አሜሪካ ፡ በዛሬው የጆ ባይደን በዓለ ሲመት ላይ ምን ሊከሰት ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ምርጫ ተመዞ አያልቅም። ወገብ ይቆርጣል።
ይህን ምርጫ ተከትሎ የሚመጣው ፕሬዝዳንት ታዲያ ደማቅ አቀባበል ቢደረግለት ቢያንስ እንጂ አይበዛበትም።
አሜሪካ አዲስ ፕሬዝዳንቶቿን ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት የምታስገባበት የራሷ ወግና ሥርዓት አላት።
ዘንድሮ ግን በኮቪድ-19 እና በነውጠኞቹ የትራምፕ ደጋፊዎች ምክንያት በታሪክ ደብዛዛው በዓለ ሲመት ነው የሚሆነው ተብሏል።
46ኛው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዚህ ረገድ ዕድለኛ አይደሉም።
ለማንኛውም ስለዚህ ሥነ ሥርዓት የሚከተሉትን ነጥቦች ማወቁ አይከፋም።
ፕሬዝዳንታዊ በዓለ ሲመት ምንድነው?
የበዓለ ሲመቱ መደበኛ ቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓቱ የሚካሄደው የፌዴራል መንግሥት መቀመጫ በሆነችው በዋሺንግተን ዲሲ ነው።
ዕለቱ የፕሬዝዳንቱ ይፋዊ የሥራ መጀመሪያ ቀን ተደርጎ ይታሰባል።
በዚህ ቀን ፕሬዝዳንቱ ቃለ መሐላ ይፈጽማል።
ቃለ መሐላው ይዘቱ የሚከተለው ነው፡-
"በሐቅና በታማኝነት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆኜ ለማገልገል ቃል እገባለሁ፤ ባለኝ አቅም ሁሉ፣ የአሜሪካንን ሕገ መንግሥት ለመጠበቅ፣ ለማክበርና ለማስከበር እተጋለሁ!"
ልክ ይህን ቃል መሐላ እንደፈጸሙ ነው ጆ ባይደን 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳት መሆናቸው በይፋ የሚበሰረው። ሥነ ሥርዓቱ በዚሁ ያበቃል። ፈንጠዚያው ግን ይቀጥላል።
ምክትል ካመላ ሐሪስም በዚሁ ዕለት ነው ቃል መሐላ የሚፈጽሙት ብዙውን ጊዜ ፕሬዝዳንቱ ቃለ መሐላ ከመፈጸማቸው በፊት ምክትላቸው ይህንኑ እንዲያደርጉ ይደረጋል።
መቼ ነው በዓለ ሲመቱ?
ዛሬ ረቡዕ ነው ኩነቱ ሁሉ የሚከወነው።
በሕግ የአሜሪካ ፕሬዝዳታዊ በዓለ ሲመት በጃንዋሪ 20 (ጥር 12) ነው የሚሆነው።
ሥነ ሥርዓቱ ብዙውን ጊዜ በዋሺግተን ሰዓት ከረፋዱ 5፡30 ነው የሚጀመረው። እኩለ ቀን ላይ ባይደንና ሐሪስ ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ።
ጆ ባይደን ያንኑ ቀን ከሰዓት በኋላ [ማለትም ወደ 9 ሰዓት ግድም] ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት ይገባሉ።
ይሄ ቤት ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የጆ ባይደን መኖሪያም መሥሪያ ቤትም ይሆናል። ዕድሜ ከሰጣቸው።
የቤቱን ጠቅላላ መንፈስ ከትራምፕ ፖለቲካና ግለሰባዊ ጠረን ለየት ለማድረግ መጠነኛ እድሳትና የዲዛይን ለውጥ አይደረግም አይባልም።
አንድ ፕሬዝዳንት ጨርሶ ሌላው ሲገባ ይህን ማድረግ የተለመደ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ረብሻ ሊቀሰቀስ ይችላል?
ወትሮም ይህ በዓለ ሲመት በየአራት ዓመቱ በመጣ ቁጥር ብዙ የደኅንነት ከለላና ጥበቃ አይለየውም። በግላጭም በኅቡዕም።
ምክንያቱ ደግሞ በርካታ ሕዝብ የሚገኝበት ኩነት ስለሆነ ነው።
ከሕዝብም እጅግ ቁልፍ የሚባሉ ኃያላን ባለሥልጣናት የሚገኙበት ነው። ለጠላትም ጥቃት ለመፈጸም ምቹ ጊዜና ቦታ መሆኑም ይታወቃል።
የዘንድሮ ደግሞ ከዚህም በላይ ጥበቃ የሚሻ ሆኗል።
የትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎች አደጋ ለመጣል ስለዛቱና ይህም በፌዴራል የምርመራ ቢሮ ስለተደረሰበት 15 ሺህ የአሜሪካ ብሔራዊ ጥበቃ ወታደሮች እዚያም እዚህም ተሰማርተዋል።
እነዚህ የጸጥታ አባላት ለዋሺንግተን ዲሲና አካባቢው ብቻ የተመደቡ ናቸው። ልብ አድርጉ፣ ዋሺንግተን ዲሲ አሁንም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ናት።
ይህን የጸጥታ ጥበቃ 'ሲክሬት ሰርቪስን' [ምስጢራዊው የደኅንነት አገልግሎት] ተክተው የሚመሩት ማት ሚለር፣ ለዛሬው ቀን ጸጥታ ከአንድ ዓመት በላይ ዝግጅት እንደተደረገ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶናልድ ትራምፕ ይገኛሉ?
