ማጥባት ለተቸገሩ እናቶች የጡት ወተት የምትለግሰው ኬንያዊት እናት

የጡት ወተት የምትለግሰው ቼሊሞ እንጆሮጌ
የምስሉ መግለጫ, የጡት ወተት የምትለግሰው ቼሊሞ እንጆሮጌ

የጡት ወተት ይለገሳል?

ኬንያዊቷ እናት ጡታቸው ወተት አላግት ላላቸው፣ በተለያየ ምክንያት ማጥባት ላልቻሉ እና ልጆቻቸውን የጡት ወተት ማጥባት ለሚፈልጉ እናቶች እየለገሰች ትገኛለች ።

ቼሊሞ ንጆሮጌ የጡት ወተት ፍሪጇ የሞላበትን ቀን ታስታውሳለች።

"የእኔ ፍሪጅ ሞልቶ የእህቴን ፍሪጅ መጠቀም ጀመርኩ" ትላለች እየሳቀች ።

የ36 ዓመቷ እና የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ቼሊሞ ከመጠን በላይ የጡት ወተት እንደምታመርት ተረዳች። ልጇን ካጠባች በኋላ እንኳን በየሳምንቱ ብዙ ሊትር የጡት ወተት ታመነጫለች።

እናም ይህንን አይታ ከማባከን ይልቅ መለገስ ጀመረች።

ለአንድ ዓመትም ያህል የረጅም ጊዜ ጓደኞቿን ጨምሮ ለስምንት እናቶች የጡት ወተቷን መለገስ ጀመረች። አንዳንዶቹ እናቶች ቪዲዮዋን በማኅበራዊ ሚዲያ አይተው የመጡ ናቸው።

"የጡት ወተቷን በፍሪጅ ስታስቀምጥ በቲክቶክ አይቼ ተገረምኩኝ" ትላለች ከቼሊሞ የጡት ወተት የምትቀበለው ማሪያን ኪቢንዳ።

"ከዚያም ጻፍኩላትና 'ሃይ እንዴት አለሽ? ወተት እፈልጋለሁ' አልኳት። በቃ በዚያ ተጀመረ" ብላለች።

ቼሊሞ እስካሁን ከአስራ ሊትር በላይ የጡት ወተት ለግሳለች።

ቼሊሞ የጡት ወተት አሁን ትለግስ እንጂ ገና ማጥባት ስትጀምር ቀላል አልነበረም።

ልጇ የጡቷን ጫፍ ይዞ ለመጥባት ከብዶት ስለነበር፣ ከጡት ጫፍ ላይ የሚጨመር አርቲፊሻል የጡት ጫፍ መሳይ በማስገባት ልጇ በሚጠባበት ወቅት ወተት እንዲወጣ ታደርግ ነበር።

ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ወተቱ መፍሰስ ጀመረ፤ ማጠራቀም ከምትችለው በላይ በፍጥነት ነበር የሚፈሰው።

"ጡቴን ማለብ በጀመርኩበት ወቅት 50 አራስ ህጻናትን ለመመገበ የሚያስችል በቂ ወተት ነበረኝ" ስትል ታስረዳለች።

ከዚያም ይህንን ልምዷን በቲክቶክ ማጋራት ጀመረች።

የጡት ወተት
የምስሉ መግለጫ, የጡት ወተት

ጡት ማጥባት ያለውን ስሜታዊ እና አካላዊ ችግሮችን በማጋራት ነበር የቲክቶክ ቪዲዮዋን የጀመረችው። ከዚያም የጡት ወተት ማስቀመጫ (ማጠራቀሚያ) እና ሊወሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄ ጠቃሚ ምክሮችን ትለግሳለች።

መጀመሪያ ላይ ቪዲዮዋቿን ያዩት ጥቂት ሰዎች ቢሆኑም አሁን ግን ከ16 ሺህ በላይ ተመልካቾች አሏት።

አንዳንዶች ተከታዮቿ እንደሷ የጡት ወተት ምርታቸው ከፍተኛ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ድጋፍ የሚሹ ወላጆች ናቸው።

"የጡት ወተት ለመለገስ የሚፈልጉ በርካታ እናቶች አሉ፤ እንዲሁም መቀበል የሚፈልጉ በርካቶች አሉ" ስትል ታስረዳለች።

ኬንያ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በሚገኘው ፑምዋኒ የእናቶች እና የህጻናት ሆስፒታል የጡት ወተት ባንክ አላት።

ነገር ግን ሆስፒታሉ ልገሳዎችን የሚቀበለው ከታካሚ እናቶች ብቻ ሲሆን፣ ወተቱ ጥቅም ላይ የሚውለውም በሆስፒታሉ በሕክምና ላይ ላሉ ህጻናት ነው።

