ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፔሩ፡ ያለፈቃዳቸው እንዲመክኑ የተደረጉ ሴቶች ፍትህ የማግኘት ትግል
ሴራፊና ዪላ በፔሩ ደቡባዊ ተራራማ አካባቢ ላይ በምትገኘው ማዕከላዊ ኩስኮ በአንድ ወቅት ሞታለች ተብላ ነበር።
ያለፈቃዷ የማምከን ቀዶ ሕክምና እንደተደረገላት የምትገልጸው ሴራፊና በአውሮፓውያኑ 1997 ሳታውቅ በተደረገላት ቀዶ ህክምና ላይ በተፈጠረ ችግር ሞታለች ተብላ የሬሳ ማቆያ ክፍል ውስጥ ገብታ ነበር። ነገር ግን ሕይወቷ አላለፈም ነበር።
በዚያው ዓመት በተመሳሳይ ሆስፒታል ቪክቶሪያ ሁዋማን ማደንዘዣ ተሰጥቷት ከሰዓታት በኋላ ስትነቃ መውለድ እንዳትችል እንደተደረገች እንኳን እንዳልተነገራት ትገልጻች። በወቅቱ ቪክቶሪያ የ29 ዓመት ወጣት ነበረች።
ሌላኛዋ ሩዴሲንዳ ኩዊላ የ24 ዓመት ወጣት እያለች በ1996 የህክምና ባለሙያዎች ለአራተኛ ልጇ የውልደት ማረጋገጫ እንዲሰጠው የግድ ከዚህ በኋላ እንዳትወልድ መምካን እንዳለባት ነገረዋት ነበር። ነገር ግን ፈቃደኛ አልነበረችም።
በመጨረሻ ደግሞ በግዴታ እጅና እግሯ ከአልጋ ጋር ታስሮ ማደንዘዣ እንዲሰጣት እንደተደረገ ትገልጻለች። ከሰዓታት በኋላ ስትነቃ ከዚህ በኋላ ልጅ መውለድ እንደማትችል በሕክምና ባለሙያዎች ተነገራት። ይህ መረጃ በአሁኑ ወቅት ተመሳሳይ ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶች ካሳ እንዲከፈል እየተደረገ ባለው የፍርድ ቤት ሂደት ላይ እንደ ማጣቀሻ የቀረበ ነው።
እነዚህ ሴቶች በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ላይ የፔሩ መንግሥት የቤተሰብ ምጣኔን በተመለከተ ባወጣው ፕሮግራም አማካይነት እንዲመክኑ ከተደረጉት በሺዎች የሚቆጠሩ የአገሬው ሴቶች መካከል ናቸው። በወቅቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት አልቤርቶ ፉጂሞሪ ነበሩ።
አሁን አንድ የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የእነዚህ ሴቶች ጉዳይ እየተከታተለው ነው። የፍርድ ሂደቱ ዓላማም እንዚህ ሴቶች ከ25 ዓመታት በኋላ ለደረሰባቸው ጉዳትና ያለፈቃዳቸው እንዲመክኑ በመደረጉ መንግሥት ካሳ መክፈል ይኖርበት እንደሆነ ይመረምራል።
ከ270 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሴቶችና 22 ሺህ ወንዶች ከ1996 እስከ 2001 ድረስ በቤተሰብ ዕቅድ ስም እንዲመክኑ መደረጉን የፔሩ ጤና ሚኒስቴር ይፋዊ መረጃ ያሳያል። አብዛኛዎቹ ደግሞ 'ኩዊንቻ' ከሚባለው አካባቢ የመጡ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ማኅበረሰቦች ናቸው።
የቤተሰብ እቅድ ፕሮግራሙ መጀመሪያ ላይ በፈቃደኝነት የሚደረግ የቀዶ ህክምና አማራጭ እንደሆነ ነበር የተገለጸው። ይህ ፕሮግራም በወቅቱ ከፍተኛ ድህነትን ለመቆጣጠርና ቤተሰቦች ከገቢያቸው ጋር የሚመጣጠን ልጅ እንዲኖራቸው ለማድረግ ያለመ ነበር ተብሏል። መንግሥት እንደሚለው ፕሮግራሙ የተካሄደው በተጠቃሚዎቹ ሙሉ ፈቃደኝነት ነው።
