ቤንሻንጉል ጉሙዝ፡ በማክሰኞ ዕለት በመተከል ዞን ከ80 በላይ ሰዎች ተገድለዋል - ኢሰመኮ

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በማክሰኞ ጥር 4/ 2013 ዓ.ም ከ80 ሰዎች በላይ መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለቢቢሲ አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ከፍተኛ አማካሪ እና ቃል አቀባይ አቶ አሮን ማሾ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጥቃቱ የደረሰው በመተከል ዞን፣ በደባጤ ወረዳ፣ ዳለቲ በምትባል ከተማ ነው።

ኮሚሽኑ በደረሰው መረጃ መሰረት ህይወታቸው የተቀጠፈው ከ80 በላይ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ2 እስከ 45 ነው።

በአካባቢው ተደጋጋሚ ጥቃቶችና ግድያዎች መድረሱን ያስታወሱት አቶ አሮን በፌደራልና በክልሉ መንግሥት የተቀናጀ እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት እየፈፀመ ባለው ቡድን ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን በዞኑ የተቋቋመው ግብረ ኃይል አስታውቋል።

ግብረ ኃይሉ እየወሰድኩት ነው ባለው እርምጃ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የመንግሥት አመራሮችን ጨምሮ በርካታ የቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኢዜአ በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በሚደርሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች አሁንም የሰዎች ህይወት እየጠፋ መሆኑን ነዋሪዎች ገልፀዋል።

በጉዳዩ ላይ ቢቢሲ ምላሻቸውን የጠየቃቸው የክልሉ የኮምዩኒኬኬሽን ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት የሚችለው የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ነው በሚል ከመናገር ተቆጥበዋል።

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የማንዱራ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደገለጹት "አካባቢው ተረጋግቷል መባሉ እውነት አይደለም" ሲሉ ገልጸዋል።

"የፖለቲካ ጨዋታ አይደለም መሆን ያለበት እውነቱ መነገር አለበት" የሚሉት ነዋሪው በተለያዩ አካባቢዎች በሚደርስ ጥቃት የሰዎች ህይወት አሁንም እያለፈ መሆኑን ጠቁመዋል።

"ትላናንት በስተያ [ሰኞ] እንኳን የመተከል ዞን አንድ ወረዳ በሆነችው ዳንጉር [ቀደም ሲል የጤና ባለሙያዎች የታፈኑበት አካባቢ] ማታ ላይ ሰው ተገድሏል። ከቻግኒ ወደ ከግልገል በለስ በሚሄድ ሕዝብ ማመላለሻ ላይ ጥቃት ተፈጽሞ አንድ ሰው ሞቶ ሦስት ቆስለዋል።

"ማከስኞ ጠዋትም ወደ ግለግል በለስ በሚሄድ መኪና ኤዲዳ ወይንም ቁጥር 2 በምትባል ቦታ ላይ አንድ ሰው ተገድሏል፤ ሁለት ቆስለው አሁን ህክምና ላይ ነው ያሉት። በድባጤ ወረዳ ዳለቲ ቀበሌ ላይ አንድ ሰው ተገድሏል። ቤቶች እየተቃጠሉ ነው። የደረሰ አካልም የለም። የጸጥታ ችግር አለ ለማለት በአንድ ቀን 200 ወይም 300 ሰው መጨፍጨፍ አለበት?" ሲሉ ተናግረዋል።

ሰኞ ዕለት በጉባ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 15 መድረሱን ቢቢሲ ከነዋሪዎች የሰማ ሲሆን የአካባቢው ኃላፊዎች ለማረጋገጥም ሆነ ለማስተባበል ፈቃደኛ አልሆኑንመ።

ጥቃት የሚፈጸመው በተለዩ ነዋሪዎች ላይ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸው "ቀደም ሲል ማንነትን መሠረት አድርጎ የነበረ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቀይ የሚባል ሺናሻ ይሁን ኦሮሞ፣ አገው ይሁን አማራ ይሁን ትግሬ እየተለየ የጥቃት ኢላማ ይሆናል" ሲል ገልጸዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ያለውን ግድያ እና ንብረት ውድመት ሲመለከቱም አካባቢው ተረጋግቷል የሚባለውን ትክክል እንዳልሆነ ሌላ በአካባቢው በስጋት ውስጥ ያሉ ነዋሪ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አሁን በአካባቢው ኅብረተሰብ ተመርጠው በኃላፊነት ላይ ያሉ አመራሮች ከችግሩ ጀርባ ያሉ ናቸው ብለው የሚያምኑት ነዋሪ "በድጋሚ ተጎጂዎችንም አካቶ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር በመሆን ጊዜያዊ አስተዳደር እየተመሰረተ ካልሄደና ጥቃት አድራሾችን ላይ ተገቢ እርምጃ ካልተወሰደ ጥቃቱ እየቀጠለ ሊሄድ ይችላል" ሚል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።

