የሞስኮው ፍርድ ቤት አሌክሲ ናቫልኒ ይታሰር የሚለውን ክስ እያየ ነው

አሌክሲ ናቫልኒ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሩሲያ ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠውና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆነው አሌክሲ ናቫልኒ ጉዳይ በፍርድ ቤት መታየት ጀምሯል።

አሌክሴ ናቫልኒ በሩሲያ ከተመረዘ በኋላ በርሊን ህክምናውን ተከታትሎ ወደ ሩሲያ ሲመለስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወቃል።

በአሁኑ ወቅት የሞስኮው ፍርድ ቤት እያየው ያለው በጊዜያዊነት በቁጥጥር ስር ያለው አሌክሲ ናቫልኒ ወደ እስር ይቀየር የሚለውን ጉዳይ ነው።

የተቃዋሚው እስር ከፍተኛ ተቃውሞ በሞስኮ ያስነሳ ሲሆን በዛሬው ዕለት ከፍርድ ቤት ውጭ በርካታ ፖሊሶች ተሰማርተዋል። አንዳንዶቹ ፖሊሶች በፈረስ የፍርድ ቤቱን ሁኔታ እየተቆጣጠሩ ነው ተብሏል።

በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። የሩሲያ መረጃ መቆጣጠሪያ ቡድን ባወጣው መረጃ መሰረት ፍርድ ቤቱ አካባቢ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ቁጥር 120 አድርሶታል።

የፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ ተቺ ነው የሚባለው አሌክሲ ከፍተኛ ተቃውሞ ባስነሳው ክሱ ሶስት አመት ተኩል እስር ይጠብቀዋል ተብሏል።

የ44 አመቱ ፖለቲከኛ የተከሰሰበትን የገንዘብ መመዝበርና ማጭበርበር ክስ የተፈበረከ ነው ይላል።

ህይወቱ በተአምር የተረፈችው አሌክሲ ወደ ሩሲያ በድፍረት ከሁለት ሳምንታት በፊት ሲመለስ በርካታ ሰዎች ድጋፋቸውን ለማሳየት ሰልፈው ወጥተዋል። በርካታዎቹ ደጋፊዎቹ ወጣቶች ናቸው ተብሏል።

አሌክሲ በአውሮፓውያኑ 2014 ቢከሰስም እስር አልተፈረደበትም ነበር። በየጊዜው ለፖሊስ ሪፖርት ማድረግም የክሱ በይደር ይቆይ አካል ስምምነት ነበር።

ፖሊስ ይህንን ስምምነት ጥሷል እያለ ቢሆንም ጠበቆቹ በበኩላቸው ትርጉም የሌለው ነው ይላሉ። ለዚህ እንደ ምክንያትነት የሚያቀርቡት ባለስልጣናቱ አሌክሲ በከፍተኛ የነርቭ መጎዳት በሞትና በህይወት መካከል ሆኖ በርሊን ውስጥ ህክምናውን እየተከታተለ እንደነበር ያውቃሉ ይላሉ።

ፍርድ ቤት ቀርቦ የነበረው አሌክሲ "በፅኑ ህመም ታምሜ በሰመመን ውስጥ ነበር የነበርኩት። ከሆስፒታል ስወጣ ጠበቆቼን አናግሬ የነበርኩበትን ሁኔታ የሚያስረዳ መረጃ ልኬያለሁ። እውነት ነው ቤቴ አልነበርኩም! ከዚህ በላይ ግን ምን ማድረግ እችላለሁ?" ብሏል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከሳምንት በፊት በአሌክሲ የተለቀቀ አንድ የቪዲዮ ሪፖርት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ያወጣል ተብሎ የሚገመት እጅግ ቅንጡና ግዙፍ መኖርያ ቤት ንብረትነቱ የፑቲን እንደሆነ የሚገልፅ ነበር።

ቪዲዮው በመላው ሩሲያ መነጋገርያ ከመሆኑም በላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቶ ሚሊዮን ሰዎች ተመልክተውታል፡፡ የቪዲዮውን መውጣት ተከትሎም ተቃውሞዎች ተበራክተው ነበር፡፡

የዚህ ቤተመንግሥት ቪዲዮ በሩሲያ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ትልቅ መነጋገርያ ከሆነ በኋላ ተቃውሞዎች ፈንድተው ከ4ሺ በላይ ሰዎች ታስረዋል፡፡

ከአሌክሴ ጋር ግንኙነታ አላቸው የተባሉ ሚዲያዎችና ግለሰቦች ተለቅመው የታሰሩ ሲሆን በሰብአዊ መብት ዙርያ የሚሰሩ በርካታ ድርጅቶችም ተዘግተዋል፡፡