ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፡ በመተከል ዞን በተፈፀመው ግድያ ተጠረጥረው የተያዙ የክልሉ ባለሥልጣናት ቁጥር ዘጠኝ ደረሰ
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ባለፈው ሳምንት በተፈፀመው ግድያ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ የክልልና የዞን አመራሮች ቁጥር ዘጠኝ ደረሰ።
እነዚህ የመንግሥት ባለሥልጣናት ታኅሣስ 13/2013 ዓ.ም በኩጂ ቀበሌ በደረሰው ጥቃት ወቅት የተሰጣቸውን የመንግሥት ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣት እንዲሁም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ ናቸው በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ዛሬ [ማክሰኞ] ጠዋት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት በመተከል ዞን ከተፈጸመው የበርካታ ሰዎች ግድያ ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት የተባሉ አራት የምክር ቤቱ አባላትን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ይታወቃል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ለቢቢሲ በተጨማሪም አንድ የፀረ ሽምቅ አባል በኩጂ ቀበሌ በተፈፀመው ግድያ ላይ እጁ አለበት በሚል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ተናግረዋል።
አክለውም የመተከል ዞን አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ አትንኩት ዛሬ ረፋድ 3፡00 ላይ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልፀዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለወራት የዘለቀ ተከታታይ ጥቃት በነዋሪዎች ላይ ሲፈጸምበት በቆየው የመተከል ዞን ውስጥ በሚገኘው ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ታኅሣስ 13/2013 ዓ. ም ንጋት ላይ በታጣቂዎች በተጸፈመ ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
አቶ መለስ አክለውም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የመተከል ዞንን የፀጥታ ማስከበር ሥራን መረከቡን ተናግረዋል።
ይህ ግብረ ኃይል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሰልጣናትን፣ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችን ያቀፈ ሲሆን በመተከል ዞን የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንደተሰጠው ተነግሯል።
አቶ መለስ፣ በአሁኑ ሰዓት ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ግብረ ኃይሉ በዞኑ በንፁሃን ላይ ጥቃት በመፈጸም፣ ህይወት በማጥፋት ወንጀል የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን በማደን ላይ መሆኑ በመግለጽ፣ በወንጀሉ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አውሎ በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በዞኑ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ጥቃቶችን ለመከላከል በተወሰደ እርምጃም ከ300 በላይ ታጣቂዎች መገደላቸውን፣ በውጊያውም ሂደት ከ200 በላይ የጦር መሳሪያዎች መማረካቸውን ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል።
በተጨማሪም በተፈጸመው ጥቃት ውስጥ ተሳታፊ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ከ60 በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አብራርተዋል።
በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ታኅሣስ 13/2013 ዓ.ም ንጋት ላይ በታጣቂዎች በተጸፈመ ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 207 መድረሱን የአካባቢው ባለስልጣናትና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቀው ነበር።
በጥቃቱ ከተገደሉት 207 ሰዎች መካከል የ171ዱ ሥርዓተ ቀብር በጅምላ ታኅሣስ 15/2013 ዓ.ም ተፈጽሟል።
ኮሚሽኑ የተፈፀመውን የጅምላ ግድያ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ላይ ከሟቾቹ መካከል አዋቂዎቹ 133 ወንዶችና 35 ሴቶች ሲሆኑ፤ አንድ የስድስት ወር ሕጻንን ጨምሮ 17 ሕጻናት፣ የቀሩት 20 ሰዎች ደግሞ አዛውንቶች ናቸው ብሎ ነበር።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ካለፈው ዓመት ጳጉሜ ወር አንስቶ በንፁሃን ዜጎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈፀም ነበር።
በዚህም የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቀያቸውን ጥለው ሲሰደዱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።