እስራኤል አፍሪካውያን ስደተኞችን ከእስር ለቀቀች

አፍሪካውያን ስደተኞች በእስራኤል ሰልፍ ሲያደርጉ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, አፍሪካውያን ስደተኞች በእስራኤል ሰልፍ ሲያደርጉ

እስራኤል 207 አፍሪካውያን ስደተኞችን ከእስር የለቀቀችው ወደ ሃገራቸው ለመመለስ የተያዘውን ቀነ ቀጠሮ ማሳካት ባለመቻሏ ነው።

የእስራኤል አሁንም ከኤርትራ እና ሱዳን የመጡ ስደተኞችን ዩጋንዳ እንድትቀበል ድርድር ላይ መሆኗ ተገልጿል።

ዩጋንዳ በበኩሏ 500 ስደተኖችን እንደምትቀበል ባለፈው አርብ አስታውቃለች።

የእስራኤሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ለጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ስደተኞቹን ወደ ሃገራው የመመለስ ስራውን ለማጠናቀቅ እስከ ፊታችን እሁድ ድረስ ጊዜ ሰጥቷቸዋል።

ይህን የማያሳኩ ከሆን ግን ባለስልጣናቱ በሳሃሮኒም እስር ቤት የሚገኙ ስደተኞችን መፍታት አለባቸው ብሏል።

የሃገሪቱ ኢሚግሬሽን ባለስልጣን ቃል አቀባይ ለኤ ኤፍ ፒ እንደተናገሩት ሁሉም ስደተኞች ለሰአታት ከቆየ ስነ ስርአት በሁዋላ ተለቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን በሃገራቸው የሚገኙ 37,000 ስደተኞችን በተመለከተ ያቀረበላቸውን የስምምነት ሃሳብ አለመቀበላቸው የሚታወስ ነው።

በስምምነቱ መሰረት 16,250 የሚሆኑ በህገወጥ መንገድ ወደ እስራኤል የገቡ አፍሪካውያን ስደተኞችን በአውሮፓ ሃገራት ጀርመን፤ ጣልያን እና ካናዳን ጨምሮ ማስጠለል ይመለከታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም እያንዳንዱ በአውሮፓ ሃገራት በሚሰፍር ስደተኛ ስም እስራኤል ሃገሯ ላሉ ስደተኞች መጠለያ ትሰጣለች ብለው ነበር። በደቡባዊ ቴል አቪቭ የሚገኙ ስደተኞችን ካነጋገሩ በኋላ ግን ሃሳባቸውን መቀየራቸውን ገልጸዋል።