እርግጥ ነው አንድ ፕሬዝዳንት ሲሸነፍም ሆነ የተገደበውን የሥልጣን ዘመኑን ሲጨርስ ለቀጣዩ ፕሬዝዳንት ሥልጣኑን በይፋ የሚያስረክበው በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ነው።
ትራምፕ ግን ለደንብና ሥርዓት የሚገዙ ሰው አይደሉም።
ትራምፕ በበዓለ ሲመቱ ላይ ተገኝተው ዓለምን ያስገርማሉ ሲባል ነበር በአንዳንድ ሚዲያዎች።
ከሁለት ሳምነት በፊት ገደማ ግን ለሕዝባቸው ቁርጡን ተናግረዋል። በትዊተር በጻፉት አጭር ጽሑፍ እንዲህ በማለት፡-
"ትመጣለህ ወይ እያላችሁ ለምትጠይቁኝ ሁሉ! አልመጣም።"
በዚህ ዕለት ትራምፕ የት ይሄዱ ይሆን? ምናልባት ከጎልፍ መጫወቻ መስኮቻቸው በአንዱ ውስኪ ይዘው ይሸጎጡ ይሆን?
በምርጫ የተሸነፉ ቀን ጎልፍ ላይ ነበሩ።
ደጋፊዎቻቸው ግን አሁንም "መሄድክን አላምንም" እያሏቸው ነው።
ለዚህም ያሸነፉት ትራምፕ ናቸው ብለው ከልባቸው ስለሚያምኑ በኦንላይን [በኢንተርኔት] የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት አዘጋጅተናል ብለዋል።
70 ሺህ ሰዎች በዚህ ሐሳዊ የትራምፕ የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት ላይ ለብሰን አጊጠን እንገኛለን ብለዋል።
ትራምፕ የዛሬ 4 ዓመት ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ ተሸናፊዋ ሒላሪ ከባለቤታቸው ቢል ክሊንተን ጋር ተገኝተው ነበር። ከዚያ ሁሉ እልህ አስጨራሽ ክርክርና የሚያስቆጭ ሽንፈት በኋላ ነው የተገኙት።
ደግሞም ያኔ ብዙ ሰው የመረጠው ሒላሪን እንጂ ትራምፕን አልነበረም። በግዛት ውክልና ቆጠራ አሰራር ነው ለሽኝት የተዳረጉት። ቢሆንም ሒላሪ ሽንፈታቸውን ዋጥ አድርገው ፈገግ ብለው ሥነ ሥርዓቱን ታድመዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ግን የዲሞክራቶችን ውለታ የሚመልሱ አይደሉም።
ከዚህ በፊት በአሜሪካ ታሪክ 3 ፕሬዝዳንቶች ብቻ በተቀናቃኛቸው በዓለ ሲመት ላይ ሳይገኙ ቀርተዋል።
እነሱም ጆን አዳምስ፣ ጆን ኩንሲ አዳምስ እና አንድሩ ጆንሰን ናቸው። ሆኖም ባለፈው መቶ ዓመት ይህ ሆኖ አያውቅም። ትራምፕ ናቸው የመጀመርያው ሰው።
ማይክ ፔንስ ግን የጆ ባይደንን በዓለ ሲመት እታደማለሁ ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምን ያህል ሕዝብ ይገኛል?
