ቤንሻንጉል ጉሙዝ፡ በመተከል ዞን ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ200 በላይ ሆነ

በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ታኅሳስ 13/2013 ዓ. ም ንጋት ላይ በታጣቂዎች በተጸፈመ ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 207 መድረሱን አንድ የአካባቢው ባለስልጣን ለቢቢሲ አረጋገጡ።

በጥቃት ፈጻሚዎቹ በሰዓት ውስጥ በተፈጸመው ጭፍጨፋ በቀበሌው ውስጥ ነዋሪ ከሆኑት ሰዎች መካከል 207ቱ በጥቃቱ መገደላቸውንና 171ዱ ሥርዓተ ቀብራቸው ሐሙስ መፈፀሙን የቡለን ወረዳ ኮሙኑኬሽን ኃላፊ አቶ ካሳሁን አዲሱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም በአካባቢው ከሚገኙ ነዋሪዎች፣ ከበጎ ፈቃድ ድጋፍ ሰጪዎችና ከጸጥታ አካላት በማጣራት ባገኘው መረጃ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 207 መድረሱን እንዳረጋገጠ አሳውቋል።

ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ላይ በጥቃቱ ስለተገደሉት ዝርዝር እንዳመለከተው ከሟቾቹ መካከል አዋቂዎቹ 133 ወንዶችና 35 ሴቶች ሲሆኑ፤ አንድ የስድስት ወር ሕጻንን ጨምሮ 17 ሕጻናት ተገድለዋል። የቀሩት 20 ሰዎች ደግሞ አዛውንቶች መሆናቸው ኢሰመኮ አረጋግጧል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎችና የአካባቢው ኃላፊዎች የሟቾቹ ቁጥር ከ207 በላይ ሊሆን እንደሚችል ስጋት እንዳለቸው ገልጸዋል።

ኢሰመኮ በመግለጫው ላይ እንዳለው ፖሊስ እና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ጨምሮ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ አካላት የተወጣጡ አባላት ያሉበት የምርመራ ኮሚቴ የሟቾቹን ማንነት የማጣራቱን፣ የመመዝገብና አስከሬኖችን የመቅበር ተግባራትን እየተከታተለ ይገኛል።

የወረዳው ኮሙኒኬሽን ኃላፊው አቶ ካሳሁን ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት በተፈጸመው የጅምላ ጥቃት የተገደሉት የሦስት የተለያዩ እምነት ተከታዮች ቢሆኑም ለይቶ የተናጠል ቀብር ለማካሄድ አስቸጋሪ በመሆኑ ሐሙስ ዕለት በጅምላ እንዲቀበሩ መወሰኑን አስረድተዋል።

በርካታ አስከሬኖች የሚያሳዩና ለጅምላ ቀብር የተዘጋጁ የቀብር ቦታዎችን የሚያሳዩ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ሲዘዋወሩ ታይተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሟቾቹ ቁጥር ከፍ ማለቱንና በአካባቢው ስላለው ሁኔታ በገለጸበት መግለጫው ላይ የሟቾችን አያያዝ በተመለከተም "የአስከሬን ፍለጋና የመቅበር ሥነ ሥርዓቱ ሰብአዊ ክብርን በጠበቀ መልኩ እንዲሆን" ጥሪ አቅርቧል።

ጥቃቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና አምንስቲ ኢንተርናሽናል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን ማክሰኞ ሌሊት ለረቡዕ አጥቢያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ገልፀው ነበር።

የክልሉ ኮሙኑኬሽን ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ በወቅቱ ለቢቢሲ በጥቃቱ በትክክል ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ ለመግለጽ ባይችሉም ቁጥሩ "በጣም ከፍተኛ" ነው ብለው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድም ይህንን ጥቃት "ጭፍጨፋ" መሆኑን ገልጸው "በወገኖቻችን ላይ በተፈጸመው ኢሰብአዊ ተግባር በእጅጉ አዝኛለሁ" በማለት ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ታኅሣስ 14/2013 ባወጣው መግለጫ በበኩጂ ቀበሌ የሚኖሩ የሽናሻ፣ የኦሮሞ እና የአማራ ብሔረሰብ ተወላጆች በጥቃቱ ዒላማ ተደርገዋል ብሏል።

ይህ ጥቃት በቤኒሻንጉል ክልል ውስጥ ያለው የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዳከመ መሄዱን እንደሚያሳይም ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።

የአምንስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገደሉትን ሰዎች አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ "እጅግ አሰቃቂው ግድያ በክልሉ የሚኖሩ አማራዎች፣ ኦሮሞዎችና ሺናሻዎች ላይ ያነጣጠረ ነው። ይህ መንግሥት ብሔር ተኮር የሆነ ግድያን ለማስቆም በፍጥነት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ የሚያሳይ ነው" ማለቱ ይታወሳል።

