ኤር ፎርስ ዋን፡ አንድ ግለሰብ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት አውሮፕላን ማረፊያን ጥሶ መግባቱ ተገለፀ

ይህ አውሮፕላን ማረፊያ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የሚገለገሉበት አውሮፕላን ማረፊያ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሚጠቀሙበት አውሮፕላን፣ ኤር ፎርስ ዋን፣ በሚያርፍበት የጦር አውሮፕላን ማረፊያ አንድ ግለሰብ ጥሶ መግባቱ ተሰማ።

ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካ አየር ሃይል በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚገኙ የአገሪቱ የጦር እሮፕላን ማረፊያዎች ላይ የደህንነት ፍተሻ ሊያደርግ ነው።

ሐሙስ ዕለት አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ ግለሰብ በሜሪላንድ በሚገኝ የጦር አውሮፕላን ማረፊያን ጥሶ መግባቱ ተሰምቷል።

ይህ የጦር አውሮፕላን ማረፊያ የመንግሥት ኃላፊዎች የሚጠቀሙባቸው አውሮፕላንና ሂሊኮፕተሮች ማረፊያ በመሆን ያገለግላል።

አርብ ዕለት የመከላከያ ቃል አቀባይ የሆኑት ጆን ኪርቢ "ሁሉም ሰው ይህንን ጉዳይ በአንክሮ ነው የሚከታተለው" ብለዋል።

የአውሮፕላን ማረፊያውን ጥሶ የገባው ግለሰብ ከጽንፈኛ ቡድኖች ጋር ስላለው ግንኙነት ምንም የተባለ ነገር የለም።

አየር ኃይሉ ባወጣው መግለጫ ተጠርጣሪው በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ወዲያው ውሏል። የተከለከለ ሥፍራን ጥሶ በመግባት ወንጀልም ለፌደራል መንግሥቱ ተላልፎ ተሰጥቶ ክስ ይመሰረትበታል ተብሏል።

ግለሰቡ ጥሶ በገባበት ወቅት ማንም ላይ ጉዳት አልደረሰም ተብሏል።

ተጠርጣሪው ግለሰብ ሁለት ክሶች የሚጠብቁት ሲሆን ዝርዝሩ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

የጦር አውሮፕላን ማረፊያው ከዋይት ሐውስ 24 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን በተደጋጋሚ በአሜሪካ ፕሬዝዳንት፣ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ሌሎች የአሜሪካ ኃላፊዎች ይጠቀሙበታል።

አርብ ዕለት ማታ ፕሬዝዳነት ጆ ባይደን ከዚሁ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስተው መኖሪያ ቤታቸው ወደሚገኝበት ዊልሚንግተን በርረዋል።

የአየር ኃይሉ መርማሪ ጄነራል እንዴት ግለሰቡ ጥሶ ገባ የሚለው ላይ ምርመራ እንደሚደርግ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

አክሎም በመላው ዓለም በሚገኙ የጦር የአሜሪካ ጦር አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ የደህንነት ፍተሻ እንደሚደረግ ተገልጿል።

ይህ አሳሳቢ የሆነ የደህንንት ጥሰት ነው ሲልም ሁኔታውን ገልጸታል።

ይህ ዜና የተሰማው የትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎች ካፒቶል ሂልን ጥሰው ከገቡ ከአንድ ወር በኋላ ነው።

የብሔራዊ ዘብ ሠራዊቶች እስከ መጋቢት ድረስ በዋሺንግተን ግዳጃቸውን እየተወጡ ይቆያሉ ተብሏል።