እስራኤልና አረቦቹ ሰላም ማውረዳቸው ለአካባቢው የሚያመጣው 5 ስጋትና በረከት

የእስራኤል ብሔራዊደህንነት አማካሪ ሜይር ቤን ሻባትና ከኤምሬት ባለስልጣናት በአቡዳቢ አየር ማረፊያ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከእስራኤል አቻዎቹ ጋር ታሪካዊ የተባለ ስምምነት ይፈርማሉ፤ ዛሬ ማክሰኞ በዋይት ሐውስ፡፡

ቀጥለው ደግሞ ባሕሬኖች ተመሳሳይ ፊርማ ያኖራሉ፤ አሁንም ከእስራኤል ጋር፡፡

ይህ በአካባቢው አገራት ዘንድ የሚያመጣው ለውጥ ምንድነው፡፡ 5ቱን ብቻ እንደሚከተለው ቃኝተናል፡፡

1. የጦር መሣሪያ ንግድ ይጦፋል

ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ራሷን የአካባቢው አለቃ ማድረግ ትሻለች፡፡ ለዚህ ተፈሪነት የሚያበቃትን የጦር ጡንቻ ግን ገላ አላወጣችም፡፡ ጡንቻውን ለማፈርጠም የሚሆን ገንዘብ አላት፣ ቴክኖሎጂ የላትም፡፡

ኢማራቶች ቴክኖሎጂ ለመግዛት እንጂ ለመፍጠር አልበቁም፡፡

አሜሪካ ኢምራቶችን ከእስራኤል ጋር ስታፈራርም፣ ኢምሬቶች ጭራሽ እጃችን ይገባሉ ብለው አስበዋቸው የማያውቁ ውስብስብ የጦር መሣሪያዎችን ከእስራኤል መሸመት ያስችላቸዋል፡፡

ኤፍ-35 (F-35 )ተዋጊ ጄት፣ ኢኤ-18ጂ (EA-18G) የተራቀቁ የጦር መሣሪያዎችን የራሳቸው ለማድረግ ቋምጠዋል፡፡፡፡

ኢምራቶች በሊቢያና በየመን እጅግ የተራቀቁ የጦር መሣሪያዎችን ሞክረዋቸዋል፡፡ ሊቢያና የመን ግን እንኳን ተዋጊ ጄት ተወርዋሪ ቀስትም ለመመከት በሚችሉበት ቁመና ላይ አይደሉም፡፡

ውስብስብና ረቂቅ የጦር መሣሪያ የምትቋቋም አገር ኢራን ናት፡፡ ዋናዋ ጠላት አገርም ኢራን ናት፡፡ ለሷ የሚመጥን መሣሪያ ማግኘት የሚፈልጉት ደግሞ ከእስራኤል ነው፡፡

ኢምራቶችንና እስራኤልን የሚያፋቅራቸው የጋራ አጀንዳ እምብዛምም የላቸውም፡፡ የጋራ ጠላት ኢራን ግን ታቀራርባቸዋለች፡፡

የባህሬንም ጉዳይ ከዚህ ተለይቶ አይታይም፡፡

በ1969 ኢራን ባህሬንን አንቺ እኮ ሉአላዊት አገር ሳትሆኚ አንድ ግዛቴ ነሽ ብላት ታውቃለች፡፡

ይህ ለባህሬኖች እስከዛሬም እንቅልፍ የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡

ባሕሬንን የሚመሯት ሱኒዎች ናቸው፡፡ ከ60 ከመቶ በላይ ሕዝቧ ግን የሺአ ኢስላም ተከታይ ነው፡፡ የኢራን በአካባቢው ጎልቶ መውጣት ሁልጊዜም የባሕሬን ገዢዎችን እንቅልፍ ይነሳል፡፡

ገልፍ አገሮች ከኢራን ጋር ንግድ ለማጧጧፍ እንደቋመጡ ነው የኖሩት፡፡ በአካባቢው ብቻም ሳይሆን በዓለም ደረጃም ካየን ውስብስብ ቴክኖሎጂ ፈጠራ እስራኤልን የሚያህል የለም፡፡

ገንዘብ ገልፎች አላቸው፣ ቴክኖሎጂ እስራኤሎች አላቸው፡፡ ከዚህ በላይ ንግድ ከየት አለ?

