ቻይና በአሜሪካ ላይ የደኅንነት ስጋት ከሚደቅኑ ዋነኛ አገራት መካከል እንደማትቆጠር አዲስ የመከላከያ ሰነድ አሳየ

የፔንታጎን ሕንጻ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር 'ፔንታጎን' ያወጣው አዲስ የብሔራዊ መከላከያ ስትራቴጂ፤ ከእንግዲህ በዋነኛ የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ቻይና ቅድሚያ የሚሰጣት አገር እንዳልሆነች አመለከተ።

በየአራት ዓመቱ የሚታተመው ይህ ሰነድ፤ የመሥሪያ ቤቱ ዋነኛ ትኩረት የአሜሪካ የአገር ውስጥ እና የምዕራባዊው ንፍቀ ክበብ (Western Hemisphere) ደኅንነት መሆኑን ገልጿል። ዋሽንግተን ለረዥም ጊዜያት የአሜሪካውያንን "ተጨባጭ ጥቅሞች" ችላ ብላ ቆይታለች ሲልም ተችቷል።

ፔንታጎን ለአሜሪካ አጋሮች የሚሰጠው ድጋፍ "የተገደበ" እንደሚሆንም ገልጿል። ይህ ሰነድ ይፋ የተደረገው አውሮፓ "የስልጣኔ ውድቀት" እንደገጠማት የሚገልጸው እና ሩሲያን እንደ አሜሪካ ስጋት ያልቆጠረውን የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ስትራቴጂ ከወጣ ከወራት በኋላ ነው።

የብሔራዊ ደኅንነት ስትራቴጂው በወጣበት ወቅት ሩሲያ ሰነዱ ከራዕይዋ ጋር "በአብዛኛው የሚጣጣም" እንደሆነ ገልጻ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2022 የወጣው የቀድሞው የብሔራዊ መከላከያ ስትራቴጂ፤ ቻይና ደቅናዋለች ያለውን "የብዙኃ ዘርፍ ስጋት" ቅድሚያ የሚሰጠው ዋነኛ የመከላከያ ጉዳይ እንደሆነ ገልጾ አስፍሮ ነበር። ከዚያ አስቀድሞ የነበረው የ2018 ሰነድ ደግሞ ለአሜሪካ ደኅንነት "ዋነኛ ፈተና" በማለት የገለጻቸው እንደ ቻይና እና ሩሲያ ያሉ "ለውጥ ፈላጊ ኃይሎችን" ነበር።

አርብ ዕለት የወጣው ባለ 34 ገጽ ሰነድ የትራምፕ አስተዳደር ወደ ሥልጣን በተመለሰ በመጀመሪያው ዓመት ያራመዳቸውን የፖሊሲ አቋሞች የሚያጠናክር ነው።

በዚህ ጊዜ ውስጥ፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰጡት የኦፕሬሽን ትዕዛዝ የቬንዙዌላውን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ይዘዋል። በምሥራቅ ፓስፊክ እና በካሪቢያን አካባቢ ዕፅ ያዘዋውራሉ በተባሉ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል፤ ከሰሞኑን ደግሞ የአሜሪካ ግሪንላንድን የመጠቅለል ፍላጎታቸውን ለማሳካት አጋሮቻቸው ላይ ግፊት እያደረጉ ነው።

ስትራቴጂው በተመሳሳይ፤ ፔንታጎን "ለአሜሪካ ወታደራዊ እና የንግድ እንቅስቃሴ ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች ላይ በተለይም ወደ ፓናማ ካናል፣ አሜሪካ ባሕረ ሰላጤ እና ግሪንላንድ መግባት መቻላቸውን እንደሚያረጋገጥ" ያስረዳል።

ሰነዱ የትራምፕ አስተዳደር አካሄድ "ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ የነበሩት አስተዳደሮች ከተከተሏቸው ዐቢይ ስትራቴጂዎች መሠረታዊ ልዩነት" እንዳለው ይገልጻል። ስትራቴጂው፤ "ከዩቶፒያዊ ሐሳባዊነት ወጥቶ፤ ወደ ጠንካራ ተጨባጭ ገብቷል" ሲሉም አክሏል።

ከቻይና ጋር ያለው ግንኙነት "በጥንካሬ እንጂ በግጭት" እንደማይመራ የሚጠቅሰው ይህ ሰነድ፤ ግቡ "ቻይናን መቆጣጠር፣ ማነቅ ወይም ማዋረድ አይደለም" ሲል አስተዳደሩ የሚከተለውን አካሄድ ጠቁሟል።

ከቀድሞዎቹ የስትራቴጂ ሰነዶች በተለየ መልኩ፤ ቻይና 'ግዛቴ ነች' የምትላት እና ራሷን የምታስተዳድረው ታይዋን ጉዳይ በዚህ ሰነድ ውስጥ አልተጠቀሰችም። ይሁን እንጂ "ቻይናን ጨምሮ ማንኛውም አካል እኛን ወይም ወዳጆቻችንን እንዳይቆጣጠር መከላከል" የአሜሪካ ዓላማዋ መሆኑን ገልጿል።