እስራኤል በጋዛ ውስጥ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የሐማስ ኮማንደርን መግደሏን ኣሳወቀች

የሐማስ ኮማንደር ኑር ባራኬህ እናት በአስከሬን መመርመሪያ ሆስፒታል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የሐማስ ኮማንደር ኑር ባራኬህ እናት በአስከሬን መመርመሪያ ሆስፒታል

ስድስት ፍልስጥኤማውያንን ጨምሮ የሐማስ ኮማንደር እስራኤል በጋዛ ስርጥ በምታደርገው ጥቃት መገደላቸውን የፍልስጥኤም ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ልዩ ኃይልን በመጠቀም በምታደርገው የጋዛ ሰርጥ ጥቃት አንድ ወታደር እንደተገደለና የቆሰለም እንዳሉ የእስራኤል ወታደራዊ እዝ አስታውቋል።

ግጭቱ በጋዛ ደቡባዊ ክፍል ክሀን ዩኒስ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ነው የተከሰተው።

የሮኬት ማስጠንቀቂያ ድምፅም በደቡባዊ እስራኤል አካባቢ የተሰማ ሲሆን ብዜ ሮኬቶችም በጋዛ አካባቢ ተተኩሶባቸው እንደወደቁ ተገልጿል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በፓሪስ የአንደኛውን የዓለም ጦርነት ማብቂያን አስመልክቶ 100ኛ ዓመት ክብረ በዓልን እያከበሩ የነበረ ሲሆን እሁድ እለት አቋርጠው እንደተመለሱ የወጣ መግለጫ አትቷል።

የሐማስ ቃለ አቀባይ በበኩሉ ጥቃቱን የእስራኤልን " ሾላካነትና፤ ሐሞተ ቢስነት" ነው ብለውታል።

የተገደለው ኮማንደር ሼክ ኑር ባራኬህ ኢዘዲን አልቃሲም ተብሎ በሚጠራው የሐማስ ጦር ብርጌድ ውስጥ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ያለው ነው።

ሐማስ እንዳስታወቀው የእስራኤል ልዩ ኃይል በጋዛ ሰርጥ ከሚገኝ ቦታ ከመኪና ላይ ጥቃት አድርሰዋል ብለዋል።

ከዚያም በኋላ የተኩስ ልውውጥ እንደተደረገ የአይን እማኞች የገለፁ ሲሆን የእስራኤል የአውሮፕላን ጥቃትም ፍንዳታዎችን እንዳስከተለ ተዘግቧል።

የእሰራኤል ጦር በበኩሉ ስለ ጥቃቱ በመጀመሪያ ዝርዝር ነገር ከማለት ታቅበው ወታደሮቻቸው ሁሉ በሰላም እንደተመለሱ ቢያሳውቁም፤ በኋላ በሰጡት መግለጫ የልዩ ኃይሉ አንድ ባለሥልጣን እንደተገደለና አንደኛውም ቆስሏል ብለዋል።

መግለጫውም ጨምሮ ለቤተሰቦቻቸውም ተነግሯቸዋል ብለዋል።

የቢቢሲ የመካከለኛ ምስራቅ ዘጋቢ ቶም ባትማን እንደዘገበው ይህ ጥቃት የተባበሩት መንግሥታት ሁለቱን ቡድኖች ለማስማማት እየተደረገ ያለውንም ሂደት ተከትሎ ነው። በቅርብ ወራትም የእስራኤልና የሐማስ ፍጥጫ ተጋግሏል።

እስራኤል በጋዛ የምታደርገው በወታደራዊ ቡድኖች ላይ ያነጣጠረው የአየርና ሮኬት ድብደባ የተለመደ ተግባር እንደሆነም ተዘግቧል።

ከመጋቢት ወር ጀምሮ 200 የሚሆኑ ፍልስጥኤማውያን በእሥራኤል ፀጥታ ኃይሎች በጋዛ የተገደሉ ሲሆን፤ ይሄም በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልሥጥኤማውያን ስደተኞች አሁን እሥራኤል ተብላ ወደምትታወቀውና ከጥንት ጀምሮ ኃገራቸው ወደሆነችው ፍልሥጥኤም እንዲመለሱ የሚሉ ሰልፎችንም ተከትሎ ነው።