ሔዝቦላ ከሌባኖስ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን አስወነጨፈ

ሔዝቦላ ያስወነጨፋቸው ሮኬቶች ያደረሱት ጉዳት መጠን አልታወቀም

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሔዝቦላ ያስወነጨፋቸው ሮኬቶች ያደረሱት ጉዳት መጠን አልታወቀም

መቀመጫውን ሌባኖስ ያደረገው የሺዓ ሙስሊም ታጣቂው ቡድን ሔዝቦላ ከሌባኖስ ሆኖ በርካታ ጸረ-ታንክ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፉ ተነገረ።

ሔዝቦላ እስራኤል ላይ ይህን ጥቃት የሰነዘረው እስራኤል ባለፈው ሳምንት የሌናቦስ መዲና ቤሩት ለፈጸመችው የድሮን ጥቃት ምላሽ እንዲሆን ነው ብሏል።

የሮኬት ጥቃቶቹ በወታደሮች እና በጦር ተሽከርካሪ ካምፕ ላይ መፈጸሙን የእስራኤል ጦር አረጋግጧል።

የእስራኤል ጦርም በደቡባዊ ሌባኖስ በሚገኙ የሔዝቦላ ካምፖች ላይ ጥቃት በመሰንዘር የአጸፋ ምላሽ ሰጥቷል።

የሔዝቦላ ምንጮች ሔዝቦላ እስራኤል ላይ በፈጸመው ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ይላሉ። ይሁን እንጂ የእስራኤል መንግሥት በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ብሏል።

ጥቃቱ ከተፈጸመበት ስፍራ እየወጡ ያሉ መረጃዎችን እንደሚጠቁሙት ከሆነ፤ የሮኬት ጥቃት የተፈጸመባቸው ነዋሪዎች ጥቃቱን በመሸሽ ጉድጓድ ውስጥ ተሸሸገው እንደነበር ያመላክታል።

ሔዝቦላ የፈጸመው የሮኬት ጥቃት አንድ በእንቅስቃሴ ላይ የነበረን የእስራኤል ታንክ ማጋየቱን እና በውስጡ የነበሩትንም መግደሉን የሔዝቦላ አባላት ተናግረዋል።

እስራኤል ወደ ሌባኖስ ድንብር አቅራቢያ ታንኮችን አሰማርታለች።

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል ወደ ሌባኖስ ድንብር አቅራቢያ ታንኮችን አሰማርታለች።

የእስራኤል ድሮን የአየር ክልሉን ጥሶ በመግባት ሁለቱ ሃገራት በሚዋሰኑበት ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ ደን ላይ ተቀጣጣይ ነገር ጥሎ ማለፉን የሌባኖስ ጦር አስታውቋል።

የእስራኤል ጦርም በደኑ እሳት እንዲነሳ ማድረጉን አምኗል።

በኢራን የሚደገፈው ሔዝቦላ በእስራኤል ላይ ጥቃቶችን ለመፈጸም ተደጋጋሚ ዛቸዎችን ያደርጋል።

ቅዳሜ ምሽት ላይ የሔዝቦላ መሪ የሆነው ሐሰን ናስራላህ እስራኤል ላይ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ እስራኤል እራሷን ከማንኛውን አይነት ጥቃት ለመከላከል ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

እ.አ.አ. 2006 ላይ በእስራኤል እና በሔዝቦላ መካከል ለወራት በዘለቀው ጦርነት ከ1ሺህ በላይ ንጹሐን ዜጎች የተገደሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አብዛኛዎቹ የሌባኖስ ዜጎች ነበሩ።