ከዚህ ሌላ እስራኤሎች በአረብ አገራት በረሃዎች ግመል እየጋለቡ "ሽር-ብትን" ማለት ይፈልጋሉ፡፡

ዱባይ መጥተው የነዳጅ ገንዘብ ምን ተአምር እንደሚሰራ ማየትና መዝናናት ይፈልጋሉ፡፡

ይህ ከጦር መሣሪያ ንግድ ሌላ ሁለቱን አገራት ሊያቀራርብ የሚችል የቱሪዝም ንግድ ነው፡፡

2. እስራኤል ጎረቤት ጠላቶቿን ትቀንሳለች

እስራኤል በአካባቢው ከጎረቤት የተኳረፈች፣ የተገለለች ሆኖ መታየትን አትፈልግም፡፡

ከተወለደች ጀምሮ በጠላት አኩራፊዎች ተከባ ነው የኖረችው፡፡

የቴክኖሎጂና ሳይንስ ምጥቀቷ ረድቷት እንጂ ጎረቤቶቿ ሰልቅጠው ሊጎርሷት በቻሉ ነበር፡፡ ለሕልውናዋም አደጋ ይሆን ነበር፡፡

የኢራን አንዳንድ መሪዎች አልፎ አልፎ እንደሚናገሩት ዓይነት ‹መካከለኛው ምሥራቅ ሰላም የሚሆነው እስራኤል ከዓለም ካርታ ስትጠፋ ነው›› የሚል እይታ ያላቸው በርከት ያሉ የአረብ አገራት ዜጎች አልጠፉም፡፡

ይህን በጠላት ተከቦ ጥሩ እንቅልፍ ለረዥም ዘመን መተኛት እንደማይቻል እስራኤሎች ገና ድሮ ነው ያወቁት፡፡ ገና አገር ሳይሆኑ፡፡ ገና በዛዮኒስት እንቅስቃሴ ጊዜ፡፡

ቤንያሚን ናታንያሁ ‹‹አይረን ዎል›› በሚባለውና በ1920ዎቹ በቪ አልሽላይም ለተጻፈው ፖሊሲ ይገዛሉ፡፡

‹‹እኛና አረቦች›› የሚለው ይህ የውጭ ፖሊሲ ሰነድ እስራኤል በአረቦች ተከባ በእኩል ታፍራና ተከብራ መኖር የምትችለው በጦር ጥንካሬዋ ብቻ ነው ይላል፡፡

‹‹አይረን ዎል›› ፖሊሲ እስራኤሎች እንደ ብረት የማይበገሩ ሲሆኑ ብቻ የአካባቢው አገራት እውቅና ለመስጠት እንደሚገደዱ የሚተነትን ሐሳብ ነው፡፡

እስራኤል በፈረጠመች ቁጥር አረቦች ልእልናዋን ከመቀበል የተሻለ አማራጭ አይኖራቸውም፡፡

እስራኤሎች በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ እንደ እብድ መታየት አይፈልጉም፡፡ መገለል አይፈልጉም፡፡ ታፍቶና ተከብሮ መኖርን ነው የሚፈልጉት፡፡

በዚህ ረገድ ከኃያሉ ጦርነት በኋላ ከዮርዳኖስና ከግብጽ ጋር ወዳጅነትን አሳክተዋል፡፡

ባህሬንና ኢምራቶችን ደግሞ አሁን አሳምነዋል፤ ዕድሜ ለወዳጃቸው ዶናልድ ትራምፕ፡፡ አሁን የሚቀሯቸው አገራት ብዙም አይደሉም፤ ሳኡዲ አረቢያ ደጅ ላይ ናት፤ ኦማንና ኳታር መከተላቸው አይቀርም ይላሉ ፖለቲካ አዋቂዎች፡፡

