ሩሲያ የጀርመንን ጨምሮ የሦስት አውሮፓ አገራት ዲፕሎማቶችን አባረረች

በሩሲያ በተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሳትፈዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, በሩሲያ በተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሳትፈዋል

ሩሲያ ለተቃዋሚው አሌክሲ ናቫልኒ በተደረገው ሰልፍ ላይ ተሳትፈዋል ያለቻቸውን የጀርመን፣ ሰዊድን እና ፖላንድ ዲፕሎማቶችን አባረረች።

የሩሲያ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ዲፕሎማቶቹ ጥር 15 በተካሄደው “ሕገ-ወጥ ሰልፍ” ላይ ተሳትፈዋል ብሏል።

የዲፕሎማቶቹን ከሩሲያ መባረር ጀርመን፣ ሰዊድን እና ፖላንድን ጨምሮ ዩናይድት ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና የአውሮፓ ሕብረት ተቃውመዋል።

አሌክሲ ናቫልኒ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን አጥብቆ በመተቸት ይታወቃል።

አሌክሲ በሩሲያ መንግሥት ተመርዟል ከተባለ በኋላ ወደ ጀርመን ለህክምና ማቅናቱ ይታወሳል። አሌክሲ ከህመሙ አገግሞ ወደ ሩሲያ ከተመለሰ በኋላ ለእስር ተዳርጓል።

የአሌክሲን እስር በመቃወም እና ለእርሱ ያላቸውን ድጋፍ የሚገልጹ ሰልፎች ጥር 15 እና 23 በመላው ሩሲያ ተካሂደው ነበር። የሩሲያ መንግሥት ግን “ሕገ-ወጥ” በማለት በከለከለው በዚህ ሰልፍ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን በርካቶችም ለእስር ተዳርገዋል።

ጀርመን የዲፕሎማቷ ከሩሲያ መባረር “በየትኛውም ሁኔታ ምክንያታዊ ሊሆን አይችልም” ያለች ሲሆን ሩሲያ ለዚህ ተግባሯም ትክፍላለች ስትል ጠንከር ያለ መግለጫ አውጥታለች።

ስዊድን በበኩሏ ጥር 15 በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ዲፕሎማቷ መሳተፉን የሚያረጋግጥ ማስረጃ የለም ያለች ሲሆን ሩሲያን ማብራሪያ ጠይቃለች።

ፖላንድ ደግሞ ዲፕሎማቷ ከሩሲያ እንዲባረር መደረጉ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ያሻክረዋል ብላለች።

የአውሮፓ ሕብረት ተወካይ ጆሴፍ ሞሬል፤ ሕብረቱ የሩሲያን ውሳኔ አጥብቆ እንደሚቃወም ከገለጹ በኋላ፤ የአውሮፓ እና የሩሲያ ግነኙነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ጀርመን እና ፖላንድ በአገራቸው የሚገኙ የሩሲያ አምባሳደሮችን ጠርተው በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠየቃቸውን አስታውቋል። አገራቱ ለሩሲያ ውሳኔ ምላሽ ይሆን ዘንድ ከአገራቸው የሩሲያ አምባሳደሮችን ሊያባርሩ እንደሚችሉ ተገምቷል።

አሌክሲ ናቫልኒ ማን ነው?

የ44 ዓመቱ አሌክሴ በሩሲያ ውስጥ እውቅና ያገኘው የባለሥልጣናትን ሙስና በማጋለጥ ነው። በዚህም በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጓል። የፑቲንን ፓርቲ የሞሉት ሸፍጠኞችና ሌቦች ናቸው ይላል አሌክሲ።

በ2011 የፑቲን ዩናይትድ ራሺያ ፓርቲ ምርጫ አጨበርብሯል ብሎ በማጋለጡ ለ15 ቀናት ታስሮ ነበር። በ2013 አሌክሴ በሙስና ክስ ተመስርቶበት ለአጭር ጊዜ ከታሰረ በኋላ ተለቅቋል።

በ2018 ፑቲንን ለመገዳደር ምርጫ ቅስቀሳ ቢጀምርም ቀደም ሲል በነበረበት የምዝበራ ክስ ምክንያት መወዳደር አትችልም በሚል ታግዷል።

በ2019 ፑቲንን የሚቃወም ትልቅ ሰልፍ በመጥራቱ ሕገ-ወጥ የሰልፍ ጥሪ አድርገሀል በሚል ለ30 ቀናት ታስሯል።

ያን ጊዜ በእስር ላይ ሳለ ባልተለመደ ሁኔታ ሕመም ገጥሞት ነበር። ሐኪሞች የቆዳ አለርጂ የሚመስል ነገር ቢጠቅሱም እሱ ግን አለርጂ ኖሮበት እንደማያውቅ ተናግሮ ነበር።

በኋላ ላይ ግን የገዛ ሐኪሞቹ መርዝነት ላለው ነገር ተጋልጠህ ነበር ሲሉ ነግረውታል። ምናልባት እስር ቤት ሳለ እሱን መርዞ ለመግደል ሙከራ ተደርጎ እንደነበር ይገመታል።

ቪላድሚር ፑቲን ከዚህ ቀደም በርከት ያሉ ተቃዋሚዎቻቸውን፣ የስለላ መኮንኖችን፣ ጋዜጠኞችን በጠራራ ጸሐይ በማስገደል እና በሰው አገር ጭምር ሄደው በመመረዝ ስማቸው ይነሳል።

አሌክሲ ባሳለፍነው ነሐሴ ወር ላይ በረራ ላይ ሳለ ተመርዞ እራሱን ስቶ ነበር። የተደረገለት ምርመራ እንደሚያሳየው፤ የተመረዘው ኖቪቾክ በተባለው ኬሚካል ነው።

አሌክሲ ለተጨማሪ ሕክምና በርሊን ወደሚገኝ ቻርቴ የተባለ ሆስፒታል ተወስዶ ነበር።

ከአሌክሲ ጋር የሚሠራው ቡድን እንደሚለው ከሆነ እንዲመረዝ ትእዛዝ ያስተላለፉት ፑቲን ናቸው። የፕሬዘዳንቱ አስተዳደር ግን እጄ የለበትም ብሏል።

አሌክሲ ሕክምናውን ተከታትሎ ከጨርሰ በኋላ ወደ ሩሲያ የተመለሰ ሲሆን አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረሰ ነበር በቁጥጥር ሥር የዋለው።