"ያለ ማህፀን በመወለዴ ጓደኛዬ አርግዛ በመውለድ እናት አደረገችኝ"

የፎቶው ባለመብት, Georgia Barrington
ጆርጂያ ባሪንግተን አዲስ እናት ሆናለች፤ ነገር ግን ልጇን የወለደችው እርሷ አይደለችም። ይልቁንስ ያ አምጦ የመውለድ ቅጽበት በልጅነታቸው ቃል መገባባታቸውን ተከትሎ ሕጻኑን ያረገዘችው የቅርብ ጓደኛዋ ዴዚ ሆፕ ነበረች።
እነዚህ ሁለት ወጣቶች በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ተነጣጥለው አያውቁም። ራሳቸውን "እህትማማቾች ነን" ብለው መጥራት ይመርጣሉ።
አባቶቻቸው የቅርብ ጓደኛሞች በመሆናቸው አብረው ነው ያደጉት።
የልጅነት መቀራረባቸው ከጊዜ በኋላ ሕይወትን ለሚቀይር የልግስና ተግባር መሠረት ሆኗል።
በ15 ዓመቷ ጆርጂያ አንዲት ታዳጊ ልጅ እሰማዋለሁ ብላ የማትጠብቀው ነገር ተነግሯታል።
ያለ ማህፀን የተወለደች በመሆኑ አርግዛ መውለድ አትችልም።
የምርመራው ውጤት ማየር ሮኪታንስኪ ኩስተር ሀውሰር (Mayer-Rokitansky-Küster-Hauser -MRKH) ሲንድሮም እንዳለባት አሳይቷል።
ከአምስት ሺህ ሴቶች መካከል አንዷን የሚያጠቃ ሲሆን ለጆርጂያ ደግሞ የወደፊት ዕጣ ፈንታዋ በአንድ ደቂቃ ውስጥ እንደገና እንደተጻፈ ያህል ተሰምቷታል።
"አሳዛኝ ነበር፣ ዓለሜ በሙሉ ፈርሶ ነበር" በማለት ታስታውሳለች።
"እናት እንደምሆን እያሰብኩ ነው ያደግኩት፤ እና ያ ሕልሜ ከእጄ ተወስዶ ያሰብኩት ነገር ሁሉ ባዶ ሆነ።"
የጆርጂያ ቤተሰብ ምርመራውን እንድትቀበል አግዟታል።
የልጅነት የቅርብ ጓደኛዋ ዴዚም በተመሳሳዩ ከጎኗ ነበረች።
በዚያን ወቅት ዴዚ ወልዶ የመሳም ሃሳብ ባይኖራትም የምርመራው ውጤቱን በግልፅ ታስታውሳለች።
እናም ሁልጊዜ ልጅ መውለድ ለምትፈልገው ጓደኛዋ "ፍትሃዊ ያልሆነ" አጋጣሚ መሆኑን እንደሚሰማት አትዘነጋም።
በኤማ ባርኔት አዘጋጅነት በሚቀርበው ፖድካስት ላይ በቀረበችበት ወቅትም "ጥሩ ስሜት እንዲሰማት እና የዓለም መጨረሻ እንዳልሆነ የተወሰነ ተስፋ እንዲሰጣት ፈልጌ ስለነበር አርግዤ እንደምወልድላት ነገርኳት" ብላለች።
"ያኔ የምናገረውን የገባኝ አይመስለኝም፤ ነገር ግን ይህ ለጆርጂያ የማደርገው ነገር መሆኑን ሁልጊዜ አውቅ ነበር።"