ነገር ግን ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሴቶች እንደሚሉት ተገደው፣ ባለሙያዎች አስፈራርተዋቸው አልያም የተሳሳተ መረጃ ተሰጥቷቸው መውለድ እንዳይችሉ ተደርገዋል።
የፔሩ ዋነኛ ጠበቃዎች የቀድሞው ፕሬዝዳንት አልቤርቶ ፉጂሞሪ እና የካቢኔ አባሎቻቸው ላይ በርካቶችን ባካተተው የቤተሰብ ዕቅድ ፕሮግራም ምክንያት ክስ አቅርበውባቸዋል።
የፕሬዝዳንቱ እና የካቢኔያቸው ጠበቃዎች ደግሞ በወቅቱ በፕሮግራሙ እንዲካተቱ የተደረጉት ሴቶችና ወንዶች በፈቃዳቸው ነው። ነገር ግን 2002 ላይ በተካሄደ ምርመራ የህክምና ባለሙያዎች የተቀመጠውን የሚመክኑ ሰዎች ቁጥር እንዲያሟሉ ከፍተኛ ጫና ይደርስባቸው እንደነበር ተረጋግጧል።
በዚህም ምክንያት ከሚደረግላቸው ቀዶ ህክምና በኋላ ሴቶቹ ሊወልዱ እንደማይችሉ እንኳን ሳይነገራቸው እንዲመክኑ ተደርጓል ብለዋል የተጎጂዎቹ ጠበቆች።
የምርመራው ውጤት እንደሚያሳየው በተለይ ደግሞ ኩዌቻ ከሚባለው አካባቢ የመጡ ሴቶች በቤተሰብ ዕቅድ ፕሮግራሙ ውስጥ እንዲካተቱ ተደርገዋል። አብዛኛዎቹ ደግሞ በጉዳዩ ላይ በቂ መረጃም ሆነ ምን አይነት ህክምና እንደሚሰጣቸው አልተነገራቸውም።
በርካታ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና ጠበቆች በመንግሥት የተካሄደው የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ፕሮግራም የአንድ አካባቢ ሰዎች ላይ ያነጣጠረና ዘረኝነት የታየበት ነበር በማለት መንግሥትን ይከሳሉ። በዚህ ፕሮግራም ውስጥም ቢያንስ 40 የሚሆኑ ሴቶች በህክምናው ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን ይገልጻሉ።
"ምን እንዳደረጉኝ አላውቅም፤ ለምን ይህን እንዳደረጉም ቢሆን አላውቅም" ትላለች ምስክርነቷ በፍርድ ቤት እየተሰማ የምትገኘው ቪክቶሪያ ሁዋማን።
ቪክቶሪያ እንደምትለው በአካባቢዋ ወደሚገኝ ክሊኒክ ሄዳ ስለጉዳዩ እስከሚነገራት ድረስ መውለድ እንደማትችል አታውቅም ነበር። ከባለቤቷ ጋር በመሆን ወደ ክሊኒኩ ሲሄዱ መውለድ እንደማትችል ተነገራቸው።
"ባለቤቴ በቀዶ ህክምናው ምክንያት ጥሎኝ ሄደ። ጥፋቱ የእኔ እንደሆነ ስላሰበ እኔንና ሦስት ልጆቼን ጥሎ ሄደ። በወቅቱ ልጆቼን ለብቻዬ እንደ እናትም እንደ አባትም ሆኜ እንዳሳድግ ተገድጃለሁ። ሁሌም ቢሆን ህመም ይሰማኛል፤ ቀዶ ህክምናው የተደረገልኝ አካባቢ ሁሌም የሚያቃጥልና የሚያም ስሜት ይሰማኛል" ብላለች።
አክላም በአካባቢው የነበሩ የሕክምና ባለሙያዎች እሷ እና ባለቤቷ እንደ አሳማ ልጆችን እየወለዱ እንደሆነ እስከመናገር መሰድረሳቸውን ታስታውሳለች።
"መጀመሪያ ላይ ቀዶ ህክምናውን እንዳደርግ ሲጠይቁኝ እምቢ አልኳቸው። ከዚያም እሺ የማልል ከሆነ ለአራተኛው ልጄ የወሊድ ማረጋገጫ ሰነድ እንደማይሰጡኝ ነገሩኝ። ባለቤቴም በጉዳዩ ላይ እንዲገባ ተደርጎ ነበር። እሱም ቢሆን ግን አሻፈረኝ አለ። ነገር ግን እሺ ብሎ የማይስማማ ከሆነ በቁጥጥር ስር እንደሚውል ነገሩት።"
ቪክቶሪያ ሁኔታው በጣም አስፈርቷት ስለነበር ከክሊኒኩ ለማምለጥ በምትሞክርበት ጊዜ በህክምና ባለሙያዎች ተይዛ እጅና እግሯ ከአልጋ ጋር እንዲታሰር ተደርጋለች። ቀጥሎም ማደንዘዣ ተሰጥቷት እራሷን ሳተች። ከዚያ በኋላ የሆነውን አታስታውስም።
