ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ አራት የምክር ቤት አባላቱን ያለመከሰስ መብት አነሳ
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት በመተከል ዞን ከተፈጸመው የበርካታ ሰዎች ግድያ ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት የተባሉ አራት የምክር ቤቱ አባላትን ያለመከሰስ መብት አነሳ።
የክልሉ ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ጥያቄ የቀረበባቸው አቶ አድጎ አምሳያ፣ አቶ ሽፈራው ጨሊቦ፣ አቶ ግርማ መኒ እና አቶ አረጋ ባልቢድ ናቸው።
አቶ አድጎ አምሳያ ቀደም ሲል የክልሉ ገዢ ፓርቲ ሊቀመንበርና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩ ሲሆን፣ አቶ ሽፈራው ጨሊቦ የክልሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር በመሆን በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የነበሩ ናቸው።
በተጨማሪም አቶ አረጋ ባልቢድ የመተከል ዞን አመራር የነበሩና አቶ ግርማ መኒ የክልሉ ምክር ቤት አባል ሲሆኑ አራቱ ሰዎች በክልሉ የመተከል ዞን በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ ምክር ቤቱ በአባልነታቸው ያላቸውን ያመከሰስ መብት እንዲነሳ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
የአራቱ የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት በተነሳበት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታደለ ተረፈ በመተከል ዞን የተፈጸመው ጥቃት አሳዛኝና ሊደገም የማይገባው መሆኑን መናገራቸውን የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ገልጿል።
አራቱ ግለሰቦች ባለፈው ሳምንት ከተፈጸመው አሰቃቂ ጥቃት በኋላ በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የክልሉ ምክር ቤት አባል በመሆናቸው የሚኖራቸው ያለመከሰስ መብት በቀዳሚነት መነሳት አስፈላጊ በመሆኑ ነው ምክር ቤቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው።
ቀደም ሲል ከዚሁ መተከል ዞን ውስጥ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ሰዎች መካከል በክልሉና በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ በሚገኙ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የነበሩ ይገኙበታል። በዚህም የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ የነበሩት አቶ ቶማስ ኩዊ አንዱ ናቸው።
በተጨማሪም አቶ ባንዲንግ ማራ የመተከል ዞን የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ አቶ ገመቹ አመንቲ የክልሉ የግዢና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም አቶ አድማሱ መልካ የገጠር መንገድና ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል ይገኙበታል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለወራት የዘለቀ ተከታታይ ጥቃት በነዋሪዎች ላይ ሲፈጸምበት በቆየው የመተከል ዞን ውስጥ በሚገኘው ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ታኅሳስ 13/2013 ዓ. ም ንጋት ላይ በታጣቂዎች በተጸፈመ ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም የጸጥታ ኃይሎች ባካሄዱት አሰሳ ከአርባ በላይ ታጣቂዎች መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን በጭፍጨፋው ውስጥ በተለያየ መልኩ እጃቸው አለበት የተባሉ የመንግሥት ባለሰልጣናትም በቁጥጥር ሰር ውለዋል።
ከጥቃቱ በኋላ የአካባቢውን ጸጥታ የሚቆጣጠር ግብረ ኃይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተቋቋመ ሲሆን ግብረ ኃይሉም ሥራውን በዚህ ሳምንት መጀመሩ ተገልጿል።
ይህ ግብረ ኃይል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሰልጣናትና የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችን ያቀፈ ሲሆን በመተከል ዞን የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንደተሰጠው ተነግሯ።
ግብረ ኃይሉ በሌፍተናንት ጄኔራል አስራት ዴኔሮ የሚመራና በዞኑ በንፁሃን ላይ ጥቃት በመፈጸም ህይወት በማጥፋት ወንጀል የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን በማደን ላይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በወንጀሉ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሰር አውሎ በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ተገልጿል።