ሌላው የእስራኤሎች ደስታ ከጠላት ጋር የውዴታ ግዴታ እርቅ መፈጸማቸው ብቻ ሳይሆን አረቦቹን ከኢራኖች መነጠል መቻላቸው ነው፡፡

ናታንያሁ በምድር ላይ እንደ ኢራን ጠላት የለንም ብለው ያምናሉ፡፡ የኢራን ባለሥልጣናትን የሚያወዳድሯቸው ከነ ሂትለርና የናዚ ባለሥልጣናት ጋር መሆኑ የጠላትነት ስሜታቸው የት እንዳለ በራሱ የሚናገር ነው፡፡

3. ትራምፕ ኖቤልን ሊመኙ ይችላሉ

እነዚህ ይሆናሉ ተብለው ያልታሰቡ ስምምነቶች በሙሉ ያለ ዶናልድ ትራምፕ የሚታሰቡ አልነበሩም፡፡

ትራምፕ ዋናው ግባቸው ኢራንን ትንፋሽ ማሳጠር ነው፡፡ ቀጥሎ ለወዳጅ አገር እስራኤል ውለታ መዋል፡፡ በዚህም በኅዳር ወር ምርጫ ደጋፊዎቻቸውን ማኩራትና ዳግም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መሆን፡፡

ዶናልድ ትራምፕ አሁን በከፍተኛ ሩጫ ላይ ናቸው፡፡ ስምምነቶቹን እያጣደፏቸው ያሉትም ከምርጫው በፊት በዓለም መድረክ ሰላም ፈጣሪ ሆነው ለመታየት ካላቸው ፍላጎት ነው፡፡

ትራምፕ ለቤንያሚን ናታንያሁና ለእስራኤል መልካም ውለታ በዋሉ ቁጥር በአሜሪካ ክርስቲያን ኢቫንጀሊካኖች ዘንድ ይጨበጨብላቸዋል፡፡

የትራምፕ ቀንደኛ ደጋፊዎችና አስተማማኝ ድምጽ ሰጪዎች ደግሞ ክርስቲያን ኢቫንጀሊካን ነጭ አሜሪካዊያን ናቸው፡፡ እነሱ ተደሰቱ ማለት ትራምፕ ዋይት ሐውስን ለሌላ አራት ዓመት ተከራዩት ማለት ነው፡፡

በቅርብ ጊዜ አገራትን ዋሺንግተን እየጠሩ እያስታረቁ ነው፡፡ እጅግ የሚመኙትን ኖቤል ሽልማት ይዛችሁልኝ ኑ ማለታቸው የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡

4. ፍልስጥኤሞች ተክደዋል

ኢምሬቶች ውስብስብ የዘመኑን የቢሊዮን ዶላር መሣሪያ ሲሸምቱ ፍልስጥኤሞች መድኃኒት በልመና፣ መብራት በፈረቃ ነው የሚያገኙት፡፡

ውሃ በቧንቧ ስትፈስላቸው የሚደሰቱበት ደረጃ ደርሰዋል፡፡ የድህነት አዘቅት እየነካካቸው ነው፡፡

ሆዳቸውን እያከኩም ቢሆን የኢምሬቶችን ‹‹የአብረሃም ስምምነት›› በፍልስጤም ልጆች ላይ የተፈጸመ ክህደት ሲሉ ጠርተውታል፡፡

የትኛውም አረብ አገር በፍልስጥኤሞች ነጻነት ዙርያ ላለመደራደር ቃል ተገባብቶ ነበር፡፡

ይህ ግን አሁን ያረጀ ያፈጀ ቃል ይመስላል፡፡ ቃል የሚያረጅ ከሆነ ማለት ነው፡፡

አሁን ፍልስጥኤሞች በሀብታም አረብ አገሮች ዘንድ የእርዳታ ስንዴ የሚሰፈርላቸው እንጂ የውጭ ፖሊሲ የሚታጠፍላቸው ሕዝቦች አልሆኑም፡፡

በአሁኑ ሰዓት ጋዛ ትልቅ እስር ቤት ሆናለች፡፡

ምሥራቅ እየሩሳሌምና ዌስት ባንክ በጉልበት የተያዙ የፍልስጤም ግዛቶች ናቸው፡፡ ዓለም እንኳን ይህን አይክድም፡፡ እስራኤልም ይህን አትክድም፡፡

