በማሊ ሁለት የፈረንሳይ ወታደሮች ተገደሉ

ይህ አደጋ ከመድረሱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሌሎች 3 የፈረንሳይ ወታደሮች መሞታቸው አይዘነጋም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሰሜን አፍሪካዊቷ ማሊ ሁለት የፈረንሳይ ወታደሮች ተገደሉ። ወታደሮቹ የተገደሉት መንገድ ላይ በተጠመደ ቦምብ አማካኝነት ነው።

ጉዳቱ የደረሰው በምሥራቃዊ የማሊ ክፍል ሲሆን ሁለቱ ወታደሮች ወታደራዊ መረጃን በመቃረም ላይ ሳሉ ነው የተገደሉት ተብሏል።

ይህ አደጋ ከመድረሱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሌሎች 3 የፈረንሳይ ወታደሮች መሞታቸው አይዘነጋም።

ፈረንሳይ በሳህል አካባቢ 5ሺ 100 ወታደሮችን አሰማርታለች። ላለፉት 10 ዓመታት አክራሪና ጽንፈኛ ኢስላማዊ ቡድኖችን ለመደምሰስ በሚል ነው የፈረንሳይ ወታደሮች እዚህ የሚገኙት።

የሳህል አካባቢ የሚባለው በከፊል በረሃማ የሆነ ደቡባዊ የሰሐራ በረሃን የሚያካትት ሲሆን በዚህ ክልል ማሊ፣ ቻድ፣ ኒጀር፣ ቡርኪናፋሶና ሞሪሸየስ ይገኙበታል።

ፈረንሳይ እንደ አውሮጳዊያኑ ከ2013 ጀምሮ በዚህ ክልል ወታደሮቿን አሰማርታ ትገኛለች።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፈረንሳይ በድምሩ የሞቱባት ወታደሮች 50 ደርሰዋል።

ከሟቾቹ ወታደሮች አንዷ የ33 ዓመት ሴት ወታደር ስትሆን የአንድ ወንድ ልጅ እናት ነበረች።

በተከታታይ ቀናት የ5 ፈረንሳይ ወታደሮችን ሕይወት ለነጠቀው የቦምብ ጥቃት ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት አለኝ የሚለው 'ግሩፕ ቱ ሰፖርት ኢዝላም ኤንድ ሙዝሊምስ' የተሰኘው ወታደራዊ ቡድን ኃላፊነቱን ወስዷል።