የፑቲን እንደሆነ ሲነገር የነበረው ቤተ መንግሥት "ባለቤት ነኝ" የሚል ሰው ተገኘ

ቅንጡ ቤተ መንግሥት

የፎቶው ባለመብት, YOUTUBE/ALEXEI NAVALNY

የሩሲያ ቢሊየነር አርካዲ ሮተንበርግ በብላክ ሲ የሚገኙው ግዙፉ ቤት የኔ እንጂ የቭላድሚር ፑቲን አይደለም አሉ፡፡

ቢሊየነሩ ይህን ያሉት ይህ ግዙፍና ቅንጡ ቤት የቭላድሚር ፑቲን የግል መንደላቀቂያቸው ነው የሚል ዜና መውጣቱን ተከትሎ በሰጡት ማስተባበያ ነው፡፡

ከሳምንት በፊት በአሌክሲ ናቫልኒ የተለቀቀ አንድ የቪዲዮ ሪፖርት ይህን እጅግ ቅንጡና እጅግ ግዙፍ መኖርያ ቤት ንብረትነቱ የፑቲን እንደሆነ የሚገልጽ ነበር፡፡

ቪዲዮው በመላው ሩሲያ መነጋገርያ ከመሆኑም በላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቶ ሚሊዮን ሰዎች ተመልክተውታል፡፡ የቪዲዮውን መውጣት ተከትሎም ተቃውሞዎች ተበራክተው ነበር፡፡

ፑቲን ይህን ዘገባ ‹ተልካሻ› ሲሉ ነበር ያጣጣሉት፡፡ ቪዲዮውንም ‹በጣም ደባሪ› ሲሉ ተሳልቀውበት ነበር፡፡

ቭላድሚር ፑቲን ለእንዲህ ዓይነት ትችቶች በቀጥታ ምላሽ የመስጠት ዝንባሌ እምብዛምም የላቸውም፡፡

ሩሲያዊው ቢሊየነርና የፑቲን የቅርብ ወዳጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሮተንበርግ ትናንት ቅዳሜ ነው ወደ ሚዲያ ወጥተው ‹ቤተ መንግሥቱ የኔ ነው፤ የፑቲን አይደለም› ብለዋል፡፡

ይህ ግዙፍ መኖርያ ቤት ግንባታው በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከተጠናቀቀ በኋላ አፓርትመንት ሆቴል እንዲሆን ፍላጎት አለኝ ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ይህ የቢሊየነሩ ማስተባበያ የመጣው በሩሲያ የፕሬዝዳንት ፑቲን ተቺዎች ላይ የሚደርሰው እስርና እንግልት በተስፋፋበት ወቅት ነው፡፡

ይህ ግዙፍ ቤተ መንግሥት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያወጣ ይገመታል፡፡

የዚህ ቤተመንግሥት ቪዲዮ በሩሲያ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ትልቅ መነጋገርያ ከሆነ በኋላ ተቃውሞዎች ፈንድተው ከ4ሺ በላይ ሰዎች ታስረዋል፡፡

የብዙዎቹ ሰልፈኞች ጥያቄ ተመርዞ በተአምር ሕይወቱ የተረፈችው የፑቲን ተቺ አሌክሴ ከእስር እንዲፈታ የሚጠይቁ ነበሩ፡፡

አሌክሴ ናቫልሪል በሩሲያ ከተመረዘ በኋላ በርሊን ሕክምና ተደርጎለት ወደ ሩሲያ በድፍረት ሲመለስ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ይታወሳል፡፡

ከአሌክሴ ጋር ግንኙነታ አላቸው የተባሉ ሚዲያዎችና ግለሰቦች ተለቅመው የታሰሩ ሲሆን በሰብአዊ መብት ዙርያ የሚሰሩ በርካታ ድርጅቶችም ተዘግተዋል፡፡

በሩሲያ ዛሬ እሑድም ተቃውሞ ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ቢሊየነሩ አርካዴ ሮተንበርግ በሩሲያ እውቅ ሲሆን የፑቲን ቀኝ እጅ እንደሆነም ይነገርለታል፡፡

ቢሊየነሩ በተለይ ድልድይና የጋዝ ቧንቧ መስመሮችን በመገንባት የሚታወቅ ግዙፍ ተቋራጭ ኩባንያ ባለቤት ነው፡፡

ሮተንበርግ የቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ወዳጅ ብቻም ሳይሆን አብሮ አደግ ናቸው፡፡ በልጅነታቸውም ጁዶ ስፖርት አብረው ይጫወቱ ነበር ተብሏል፡፡

ቢሊየነሩ አሜሪካ 2014 በሩሲያ ባለሃብቶች ላይ በጣለችው ማእቀብ ስሙ የተካተተ ሰው ነው፡፡

ተቺዎች ይህ ቢሊየነር ‹ቤተ መንግሥቱ የኔ እንጂ የፑቲን አይደለም› እንዲል የተደረገው በራሳቸው በፑቲን ትእዛዝ ሊሆን ይችላል ብለው ይጠረጥራሉ፡፡