የአቡዳቢው ልዑል ቢሊየነሩ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን የኢምሬቶች ቅቡል መሪ ነው፡፡ እሱ ፍልስጤሞችን አልረሳችሁም ይላል፡፡

እንዴት ሲባል በዚህ ስምምነታችን ውስጥ እስራኤል ከእንግዲህ የዌስት ባንክን ሰፊ ክልል እንዳትጠቀልል ነግረናት እሺ ብላናለች ብሏል፡፡

ናታንያሁ የዓለም አቀፍ ግፊት ተጭኗቸው በዌስት ባንክ ጉዳይ ዝምታን ቢመርጡም በእርግጥ የዌስት ባንክን የእስራኤል ግዛት አካል አድርጎ ለመጠቅለል የታሰበው ነገር ቀርቷል ማለት ግን አይደለም፡፡ ለጊዜው ስለሱ ባናነሳስ የተባባሉ ይመስላል፡፡

ሳኡዲ የፍልስጥኤሞች ጠበቃ ሆና ኖራለች፡፡ አሁን ግን የበቃት ይመስላል፡፡ ኢምሬቶች ያለ ሳኡዲ እንዲህ ያለ ስምምነትን በፍልስጥኤሞች አናት ላይ እየደነሱ ሊፈጽሙ አይችሉም ነበር ይላሉ ተንታኞች፡፡

ይህ የሚያሳየው ሳኡዲ አረቢያ እንኳን ለፍልስጥኤሞች ጀርባዋን መስጠቷን ነው፡፡

የሳኡዲው ንጉሥ፣ ከዛሬ ነገ ይቺን ምድር ይሰናበታሉ የሚባሉት ንጉሥ ሳልማን ናቸው፡፡ የሁለቱ ቅዱስ የኢስላም ቦታዎች የበላይ ጠባቂ ናቸው፡፡ በድፍረትና በይፋ እስራኤልን ወዳጅ አገር ብለው የሚጠሩበት ዕድሜ ላይ አይደሉም፡፡

ወራሻቸው ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን ግን ስለ ፍልስጥኤሞች የሚያሳስበው ሰው አይመስልም፡፡ የአባቱን ሞት ተከትሎ ከእስራኤል ጋር ይሻረካል ይህ በጭራሽ አያጠራጥርም ይላሉ አካባቢውንና ፖለቲካውን በቅርብ የሚከታተሉ፡፡

5. ኢራን አዲስ ራስ ምታት ጀምሯታል

ኢምራቶችና ባሕሬን ይህን ስምምነት በዶናልድ ትራምፕ አሰናጅነት ለመፈጸም መስማማታቸው እንደተሰማ ከፍልስጤሞች ቀጥሎ ጨጓራቸው የተላጡት ዜጎች የሚገኙት በቴህራን ነበር፡፡

‹‹የኢስላም ከሐዲዎች›› ብለዋቸዋል ሁለቱን አረብ አገራት፡፡

የ‹‹አብርሃም ስምምነት›› ተብሎ የሚጠራውን የኢምራቶችና የእስራኤል የዛሬ ስምምነት ሲፈረም ኢራኖች ሌላ ራስ ምታት ይጀምራቸዋል፡፡

የመጀመርያው ራስ ምታት የትራምፕ ጨካኝ ማዕቀብ ነው፡፡ ማይግሪን ቢባል ይቀላል፡፡

አላላውስ ብሏቸዋል፡፡

አሁን ደግሞ የስትራቴጂክ ራስ ምታት ጀምሯቸዋል፡፡ ይህ ከዛሬ ከሰዓት የሚጀምር ራስ ምታት ነው፡፡

ከዚህ ቀደም የኢራን ጠላቶቿ ቢያንስ ተከፋፍለው ነበር የቆሙት፤ አሁን በአንድ ሊቆሙ ነው፡፡ የአካባቢው የተገለለችው አገር እስራኤል ነበረች፤ ቀጣይዋ ግን ራሷ ኢራን ሆናለች፡፡