"ቀዶ ህክምናውን ለማድረግ ሆዴ አካባቢ ሲቀዱኝ ሙሉ በሙሉ እራሴን ስቼ ስላልነበረ ህመሙ ተሰማኝ። በጣም እየጮህኩኝ ነበር፤ ከዚያም ተጨማሪ ማደንዘዣ ወጉኝ። ከሰዓት በኋላ ስነቃ ሥራቸውን ጨርሰው ነበር። ከቀናት በኋላ ደግሞ የቁስሉ ህመም ጭራሽ ባሰብኝ" ትላለች።
ህመሙ ሲጠናባት ከባለቤቷ ጋር ወደ ክሊኒኩ ተመልሰው ቢሄዱም ጭራሽ ባለቤቷን እንዳንቋሸሹትና "እንስሳ" እያሉ ይጠሩት እንደነበር ታስታውሳለች። በዚህመ ምክንያት ወደዚያ ክሊኒክ ተመልሰው አልሄዱም።
ጉዳዩ ለምን እስካሁን አልታየም?
ምንም እንኳን የቪክቶሪያ እና ሌሎች መሰል ሴቶች ታሪክ ባለፉት አስርት ዓመታት በስፋት የሚታወቅ ቢሆንም በፔሩ ፍርድ ቤቶች በይፋ ሲቀርቡ ግን አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
እስካሁን ድረስ የፔሩ መንግሥት በአውሮፓውያኑ 1998 ላይ የ33 ዓመቷ ማሪያ ማሜሪታ የቀዶ ሕክምናው ከተደረገላት በኋላ ተገቢው ክትትል ስላልተደረገላት ሕይወቷ ማለፉን ያመነ ሲሆን ህክምናው ሲካሄድም ቢሆን ያለእውቅናዋ ነበር ተብሏል።
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ 2010 (እአአ) ላይ ለዚህች ሴት ሞት ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችን ለመጠየቅ ምርምራ ተጀምሮ ነበር። በፕሬዝዳንት አልቤርቶ ፉጂሞሪ እና የቀድሞ ካቢኔዎች ላይም ሦስት የተለያዩ አይነት የወንጀል ምርመራዎች ተጀምረውባቸው የነበረ ቢሆንም በቂ ማስረጃ ማግኘት ባለመቻሉ ተቋርጧል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት የወሊድ መቆጣጠሪያ ፕሮግራሙ ላይ በቀጥታ ተሳታፊ እንዳልነበሩ የገለጹ ቢሆንም 2002 ላይ አንድ የምርመራ ቡድን ፕሬዝዳንቱ የጤና ኃላፊዎች እንዲመክኑ የተቀመጠውን የሰዎች ቁጥር እንዲያሟሉ ግፊት ያደርጉ እንደነበር ደርሼበታለሁ ብሎ ነበር።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከ2007 ጀምሮ በሙስና እና በሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች ተከሰው እስር ቤት የሚገኙ ሲሆን 2014 ላይ ሴቶችን እንዲመክኑ ከተደረገበት ፕሮግራም ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳልነበራቸው ተረጋግጧል።
የእነዚህ ሴቶች ጉዳይ ለ16 ዓመታት በፍር ቤት የተቀመጠ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን በድጋሚ እንዲከፈት ተደርጓል።
በሺዎች የሚቆጠሩት የእነዚህ ሴቶች ታሪክ አሁን ፍርድ ቤተ ቀርቧል። በፔሩ ያለው ቀርፋፋ የፍርድ ሂደት ምናልባት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ሊያዘገየው ቢችልም ጉዳዩ እንዲህ አደባባይ መውጣቱ ግን በርካቶችን ያስደሰተ ነው።
በአገሪቱ ዜጎች ላይ ያለፈቃዳቸው በተፈጸመው በዚህ ድርጊት የተናሳ ምናልባትም ፍርድ ቤቱ መንግሥት የገንዘብ ካሳ እንዲከፍላቸው ሊበይን ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።