ደቡብ ኮሪያ ዜጎቿን 'ወልዳችሁ ሳሙ' ስትል እየተማፀነች ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
ደቡብ ኮርያ በተተናቀቀው 2020 በአገሪቷ ውስጥ ከውልደት ምጣኔ ይልቅ የሞት ቁጥር አሻቅቦ መገኘቱ አሳሰስቧታል።
ይህ የሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሆንም የደቡብ ኮርያ መንግሥትን ግን አስጨንቆታል።
በ2020፣ 275,800 ሕጻናት የተወለዱ ቢሆንም ከ2019 ጋር ሲነጻጸር በ10 በመቶ ቀንሶ ተገኝቷል።
በዚሁ ዓመት ከተወለዱት ይልቅ በሞት ያጣቻቸው ዜጎቿ ቁጥር ከፍ ብሏል። 307,764 ዜጎቿን በሞት አጥታለች።
ይህ ቁጥር የአገር ውስጥ ሚኒስትሯ መሰረታዊ የሆነ የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ እንዲያስብ አድርጎታል።
የሕዝብ ቁጥር መቀነስ በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮባታል።
የወጣቶች ቁጥር መቀነስ የአምራች ኃይል በመቀነስ በምጣኔ ሀብቱ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ የሚፈጥር ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ጡረታ እና የጤና እንክብካቤ ፍላጎት ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል።
ባለፈው ወር ፕሬዝዳነት ሙን ዤ ኢን በአገራቸው የውልደት መጠን እንዲጨምር በማሰብ የተለያዩ ፖሊሲዎችን ያስተዋወቁ ሲሆን ለመውለድ ለሚወስኑ ቤተሰቦች የገንዘብ ድጎማ ማድረግ ከእቅዶቻቸው መካከል ይገኝበታል።
በዚህ እቅድ መሰረትም ከ2022 ጀምሮ የሚወለድ እያንዳንዱ ልጅ የቅድመ ወሊድ ወጪውን ለመሸፈን 2 ሚሊዮን ዩዋን (የኮሪያ ገንዘብ) ወይንም 1,850 ዶላር ይቀበላል።
ይህ ገንዘብ ከ2025 ጀምሮ ለመተግበር ከታሰብው ልጁ አንድ ዓመት እስኪሞላው ድረስ በየወሩ ለቤተሰቡ የሚሰጠውን 300,000 ዩዋንን ሳይጨምር ነው።
በደቡብ ኮሪያ ሴቶች የሥራ ሕይወታቸውን ከሌሎች ማኅበራዊ ስኬቶቻቸው ጋር አጣጥመው ለመሄድ ሁሌም ይታገላሉ።
በዚህም የተነሳ ከመውለዳቸው በፊት የሚፈልጉትን ሥራ መያዝ፣ ቤት መግዛት እንዲሁም ሌሎች ግቦቻቸውን ማሳካትን ስለሚያስቀድሙ የአገሪቱ የውልደት ምጣኔ እየቀነሰ መጥቷል።
መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ቢገባም አሁንም ይህ የመንግሥታቸው እርምጃ ልባቸውን ያላማለለው ደቡብ ኮሪያውያን አልታጡም።












