ምርጫ 2013፡ የመራጮች ምዝገባ ወደ ሌላ ጊዜ ተላለፈ

የምርጫ ቦርድ ሎጎ

የፎቶው ባለመብት, NEBE

በዚህ ዓመት ለሚካሄደው ምርጫ የመራጮች መዝገባ ለሌላ ጊዜ መዘዋወሩን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ቦርዱ እንዳለው ለምርጫው ዝግጅት መከናወን ባለባቸው ቀዳሚ ሥራዎች ላይ መዘግየቶች በማጋጠሙ በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የካቲት 22/2013 ዓ.ም እንዲጀመር ታስቦ የነበረው ምዝገባ በሦሰት ሳምንታት ዘግይቶ መጋቢት 16/2013 ዓ.ም እንዲጀመር መወሰኑን ገልጿል።

ለዚህም ከክልሎች የሚጠበቀው የቢሮዎች ትብብር በመዘግየቱ፣ የዕጩዎች ምዝገባ ከተጀመረ በኋላ በነበሩ መስተጓጉሎች፣ የዕጩዎች ምዝገባ በመራዘሙ እና የአስፈጻሚዎችን ገለልተኝነት የማጣራት ሥራን በተገቢው ሁኔታ ለማከናወን ሲባል የመራጮች ምዝገባ ቀን ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፉን አሳውቋል።

ለስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳድር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያና በሐረሪ ክልሎች ከየካቲት 8 እስከ የካቲት 21/2013 ሲካሄድ የቆየ ሲሆን የነበረውን ሂደት በመገምገም ምዝገባው ለተጨማሪ አራት ቀናት እንዲራዘም ማድረጉ ይታወሳል።

ቦርዱ እንዳለው ከዕጩዎች ምዝገባ ጎን ለጎን ገለልተኛ ምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላን እያከናወነ ሲሆን፤ በዚህም ከ140 ሺህ በላይ በምርጫ አስፈጻሚነት የሚሰሩ ግለሰቦችን አዘጋጅቶ ገለልተኝነታቸውን የማጣራት ሥራን እያከናወነ ነው።

ባለፈው ዓመት ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ወደዚህ ዓመት ከተሸጋገረ በኋላ በመጪው ግንቦት ማብቂያና በሠኔ ወር መጀመሪያ ላይ ለማካሄድ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ዝግጅት እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ከትግራይ ክልል በስተቀር በሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ይካሄዳል በተባለው ምርጫ ከአገሪቱ ሕዝብ ግማሽ ያህሉ በመራጭነት ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምርጫ ቦርድ ገልጿል።

በዚህ ምርጫ በመላው አገሪቱ ድምጽ የሚሰጡባቸው ከ50 ሺህ በላይ የምርጫ ጣቢያዎች፣ ከ152 ሺህ በላይ የመራጮች ምዝገባን የሚያከናውኑ ባለሙያዎችና ከ254 ሺህ በላይ ምርጫ አስፈጻሚዎ እንደሚሰማሩ ተገልጿል።