ትራምፕ ካናዳ ከቻይና ጋር ስምምነት የምትፈጽም ከሆነ 100% ታሪፍ ለመጣል ዛቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ካናዳ ከቻይና ጋር የንግድ ስምምነት የምትፈጽም ከሆነ የካናዳ ምርቶች ላይ 100% ታፊፍ ለመጣል ዛቱ።
"ካናዳ ከቻይና ጋር ስምምነት የምትፈጽም ከሆነ ወዲያውኑ ከካናዳ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገቡ ምርቶች ላይ 100% ታሪፍ እንጥላለን" ሲሉ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገፃቸው ላይ ጽፈዋል።
ትራምፕ ስለየትኛው የንግድ ስምምነት እያወሩ እንደሆነ በማኅበራዊ ሚድያ ልጥፋቸው ላይ አልጠቆሙም።
ባለፈው ሳምንት የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ከቻይና ጋር ስትራቴጂካዊ ጥምረት እንደሚፈጥሩ አሳውቀው ታሪፍ እንደሚቀንሱም ገልጸዋል።
በወቅቱ ትራምፕ እርምጃውን "መልካም ነገር ነው" ብለውት ነበር። ነገር ግን ካርኒ በዳቮስ አሜሪካ የዓለምን ቅርፅ እየቀየረች ነው የሚል ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ በካናዳ እና በአሜሪካ መካከል ያለው ውጥረት ተባብሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትራምፕን ስም ባይጠቅሱም "ኃያላን ሀገራት" የሚፈጥሩትን የምጣኔ ሀብት ጫና ለመቋቋም "መሐል ላይ ያሉ ሀገራት" ጥምረት መፍጠር አለባቸው ብለዋል።
በቀጣይ ቀን ንግግር ያደረጉት ትራምፕ "ካናዳ የምትኖረው በአሜሪካ ምክንያት ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
ትራምፕ ካናዳ እሳቸው የፈጠሩትን የሰላም ቦርድ ለመቀላቀል ቀርቦላት የነበረው ጥሪ መሰረዙንም አስታውቀዋል።
ቅዳሜ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ገፃቸው ሐሳባቸውን ያሰፈሩት ትራምፕ፤ ካርኒ "ካናዳን የምርቶች ማስተላለፊያ ወደብ በማድረግ የቻይና ዕቃዎች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዲገቡ ለማድረግ አስቦ ከሆነ በጣም ተሳስቷል" ብለዋል።
ቢቢሲ ዋይት ሐውስ እና የካርኒ ቢሮን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ጠይቋል።
ካናዳ ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን የንግድ ልውውጥ የሚመሩት ሚኒስትር ዶሚኒክ ሌብላንክ ባወጡት መግለጫ "ከቻይና ጋር የሚደረግ ነፃ የንግድ ስምምነት የለም" ብለዋል።
"ያደረግነው ስምምነት ከታሪፍ ጋር የተገናኙ በርካታ ጉዳዮችን ለመፍታት የተደረገ ነው።"
ሌብላንክ አክለው መንግሥታቸው የካናዳን ምጣኔ ሀብት ጠንካራ ለማድረግ "በመላው ዓለም" ከተለያዩ ሀገራት ጋር የንግድ ጥምረት እየፈጠረ እንደሆነ ገልጸዋል።
ትራምፕ በተደጋጋሚ የሚጥሉትን ታሪፍ ተከትሎ ካናዳ ትልቋ የንግድ አጋሯ ከሆነችው አሜሪካ ገለል በማለት ከሌሎች ሀገራት ጋር የንግድ ስምምነት ለመድረስ እየጣረች ነው።
ባለፈው ሳምንት የቻይናው ፕሬዝደንት ዢ ጂንፒንግ እና ካርኒ በደረሱት ስምምነት መሠረት ቻይና በካናዳ ካኖላ ዘይት ላይ የጣለችውን ታሪፍ ከ85 ወደ 15 በመቶ ዝቅ ታደርጋለች።
ካናዳ በበኩሏ የቻይና ኤሌክትሪክ መኪናዎች ላይ የጣለችውን ታሪፍ ከ100 ወደ 6.1 በመቶ ዝቅ ታደርጋለች።
ለዓመታት በታሪፍ ተሳስረው የቆዩት ሁለቱ ሀገራት ያደረጉት ስምምነት በካናዳ የቻይና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ሊያደርግ ይችላል ተብሏል።
ካርኒ ከቻይና ጋር የተደረሰው ስምምነት ሀገራቸው "ለአዲሱ የዓለም ቅርፅ" የተዘጋጀች እንድትሆን እንደሚያደርጋት ተናግረዋል።















