ጀርመን፡ የተመረዘው ሩስያዊ አሌክሲ ናቫልኒ ወደ ሩስያ ሊመለስ ነው

አሌክሲ በሀኪሞች ተከብቦ

የፎቶው ባለመብት, @NAVALNY

ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲንን አጥብቆ በመተቸት የሚታወቀው ሩስያዊው አሌክሲ ናቫልንሊ ወደ ሩስያ ሊመለስ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናገሩ።

አሌክሲ መመረዙን ተከትሎ ጀርመን ውስጥ ሕክምና ሲደረግለት ነበር። ቃል አቀባዩ ኪራ ያርሚሽ “ወደ ሩስያ አይመለስም ብሎ ማሰብ አስገራሚ ነው” ብለው ትዊት አድርገዋል።

አሌክሲ ከተመረዘ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተነሳውን ፎቶግራፍ በኢንስታግራም ገጹ ላይ ለጥፏል።

ፎቶው ላይ አሌክሲ በሀኪሞች ተከብቦ ይታያል። ያለ ቬንትሌተር ድጋፍ መተንፈስ መጀመሩንም ኢንስታግራሙ ላይ ጽፏል።

አሌክሲ ነሐሴ 20 በረራ ላይ ሳለ ነበር ራሱን የሳተው። የተደረገለት ምርመራ እንደሚያሳየው፤ የተመረዘው ኖቪቾክ በተባለው ኬሚካል ነው።

መመረዙ እንደታወቀ በርሊን ወደሚገኝ ቻርቴ የተባለ ሆስፒታል ተወስዷል።

ከአሌክሲ ጋር የሚሠራው ቡድን እንደሚለው ከሆነ እንዲመረዝ ትእዛዝ ያስተላለፉት ፑቲን ናቸው። የፕሬዘዳንቱ አስተዳደር ግን እጄ የለበትም ብሏል።

ከዚህ ቀደም የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ሩስያ ስለ ኖቪቾክ ፕሮግራሟ ለዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎች መረጃ መስጠት ማለቱ ይታወሳል።

የመብት ተሟጋቹ አሌክሴ ናቫልኒ መመረዙን ተከትሎ ሩስያ ስለ ኖቪቾክ ነርቭ ኤጀንት (መርዛማ ኬሚካል) መረጃ እንድትሰጥ ተጠይቃ ነበር።

የኔቶ ጸሐፊ ጄንስ ስቶልበርግ አባላቱ ጥቃቱን አውግዘዋል ብለዋል። የመብት ተሟጋቹ በኖቪቾክ እንደተመረዘ “ማስረጃ አለ” ሲሉም አክለዋል።

ሩስያ ግን ለአሌክሴ ሕክምና እያደረገ የነበረው ሆስፒታል የሰጠውን ማብራሪያ አጣጥላለች።