተከሰተው ከጠቅላላው ክትባት ወሳጅ እጅግ በተወሰኑ ሰዎች ሲሆን ይህም መከተብን ተከትሎ ስለመሆኑ ገና አልተጣራም ብለዋል፡፡

"ማሳሰብ የምፈልገው ነገር ቢኖር ደማቸው ረጋ የተባሉት ሰዎች ክትባቱን በመውሰዳቸው ነው ያ የሆነው የሚለው ገና አልተረጋገጠም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪዮ ድራጊ የኤጀንሲውን አስተያየት 'ተስፋን የሚሰጥ' ብለውታል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ የዓለም ጤና ድርጅት የሊቃውንት ቡድን ትናንት ማክሰኞ በጉዳዩ ላይ አንዳች ውሳኔ ላይ ለመድረስ ተሰብስቦ የነበረ ሲሆን የደም መርጋቱ ክትባቱን ከመውሰድ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ መረጃ ማግኘት አልቻልኩም ብሏል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው አገራት ክትባቱን መስጠት ማቆም አይጠበቅባቸውም፡፡ ክትባቱን መስጠቱ ነው የሚበጀው ሲል መክሯል፡፡

በታላቋ ብሪታኒያ እስከአሁን ወደ 11 ሚሊዮን ሰዎች ቢያንስ አንዲት ቀንጣት አስትራዜኒካ ክትባትን መውሰዳቸው ተረጋግጧል፡፡ ከ11 ሚሊዮን ዜጎች እስከአሁን የደም መርጋትም ሆነ ሞት ስለመመዝገቡ መረጃ የለም፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ 13 የአውሮጳ አገራት ክትባቱ ‹ለማንኛውም ይቆየን› ብለው እደላውን ያቆሙ ሲሆን ይህን እርምጃ በመውሰድ ረገድ ዴንማርክን የቀደማት የለም፡፡

ከዴንማርክ ሌላ ኖርዌይ አይስላንድ ጀርመን ፈረንሳይ ጣሊያን፣ ሳይፕረስ ስፔን ላቲቪያና ስዊድን ተመሳሳይ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል፡፡

ከትናንት በስቲያ ሰኞ ጀርመን ፈረንሳይና ጣሊያን የአውሮፓ ሜዲካል ኤጀንሲን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ ይፋ አድርገዋል፡፡

ሁሉም የአውሮፓ አገራት የአውሮፓ ሜዲካል ኤጀንሲን ግምገማ ተከትሎ አስትራዜኒካ ክትባትን ለሕዝቦቻቸው ማደላቸውን ይቀጥላሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