ከዚህ ቀደም ሚሊዮነች ይጎርፉ ነበር። ለምሳሌ ባራክ ኦባማ በ2009 ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ 2 ሚሊዮን ሕዝብ ዲሲን አጨናንቋት ነበር።
ሆቴል አልጋ የሚባል ጠፍቶ፣ ጎዳናዎች በሕዝብ ተሞልተው፣ እንደው ነገሩ ሁሉ ትልቅ ብሔራዊ በዓል ነበር የሚመስለው። የሥነ ሥርዓቱ ታዳሚ በሚሰባሰብበት በናሽናል ሞል ሰፊ መስክ ላይ ጠጠር ቢጣል መሬት አይወድቅም ነበር።
ዘንድሮ ግን ኮቪድና የትራምፕ ደጋፊዎች ነገሩን አደብዝዘውታል። ሥነ ሥርዓቱ ላይ በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ነው የሚገኙት።
ጆ ባይደንም "አሜሪካዊያን እኔን ብላችሁ ወደ ዲሲ ድርሽ እንዳትሉ" ብለዋል።
እሳቸው ጤናን የሚያስቀድሙ ጤነኛ መሪ ናቸው እያሉ አሞግሰዋቸዋል፣ አንዳንዶች።
ሆኖም ሐሪስና ባይደን እንደተለመደው ከካፒቶል ሒል ፊት ለፊት ባለው ቦታ ነው ቃለ መሐላ የሚፈጽሙት። እንጂ አዳራሽ ተቆልፎባቸው አይደለም ሥርዓቱን የሚታደሙት።
ሁለት መቶ የሚሆኑ ሰዎች ተራርቀው መድረክ ላይ ይቀመጣሉ ተብሏል።
በቦታው የሚገኙት ሰዎች በሙሉ ከሳምንት ጀምሮ በየሁለት ቀኑ የኮቪድ-19 ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሁሉም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማጥለቅ አለባቸው።
ባይደንም ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ ብቻ ጭምብላቸውን ያወልቃሉ።
ከዚህ ቀደም ይህን ልዩ በዓለ ሲመት ለመታደም ሁለት መቶ ሺህ የግብዣ መጥሪያዎች ታድለው ያልቁ ነበር።
ዘንድሮ ግን 1ሺህ የግብዣ ካርዶች ብቻ ናቸው የተዘጋጁት።
ሥነ ሥርዓቱ ካለቀ በኋላ ጆ ባይደን ከሚስታቸው ጋር፣ ካመላ ሐሪስ ደግሞ ከባላቸው ጋር በወታደራዊ አጀብና በልዩ የማርሽ ሙዚቃ ታጅበው ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት ይወሰዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የግብዣ ካርዱ የት ይገኛል?
ከዚህ በፊት በነበረው ሥርዓት ከፊት መቀመጫ ለማግኘት ወይም በቅርብ ቆሞ ለማየት የግብዣ ካርድ መያዝ የግድ ነበር። የተቀረው የናሽናል ሞል ቦታ ግን ለሕዝብ ክፍት ነው የሚሆነው።
ስለዚህ አንድ ሰው ይህን ሥነ ሥርዓት በቅርብ ተገኝቶ ለመከታተል የግብዣ ካርዱን ከአካባቢው አስተዳዳሪዎች ማግኘት ይኖርበታል።
ከዚህ የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት በኋላ ለሚኖሩ የፈንጠዚያ መርሐ ግብሮች የግብዣ ካርዶች የሚገኙት ከአዘጋጆቹ ነው። የሕግ መምሪያውና የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት በርከት ያሉ የግብዣ ካርድ ይታደላቸዋል። እነሱ ለፈለጉት ሰው ካርዱን ያድላሉ።
ሌዲ ጋጋ ትዘፍናለች?
በቅርብ ዓመታት በዚህ በዓለ ሲመት እውቅ ሙዚቀኞች እንዲያቀነቅኑ ይጋበዛሉ። ዘንድሮም ይህ ነገር አልቀረም ተብሏል።
የጆ ባይደንና የሐሪስ ደጋፊ እንደሆነች የሚነገርላት ሌዲ ጋጋ ዕለቱን በደማቅና ወጣ ባለ አለባበሷና በውብ ሙዚቃዎቿ ታደምቀዋለች ተብሎ ይጠበቃል።
ጄኔፈር ሎፔዝም ታዜማለች ተብሎ መድረክ ተሰናድቶላታል።
በባራክ ኦባማ ሲመተ በዓል ላይ ያቀነቀኑ ታዋቂ ድምጻዊያን መካከል ታላቅ ክብር የሚሰጣት አሪታ ፍራንክሊን እና ቢዮንሴ ነበሩ። ኦባማ እምባ እየተናነቃቸው ለአሪታ ፍራንክሊን ቆመው አጨብጭበዋል።
በኦባማ ጊዜ ጭንቀቱ የትኛው ዘፋኝ ዕድሉን ያግኝ የሚል ነበር። ምክንያቱም ለእሳቸው ሁሉም መዝፈን ይፈልግ ነበርና።
የዛሬ 4 ዓመት ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ የበዓለ ሲመታቸውን መድረክ የሚያደምቅላቸው ዘፋኝ ለማግኘት ብዙ ለፍተዋል። በደላላ ሁሉ ማግባባት ይዘው ነበር። ከየት ይምጣ?
ሰር ኤልተን ጆን እንዲዘፍን ትራምፕ ጠይቀውት "ይለፈኝ" ብሏቸው ነበር። ሴሊን ዲዮንም እንዲሁ ትራምፕ ጠይቀዋት "እምቢኝ" ብላ ነበር ብለዋል ውስጥ አዋቂዎች።
የትራምፕን ከነጩ ቤተ መንግሥት መሰናበት እንደ እፎይታ የሚቆጥሩ ዘፋኞች ኮቪድ-19 አቆማቸው እንጂ የባይደንን በዓለ ሲመት በአያሌው ባደመቁላቸው ነበር። ለዚያውም በደስታ!
ምናልባት የዛሬ 4 ዓመት ኮቪድ-19ኝም ባይደንም ታሪክ ይሆኑ ይሆናል። ወይም ደግሞ አይሆኑ ይሆናል። ማን ያውቃል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images















