እነ አቶ ጃዋር መሐመድ ከሦስት ሳምንት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት በአካል ቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Jawar Mohammed/FB
በረሃብ አድማ ላይ እንደሚገኙ የሚነገረው እነ አቶ ጃዋር መሐመድ ዛሬ ረፋድ ላይ ፍርድ ቤት ለነበራቸው ቀጠሮ ሲቀርቡ አካላቸው ደክሞ እና ከስተው ታዩ።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ የተከሰሱ የ24 ሰዎችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ዛሬ ጠዋት ላይ ቀጠሮ ይዞ ነበር። ከእነዚህ መካከል እነ አቶ ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ 21 ሰዎች በፍርድ ቤት ተገኝተው ነበር።
ይኹን እንጂ ጠበቆች ደንበኞቻቸው እነ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሐምዛ አዳነ እና ደጀኔ ጣፋ የረሃብ አድማ ከጀመሩ 33 ቀናት እንዳለፋቸው ለፍርድ ቤት ተናግረው፤ ደንበኞቻቸው አሁን ባሉበት ሁኔታ የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠት አይችሉም በማለት ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
ዐቃቤ ሕግም ተለዋጭ ቀጠሮ ቢሰጥ እንደማይቃወም ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።
በዚህም መሠረት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀረ ሽብርና ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮች አንደኛ ችሎት የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ለመጋቢት 6/2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ከድምጻዊ ሃጫሉ ግድያ በኋላ በቁጥጥር ስር የዋሉት እና ክስ ተመስርቶባቸው በእስር የሚገኙት እነ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሸምሰዲን ጠሃ እና ሃምዛ አዳነ በፖለቲከኞች እና በቤተሰብ አባላቶቻቸው ላይ የሚደርሰውን እስር እና ወከባ በመቃወም የረሃብ አድማ ማድረግ ከጀመሩ ከ33 ቀናት በላይ እንዳስቆጠሩ ጠበቆቻቸው ይናገራሉ።

የተከሳሽ ጠበቆች ምን አሉ?
የተከሳሽ ጠበቆች "መንግሥት እና ሕግ ባለበት አገር ደብዳቤ ስናመላልስ ደንበኞቻችን ሕይወታቸው ሊያልፍብን ነው" በማለት የደንበኞቻቸው በሕይወት የመኖር መብት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
ከደንበኞቻቸው መካከል አቶ ጀዋር መሐመድ እና አቶ ሐምዛ አዳነን ጨምሮ አራት ተከሳሾች በጠና ታምመው እንደሚገኙ በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ ጠበቆች ለችሎቱ አስረድተዋል።

ተከሳሾች የሚገኙበት ሁኔታ
የቢቢሲ ሪፖርተር እንደተመለከተው ዛሬ ጋዜጠኞች ወደ ፍርድ ቤቱ ሲገቡ፤ አቶ በቀለ ገርባ ጭንቅላታቸውን በተከሳሽ አረፋት አቡበከር ላይ እንዲሁም እግራቸውን ደግሞ በአቶ ጃዋር መሐመድ ላይ አድርገው በአግዳሚ ወንበር ላይ በጀርባቸው ተኝተው ነበር።
አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ሐምዛ አዳነ ሰውነታቸው እጅጉን ከስቶ እና ጸጉራቸውን ተላጭተው ታይተዋል።
አቶ ሐምዛ አዳነ በሰዎች ድጋፍ ወደ ችሎቱ ሲገቡ የቢቢሲ ሪፖርተር ተመልክቷል።
ችሎቱ ሲጀመር አቶ በቀለ ገርባ በሰዎች ድጋፍ በጀርባቸው ተኝተው ከነበሩበት አግዳሚ ወንበር ተነስተው ተቀምጠዋል።
የተከሳሽ ቤተሰብ አባላት መካከል አንዳንዶቹ በችሎት ውስጥ ሲያለቅሱ ሪፖርተራችን ተመልክቷል።
እነ አቶ ጃዋር ለመጨረሻ ጊዜ ጋዜጠኞች እና ታዳሚዎች በተገኙበት በፍርድ ቤት ቀርበው የታዩት ጥር 27/2013 ዓ.ም ነበር። በዕለቱ የችሎት ውሎውን ለመዘገብ እና ለመከታተል በስፍራው የተገኙ ጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ሠራተኞች ተፈትሸው ወደ ችሎቱ ከገቡ በኋላ በጸጥታ አስከባሪዎች ከችሎቱ እንዲወጡ ተደርገው ነበር።
'የደረሰብን ክፍት ከፍተኛ ነው'

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዛሬው የችሎት ውሎ ከተከሳሾች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ከተቀመጡበት ሳይነሱ እንዲናገሩ ተፈቅዶላቸዋል። አቶ በቀለ ለፍርድ ቤቱ ክብር እንዳላቸው ተናግረው፤ ለሕክምና ወደ ላንድማርክ ሆስፒታል እየተወሰዱ ሳለ፤ መንገድ ተዘግቶባቸው በኃይል ወደ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል መወሰዳቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
"ይህ ቡድን የፍርድ ቤት ትዕዛዝን የማያከብር ነው" ያሉት አቶ በቀለ ገርባ፤ "ጨካኝ የሆነውን ሥርዓትን መታገል እንፈልጋለን። እኛ ላይ የደረሰው ክፋት ከፍተኛ ነው" ብለዋል።
አሁን ባሉበት ሁኔታ ወደፊት በችሎት መቅረብ እንደማይገባቸው የተናገሩት አቶ በቀለ፤ ወደፊት ጤናቸው የሚመለስ ከሆነ ለጤና መቃውስ ዳርገውናል ያሉትን አካል ካሳ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል።
አቶ በቀለ ደብዳቤ በመጻፍ ላንድማርክ በተሰኘው የግል ሕክምና ተቋም እንዳይታከሙ የከለከሉት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

እነ አቶ ጃዋር መሐመድ የረሃብ አድማውን እያደረጉ ያሉት በፖለቲከኞች ላይ የሚደርሰውን እንግልት እና እስር፣ እነሱን ለመጠየቅና የችሎት ሂደታቸውን ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት በሚመጡ ሰዎች ላይ የሚፈጸም እስር እና ወከባ እንዲቆም ለመጠየቅ እንደሆነም ቢቢሲ ከጠበቆቻቸው ለመረዳት ችሏል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የረሃብ አድማው ተከሳሾችን የከፋ አደጋ ላይ እንዳይጥል የቅርብ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን ኮሚሽኑ ባሳለፍነው አርብ ባወጣው መግለጫ አስነብቧል።
"ለታሳሪዎች ምክንያታዊ የሆኑ ጥያቄዎች ተገቢውን አፋጣኝ ምላሽ መስጠትና የእስረኞች ጠያቂዎችን በማረሚያ ቤቱም ሆነ በፍርድ ቤቶች በአግባቡ ማስተናገድ ይገባል" ስለማለታቸው በመግለጫው ሰፍሯል።
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በቁጥጥር ሥር የዋሉት እነ አቶ ጃዋር ከቀረቡባቸው ተደራራቢ አስር ክሶች ስድስቱ እንዲቋረጡ ፍርድ መወሰኑ ይታወሳል።
የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ፤ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ፤ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ የመተላለፍ ክሶች ከተመሰረቱባቸው ክሶች መካከል ሲሆኑ፤ እንዲቋረጡ የተደረጉት ክሶች የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ 1177/2021 ጋር የተያያዙ ናቸው።