ሌላ የአካባቢው ነዋሪም ትላንት መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አይሚሽሚሽ ቀበሌ ጥቃት መፈጸሙን ገልጸው፤ በጥቃቱ እናቱ ያዘለችውን ህጻን ጨምሮ 11 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ትላንት ሰኞ ጠዋት በግምት 12፡30 አካባቢ ነው ጥቃቱ ተፈጸመው። እኔ አልመሃል ነው ያለሁትና ወዲያው ወደ እኛ ተደወለ። ለመከላከያ ተናግረን በማስተባበር አስከሬናቸው ተነስቷል። ማታ ላይ አልመሃል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ነው የተቀበሩት" ሲሉ አስረድተዋል።

ቤቶች እና የተለያዩ ንብረቶች መቃጠላቸውንም አስታውቀው ጥቃት አድራሾቹ "የሚያስፈልጋቸውን ንብረት በአህያ ጭነው ሄደዋል" ሲሉ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ከጥቃቱ ጀርባ አሉ ያሏቸውን ሰዎች ለሕግ አካላት ቢያሳውቁም ከእስር እየተፈቱ መሆኑንና ጥቃቱን በመምራት ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

አካባቢው ስላለበት ሁኔታ ተጠይቀውም "አልመሃል ላይ መከላከያም ፌደራልም አለ። በፊትም ደህና ነበር። አልመሃል ሠላም ነው ባይባልም ድባቡ ጥሩ አይደለም። . . . በእርሻ ኢንቨስትመንት ጥጥ ለቀማ ላይ የነበሩ ሠራተኞች እንዳሉ እየወጡ ነው። ይቅርብን አንሠራም አውጡን እያሉ ከባለሃብቶች ጋር ግብ ግብ እየፈጠሩ ወደ አልመሃል እየገቡ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ሰሞኑን ስለተፈጸሙት ጥቃቶች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የክልሉን የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ መለሰ በየነን ለማናገር ቢሞክርም እሳቸው በአሁኑ ጊዜ መግለጫ እንደማይሰጡና ጉዳዩን ከሚከታተለው ኮምንድ ፖስት እንድንጠይቅ በሰጡን ምላሽ፤ የኮምንድ ፖስቱ አባል የሆኑት አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ጋር በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ጥሪያችን ስለማይነሳ ሐሳባቸውን ለጊዜው ማካተት አልቻልንም።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለወራት የዘለቀ ተከታታይ ጥቃት በነዋሪዎች ላይ ሲፈጸምበት በቆየበት የመተከል ዞን ውስጥ በሚገኘው ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ታኅሣስ 13/2013 ዓ.ም በታጣቂዎች በተጸፈመ ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

በመተከል ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በታጣቂዎች የሚፈፀመውን ግድያ ለማስቀረት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የዞኑን የፀጥታና የሕግ ማስከበር ሥራ ተረክቦ እየሰራ መሀኑ ይታወቃል።

ይህ ግብረ ኃይል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሰልጣናትን፣ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችን ያቀፈ ሲሆን በመተከል ዞን የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንደተሰጠው ተነግሯል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ታኅሣስ 13/2013 ዓ.ም በመተከል ዞን ከተፈጸመው የበርካታ ሰዎች ግድያ ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት የተባሉ አራት የምክር ቤቱ አባላትን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ይታወሳል።

የቤንሻንጉል ክልል ምክር ቤት በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ የነበሩትንና የምክር ቤት አባል ከነበሩት መካከል የአቶ አድጎ አምሳያ፣ አቶ ሽፈራው ጨሊቦ፣ አቶ ግርማ መኒ እና አቶ አረጋ ባልቢድ ያለመከሰስ መብትን ነው ያነሳው።

የአራቱ የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት በተነሳበት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታደለ ተረፈ በመተከል ዞን የተፈጸመው ጥቃት አሳዛኝና ሊደገም የማይገባው መሆኑን መናገራቸውን የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ገልጾ ነበር።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ካለፈው ዓመት ጳጉሜ ወር አንስቶ በንፁሃን ዜጎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈፀም የቆ ሲሆን በዚህም የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቀያቸውን ጥለው ሲሰደዱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።