የፎቶው ባለመብት, Georgia Barrington
ከአሥር ዓመት በኋላ ዴዚ የገባችውን የተስፋ ቃል በመከተል በ2023 ሁለቱ ሴቶች ከማህጸን ውጪ የሴት እንቁለልን እና የወንድ የዘር ፍሬን በማዋሃድ ጽንስ እንዲፈጠር የሚደረግበት የአይቪኤፍ ሕክምና ጀመሩ።
ጆርጂያ እገባበታለሁ ብላ የማታስበው ዓለም ውስጥ በመግባት አዋላጅ ነርስ ሆና ሠልጥናለች።
"በአንድ ወቅት ይህ ለእኔ ትክክለኛ ሥራ እንደሆነ ጠየቅኩ" ትላለች። "በእውነቱ ግን እንድፈወስ ረድቶኛል፤ እናም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ልጅ እንደምወልድ አውቅ ነበር።"
ከዓመታት በኋላ ዴዚ የመጀመሪያ ልጇን ወለደች።
ጆርጂያ ደግሞ አዋላጅ ነርሷ በመሆን አጠገቧ ነበረች። እና እናት መሆኗ የገባችውን ቃል ለመፈጸም ያላትን እምነት የበለጠ አጠናከረላት።
"ለልጄ ያለኝ ፍቅር አስደናቂ ነው፤ እናም ሁሉም ሰው እንደዚህ ዓይነት ስሜት ሊኖረው ይገባል ብዬ አስብ ነበር" ትላለች።
ልጇን እንዳረገዘች መጀመሪያ ላይ "ትንሽ ተላላ ሆኜ ነበር " በማለት "ሁሉም ነገር በጥሩ ሁኔታ እንደሚሄድ ገምቼ ነበር" ስትል ታስታውሳለች።
'የመከነው ተስፋ'
የመጀመሪያውን ፅንስ እንደፀነሰች ሁሉም ነገር በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ስለመሰለ ሁለቱም ጓደኛሞች ይሆናል ብለው ያሰቡት እየተሳካ መሆኑን አምነው ነበር።
ነገር ግን በሰባት ሳምንት ውስጥ በተደረገው ምርመራ ባዶ ማህፀን ብቻ ተገኘ።
ጆርጂያ ነርሷ በምርመራው ወቅት ምንም ነገር ማየት እንዳልቻለች የተናገረችበትን ቅጽበት ታስታውሳለች።
"የሆነ ነገር ሲከዳኝ ተሰማኝ፤ እናም የነበረኝ ሁሉም ተስፋዬ ጠፋ።"
"በሕይወቴ በሙሉ እንደዚህ ዓይነት ሐዘን ተሰምቶኝ አያውቅም፤ እናም ሁሉም የእኔ ጥፋት ነው ብዬ አስቤ ነበር" ስትል የመጀመሪያው ሙከራ ሳይሳካ ሲቀር የተሰማትን ትናገራለች።
ጥንዶቹ በሕይወታቸው ውስጥ በጣም አስደሳች ከሆኑት ቀናት ውስጥ አንዱ ይሆናል ብለው ያሰቡት ያ ቀን ካዘኑበት ውስጥ አንዱ ሆነ፤ እናም ከአንድ ሳምንት በኋላ አለመፀነሷ ተረጋገጠ።
ያም ሆኖ ግን ለሁለተኛ ጊዜ ሙከራ አድርገው ዴዚ የተለየ ነገር እንደተሰማት ታስታውሳለች።
"እንደገና እንዳረገዝኩኝ ሳውቅ ዓለም ሁለት ጊዜ ጨካኝ ልትሆን እንደማትችል አስብ ነበር።"

የፎቶው ባለመብት, Georgia Barrington
ከስድስት ሳምንታት በኋላ ጥንዶቹ በአልትራሳውንድ ማሽኑ ስክሪን ላይ ትንሽ የልብ ምት ሲሰማ በሆስፒታል የምርመራ ክፍል ውስጥ ትንፋሻቸውን ውጠው በጉጉት ተቀምጠው ነበር።
ነገር ግን በዚያው ዕለት ዴዚ በጣም ደም ይፈስሳት ጀመረ።
"እንደገና ፅንሱ ችግር ሊገጥመው መስሎኝ ነበር፤ እናም በጣም ፈራሁ" ትላለች።
ለስድስት ሰዓታት ያህል ደም ከፈሰሳት በኋላ ፅንሱ የተቋረጠ መስሏት ነበር፤ ነገር ግን ዶክተሮች ምርመራ ሲያደርጉላት የልብ ምቱ ያለ በመሆኑ እርግዝናው ሙሉ በሙሉ ቀጠለ።
ዴዚ ከመውለጃ ቀኗ ትንሽ ቀደም ብሎ ምጧ መጥቶ ሴት ልጅ በሰላም ተገላገለች።
ጆርጂያ በጣም በመደሰቷ የተነሳ "የሕፃኑን ፆታ ማየት ረስቼ ነበር" ትላለች።
"የሕፃኑን ጭንቅላት እንዳየሁ በደስታ ሰከርኩ፤ እና ሁላችንም እያለቀስን ነበር።"
አሁንም ልጅ እንዳላት ለማመን እየታገለች እንደሆነ የምትናገረው ጆርጂያ "ይህን ጊዜ ወስጄ የ15 ዓመት ልጅ ሳለሁ በዚያ ሕክምና ተቋም የቀዶ ሕክምና ክፍል ለተቀመጠችው ልጅ ባሳያት" ስትል ምኞቷን ትናገራለች።
ጆርጂያ ምን ያህል "ዕድለኛ እና አመስጋኝ" እንደሆነች ስትናገር፣ ዴዚ በበኩሏ የቅርብ ጓደኛዋን ለመርዳት የምትችለውን ሁሉ እንደምታደርግ ሁልጊዜ ታወቅ እንደነበር ገልጻለች።
ዴዚ "ማንም ሰው ከጓደኛው ጋር የማይኖረው ዓይነት ትስስር አለን፤ ምክንያቱም ያጋጠመን በጣም ግላዊ ነገር ነው" በማለት ጓደኝነታቸው ምን ያህል ልዩ መሆኑን ተናግራለች።















