በደቡብ ሱዳን 15 የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ አባላት ወደ አገራቸው አንመለስም ማለታቸው ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አስራ አምስት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ መመለስ አንፈልግም ማለታቸውን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ዘገበ።
እንደ ዘገባው ከሆነ ደቡብ ሱዳን ውስጥ በሰላም ማስከበር ላይ ተሰማርተው የነበሩ 169 ወታደሮች በሌሎች ለመተካት በትናትናው ዕለት ወደ አዲስ አበባ ይመለሱ ነበር።
ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንደማይፈልጉ ያሳወቁት 15 የሰላም አስከባሪው ኃይል አባላት በአጠቃላይ የትግራይ ተወላጅ መሆናቸውም ተገልጿል።
ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የፌስቡክ ገጽ የሠራዊቱ የኢንዶክትርኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል መሐመድ ተሰማን በመጥቀስ የወጣው ዜና ወደ አገር አንመለስም ያሉት የ15ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ አባላት መሆናቸውን አመልክቷል።
ሜጀር ጀነራል ተሰማ እንዳሉት ሻለቃው በደቡብ ሱዳን የነበረውን ቆይታ አጠናቆ ለተተኪው ኃይል ኃላፊነቱን በማስረከብ በመመለስ ላይ እንዳለ አስራ አምስት የሠራዊቱ አባላት ወደ አገር ቤት አንመለስም ብለዋል።
"የጁንታው ተላላኪዎች ወደ አገራችን አንሄድም በማለት ጁባ አየር ማረፊያ ላይ በመንከባለልና በመጮህ ሁከት ለመፍጠር ሞክረዋል" ሲሉ ሜጀር ጀኔራል መሐመድ ተናግረዋል።
የመከላከያ ሠራዊቱ በዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ግዳጅ አኩሪ ተግባር እየፈፀመ እንደሚገኝ በመግለጽ በግለሰቦቹ የተፈጸመው ድርጊት "የሠራዊቱን አባላት የማይወክል አሳፋሪ ተግባር" መሆኑን ሜጀር ጄነራል መሐመድ ተሰማ ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ቃል አባይ የሆኑትን ስቴፋኔ ዱዣሪክን የጠቀሰው የፈረንሳዩ ዜና ወኪል በበኩሉ "ዝርዝር መረጃ ለማግኘት እየሞከርን ነው። ነገር ግን 15 አባላት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ እንደማይፈልጉ በጁባ አየር ማረፊያ እያሉ አሳውቀዋል. . ." ማለታቸው ዘግቧል።
ሱዳን ፖስት የተሰኘው ጋዜጣ በበኩሉ ወታደሮቹ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ የማይፈልጉት በትግራይ ክልል መንግሥት እያካሄደ ካለው "የሕግ ማስከበር" ጋር በተያያዘ የሚደርስባቸውን ባለማወቃቸው ፍርሃት እንደገባቸው መግለጻቸውን ዘግቧል።
በግል የሚታደረው ሱዳን ፖስትን ጨምሮ ተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በትናንትናው ዕለት በጁባ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ኢትዮጵያ ከሚጓዘው ቡድን ጋር ለመሄድ ያልፈለጉ የሰላም አስከባሪ ኃይሉ አባላት ግጭት ውስጥ ገብተው እንደነበር ተዘግቧል።
ወታደሮቹ በግድ ወደ አውሮፕላን እንዲገቡ ሊደረጉ ነበር የተባለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከደረሱ በኋላ ምን ሊደርስባቸው እንደሚችል ስለማያውቁ መስጋታቸውን ተናግረዋል ተብሏል።
እነዚህ ወታደሮች በአሁኑ ሰዓት በደቡብ ሱዳን ብሔራዊ የደኅንነት አገልግሎት ጥበቃ ስር መሆናቸው ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም ለማስከበር በሚያደርገው ጥረት ውስጥ 8 ሺህ ያህል ሠራዊት በማዋጣት ከቀዳሚዎቹ አገራት መካከል አንዷናት። ይህ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት በዓለም ዙሪያ ካሉት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች መካከል 8 በመቶ ያህሉ ነው።
በፌደራል መንግሥትና በህወሓት ኃይሎች መካከል ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት የአገሪቱ ሠራዊት ክልሉን ያስተዳድሩ የነበሩትን የህወሓት አመራሮች ከስልጣን ማስወገዱ ይታወሳል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በርካታ የህወሓት አባል ናቸው የተባሉና በወንጀል የተጠረጠሩ የሠራዊቱ አባላት በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን የእስር ማዘዣ የወጣባቸውና የሚፈለጉ እንዳሉም ይታወቃል።
በወታደራዊ ግጭቱ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ትክክለኛ አሃዝ ባይታወቅም በሺዎች የሚቆጠሩ ሳይሞቱ እንዳልቀሩ ይገመታል።
ከዚህ በተጨማሪም በቀውሱ ምክንያት ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ግጭቱን ሸሽተው ወደ ሱዳን ሲሰደዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ የዕለት እርዳታ ጠባቂ መሆናቸውን ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ይናገራሉ።
በትግራይ ክልል የተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ማብቃቱ በመንግሥት ከተገለጸ በኋላ ሰብአዊ እርዳታ ሰጪዎች ወደ ክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ድጋፍ እንዲያቀርቡ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ስምምነት መደረሱ ይታወሳል።
ነገር ግን እርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር "እጅግ ከፍተኛ " መሆኑን የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ አሳሰቧል።