አቶ ካሳሁን አዲሱ እንደገለፁትም በአካባቢው የደረሰውን ጥቃት ለማጣራት የተሰማራው የመከላከያ፣ የክልል እና የመገናኛ ብዙሃን ቡድን ከወረዳ እና ከዞን ኃላፊዎች ጋር ሆኖ ባደረገው ማጣራት የተገደሉት 207 ሰዎች ከአማራ፣ ከኦሮሞ፣ ከሽናሻ እንዲሁም ከአገው ብሔር መሆናቸውን አረጋግጧል።

ኃላፊው በጥቃቱ የተገደሉ ዜጎች በስለት፣ በጥይትና በቀስት መሞታቸውን ተናግረው አንድ ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው የተቃጠሉ መኖራቸውንም አክለዋል።

ከእነዚህ ውጪ እስካሁን ድረስ የደረሱበት ያልታወቀ ሰዎች እንዳሉ እና በየጫካው አስከሬናቸው በመርማሪ ቡድኑ እየተፈለገ መሆኑን አስታውቀዋል።

አስከሬኑን በጅምላ ለመቅበር ከአካባቢው ሽማግሌዎች ጋር በመነጋገር መፈፀሙን ያስረዱት አቶ ካሳሁን፤ የተናጠል ቀብር ለማካሄድ አስቸጋሪ በመሆኑ እንዲሁም የቀበሌው አስተዳደር በአካባቢው የጋራ መታሰቢያ ለማቆም እንዲቻልም በሚል በአንድ ላይ መቀበራቸውን አብራርተዋል።

የቀብር ቦታውን በመምረጥ የወረዳው አስተዳዳሪዎች ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን መሳተፋቸውንም አክለው ገልፀዋል።

በበኩጂ ቀበሌ ጥቃት ከተፈፀመ በኋላም ስጋት የገባቸው ዜጎች ከተለያዩ የወረዳው ቀበሌዎች ወደ ወረዳው ከተማ ቡለን እየመጡ መሆኑንም አቶ ካሳሁን ገልፀዋል።

"በኩጂ ቀበሌ ጥቃቱ ከተፈፀመ በኋላ፣ በጭላንቆ፣ በአዲስ ዓለም፣ በዶቢ እና ጎንጎ ቀበሌዎች የሚኖሩ ማኅበረሰቦች በስጋት ምክንያት ወደ ወረዳዋ ከተማዋ ቡለን እየመጡ ነው" ብለዋል።

በአካባቢው ቀያቸውን ጥለው እየመጡ ላሉ ሰዎች ከዚህ በፊት ከፌደራል መንግሥት መጥቶ የነበረ የተለያየ ድጋፍ እየተሰጣቸው ቢሆንም በቂ አለመሆን ኃላፊው ይናገራሉ።

ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ከሰባት ቀበሌ ነዋሪ በላይ ቀዬውን ለቅቆ ወደ ቡለን ከተማ እየመጣ በመሆኑ እርዳታው በቂ አለመሆኑን አቶ ካሳሁን ተናግረዋል።

ወደ ቡለን ከተማ ከሚመጡት ነዋሪዎች ውጪ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የአማራ ክልል ከተማ የሚሄዱ ሰዎች መኖራቸውንም አክለው ገልፀዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ጥቃቱን ተከትሎ በግድያው ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉ የክልልና የፌደራል አመራሮች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ፤ 42 የታጠቁ ሽፍቶች በጸጥታ በተካሄደ አሰሳ መገደላቸውን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት በመተከል ዞን ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት የተባሉ አመራሮችን በሕግ ቁጥጥር ሥር እያዋለ መሆኑን ተናግሯል።

የክልሉ የኮሙኑኬሽን ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ እስካሁን ድረስ ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ውስጥ እጃቸው ያለበትና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አመራሮች በሚል በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ውስጥ መካከል አቶ ቶማስ ኩዊ የኢፌዴሪ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ፣ አቶ አድጎ አምሳያ የቀድሞው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ይጘኙበታል።

በተጨማሪም አቶ ሽፈራው ጨሊቦ የቀድሞ የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር፣ አቶ ባንዲንግ ማራ የመተከል ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ አቶ አረጋ ባልቢድ የመተከል ዞን የቀድሞ አመራር፣ አቶ ገመቹ አመንቲ የክልሉ የግዢና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም አቶ አድማሱ መልካ የገጠር መንገድና ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር መሆናቸውን ገልፀዋል።

እነዚህ አመራሮች ከመተከል ዞን የጸጥታ ችግር ጋር እጃቸው እንዳለበት በመረጋገጡ በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል ይባል እንጂ ከዚህ ቀደምም በዚሁ ዞን ኅዳር 5 ቀን 2013 ዓ. ም በተከሰተ የጸጥታ ችግር ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣት የተጠረጠሩ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮች ላይ ፖለቲካዊ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይስሃቅ አብዱልቃድር ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።