በዚህም የተነሳ እንደ ቼሊሞ ያሉ ለመለገስ የሚፈልጉ እናቶች ያላቸው መደበኛ አማራጮች ጥቂት ናቸው።

"ከመጠን በላይ የጡት ወተት ለሚያመርቱ እናቶች ወተት የሚቀበል የጡት ወተት ክምችት የለንም" ትላለች ቼሊሞ።

የኬንያ ብሔራዊ የጡት ወተት ባንክ

የኬንያ ብሔራዊ የጡት ወተት ባንክ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የናይሮቢ የሥነ ምግብ ዳይሬክተር ክዋምቦካ ሞጉሱ፣ ፑምዋኒ የእናቶች እና የህጻናት ሆስፒታልን የማስፋፋት ዕቅድ እንዳለ ይናገራሉ።

"ከሆስፒታሉ ውጪ ሌሎች ህጻናትን መደገፍ እንድንችል በከተማዋ ሁለት ተጨማሪ የጡት ወተት ባንኮችን ልናቋቁም ነው" ብለዋል።

የአገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከናይሮቢ አስተዳደር እና ከዓለም አቀፉ የጤና ተቋም ፓዝ (PATH) ጋር በመተባበር በአገር አቀፍ ደረጃ ደኅንነቱ የተጠበቀ የጡት ወተት ልገሳ ተደራሽነትነን ለማሳደግ ግምገማ ማድረጉን አስታውቋል።

የጡት ወተት ባንክን ጨምሮ ከሌሎች የህጻናት አመጋገብ ጋር የተያያዙ ሁኔታዎችን ተቋማዊ ለማድረግ የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አዲስ ብሔራዊ የሥነ ምግብ ፖሊሲ ማዘጋጀት መጀመሩን በሚኒስቴሩ የሥነ ምግብ አገልግሎት ዳይሬክተር ቬሮኒካ ኪሮጎ ይናገራሉ።

"ፖሊሲው የህጻናትን አመጋገብ ለማሻሻል የጡት ወተት ባንክን በመሠረታዊነት ይመለከተዋል፤ እንዲሁም በሰፊው ለአራስ እና ለጨቅላ ህጻነት ጤና አጠባበቅ ሥርዓትን ያዋሃደ መመሪያ ይሰጣል" ብለዋል።

አዋላጅ እና የጡት ማጥባት ባለሙያ ሜሪ ማቲንጌ በበኩላቸው በጡት ወተት አቅርቦት ላይ ክፍተት እንዳለ ይስማማሉ ሆኖም ጥንቃቄ መደረግ አለበት ይላሉ።

ጡት ከሚያጠቡ እናቶች ጋር ከአራት አስርት ዓመት በላይ የሠሩት ሜሪ፣ ኬንያ የጡት ወተት ልገሳን ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ለመቆጣጠር ብሔራዊ ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት ያምናሉ።

"ማንኛውም ህጻን ከማንኛዋም እናት የጡት ወተት መቀበል ይችላል" ይላሉ።

"ነገር ግን በደም የሚተላለፍ ማንኛውም በሽታ በእናት ጡት ወተት ሊተላለፍ ስለሚችል ለጋሿ እናት መመርመር አለባት" ሲሉ አጽንኦት ይሰጣሉ።

"የተለገሰ የጡት ወተትን ለማጣራት፣ ለመከታተል እና ለማከማቸት ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል። በዚህም መንገድ ህጻናት ደኅንነቱን በጠበቀ መልኩ መጠቀም ይችላሉ" ብለዋል።

ቼሊሞ የጡት ወተት የህጻን ቆዳ እንደሚያለሰልስ ስለሚታመን አንዳንድ ጊዜም የተረፈ ወተቷን ህጻን ልጇን ለማጠብ ትጠቀምበታለች።

ነገር ግን አብዛኛው የጡት ወተቷ የሚለገሰው በተለያዩ ምክንያቶች ልጆቻቸውን ማጥባት ላልቻሉ ቤተሰቦች ነው።

በርካቶች ለዚህ ውለታዋ ምስጋናቸውን የቸሩ ሲሆን፤ ከዚህም ባለፈ "ባለወርቅ ፈሳሿ መልዓክ" የሚል ስያሜ ሰጥተዋታል።

ነገር ግን ቼሊሞ ይህ የእሷ ብቻ ጉዞ ሳይሆን እንደሷ በርካታ እናቶች እንዳሉ ታስረዳለች።

ለመጨረሻ ጊዜ የፍሪጅ በሯን ስትዘጋ በጡት ወተት ልገሳ ዙሪያ ያለው ውይይት እንደሚቀጥል እና በርካታ እናቶች ወተት የሚለግሱበት እንዲሁም የሚቀበሉበት መደበኛ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ አሠራር እንደሚዘረጋላቸው ተስፋ ታደርጋለች።

በመጨረሻም ጡት ለሚያጠቡ እናቶች "በማጥባት ቀጥሉ" የሚል መልዕክት አስተላልፋለች።