ኢትዮጵያ በርካታ ሠራዊት ያበረከተችበት የዳርፉር ሠላም ማስከበር ስምሪት አበቃ

የፎቶው ባለመብት, UN
በተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ ስር ኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ወታደሮችንና የፖሊስ ኃይል ያሰማራችበት የዳርፉር ሠላም ማስከበር ተልዕኮ ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ስር በተለያዩ አገራት ውስጥ ለሚደረጉ የሠላም ማስከበር ተልዕኮዎች ከፍተኛ የሚባለውን ከ8,300 በላይ ሠራዊት የምታበረክት ሲሆን ከዚህም ውስጥ ከፍተኛው ቁጥር በሱዳን ውስጥ በሚገኙት ዳርፉርና በአብዬ ግዛት ውስጥ የተሰማሩ ናቸው።
ዩናሚድ በሚባል የአንግሊዝኛ ምህጻረ ቃል የሚታወቀው የዳርፉር ሠላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ወታደሮች ካበረከቱ ሦሰት ቀዳሚ አገራት አንዷ ናት።
በምዕራባዊ ሱዳን ለ13 ዓመታት በተባበሩት መንግሥታት አማካይነት ሠላም ለማስከበር ተሰማርቶ ለቆየው ሠራዊት በርካታ የዓለም አገራት ወታደሮቻቸውን አዋጥተዋል ከእነዚህም ውስጥ በርካታ የሠራዊቱ አባላትን በማበርከት ሩዋንዳ፣ ፓኪስታንና ኢትዮጵያ ቀዳሚዎቹ ናቸው።

በምጽሀረ ቃል 'ዩናሚድ' (UNAMID) ተብሎ የሚታወቀው በዳርፉር ሰላም ለማስከበር የተሰማራው ኃይል ከዚህ በኋላ በሱዳን እንደማይቀጥል የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ማስታወቁ ይታወሳል።
ምክር ቤቱ በሱዳን እና በዳርፉር ያለውን አንጻራዊ ሰላም፣ የሽግግር መንግሥቱ ከአማጺያን ጋር ያደረጋቸውን የሰላም ስምምነቶች እንዲሁም አጠቃላይ ለውጦችን ከግምት በማስገባት እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱ ተገልጿል።
በዚህ ውሳኔ መሰረትም ዩናሚድ በዳርፉር ከሐሙስ ታኅሣስ 31/2020 በኋላ ምንም አይነት ኃላፊነት አይኖረውም ማለት ነው። ሰላም የማስከበርና ተያያዥ ሥራዎችም ለመጨረሻ ጊዜ የሚካሄዱት በዚሁ ቀን ነው።
በሚቀጥሉት ስድስት ወራትም ወታደሮችን ወደ አገራቸው፣ አልያም ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወር፣ እንደ ወታደራዊ መኪና ያሉ ንብረቶችን ለተባበሩት መንግሥታት ማስረከብ የመሳሰሉት ሥራዎች ይከናወናሉ።
በዚህ መሰረት ሁሉም የዩናሚድ ሲቪልና ወታደራዊ ሠራተኞች ሰኔ 2021 ላይ ጠቅልለው ይወጣሉ ተብሏል።
ዩናሚድ እንዴትና ለምን ተቋቋመ?
በአውሮፓውያኑ 2003 ዳርፉር ውስጥ የተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው አፈናቅሏል።
በመንግሥት ወታደሮችና በርካታ ታጣቂ ቡድኖች መካከል የሚካሄደውን ውጊያ ተከትሎ በጣም ዘግናኝ የሚባሉ ወንጀሎች እንደተፈጸሙ ይነገራል። በርካቶች ተገድለዋል፣ ሴቶችና ህጻናት ተደፍረዋል፣ ንጹሀን ዜጎች ሰብአዊ መብታቸው ተጥሷል።
የእርስ በርስ ጦርነቱን ተከትሎ በዚያው ዓመት የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን ዓለም አቀፍ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስቦ ነበር።
በወቅቱ በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ የዳርፉር የሰላም ስምምነት 2006 ላይ ተፈረመ። ነገር ግን ስምምነቱ ላይ የደረሱት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ነበሩ። ይህን ተከትሎም በአፍሪካ ሕብረትና በተባበሩት መንግስታት አደራዳሪነት ኳታር ዶሃ ውስጥ ሁለተኛ ስምምነት ተፈረመ።
ወርሃ ኅዳር 2006 ላይ ደግሞ በአዲስ አበባ በተካሄደው ውይይት የተባበሩት መንግሥታት እና አፍሪካ ሕብረት በጥምረት ዳርፉር ውስጥ ሠላም አስከባሪ ኃይል ለማሰማራት ተስማሙ።
የወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ ባን ኪ ሙን እና ሌሎች በርካታ የዓለም መሪዎች ባካሄዱት የማግባባት ስራ፣ ሱዳን ሰኔ 2007 ላይ ይህ ሠላም አስከባሪ ቡድን ወደ ድንበሯ እንዲገባ ፈቀደች።
ይህን ተከትሎም የተባበሩት መንግሥታት እና የአፍሪካ ሕብረት ጥምር ኦፕሬሽን፣ ሐምሌ 2007 ላይ የተቋቋመ ሲሆን በምጽሃረ ቃል ዩናሚድ ተብሎ እንዲጠራም ተወሰነ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዋና ዋና ኃላፊነቶቹ
- ንጹሃንን ዜጎችን ያለምንም አድልዎ መጠበቅ
- ከተባባሩት መንግሥታት እና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች የሚመጡ የሰብአዊ እርዳታዎችን ደህንነት መጠበቅና ማድረስ እንዲሁም የበጎ አድራጎት ድርጅት ሠራተኞችን ደህንነት መጠበቅ
- በዶሃው ስምምነት መሠረት በሱዳን መንግሥትና ስምምነቱን ያልፈረሙ አማጺያንን ማደራደር
ይህ ተልዕኮ ዋና መቀመጫው በሰሜናዊ ዳርፉር ኤል ፋሽር ውስጥ ሲሆን በአምስቱም የዳርፉር ግዛቶች በአጠቃላይ 35 የስምሪት ማዕከላት አሉት።
ሐምሌ 2007 ላይ ተልዕኮው 25 ሺ 987 ዩኒፎርም ለባሽ ሰላም አስከባሪዎችን ወደ ሱዳን ለማስገባት ፈቃድ ያገኘ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 19 ሺ 55 ወታደሮች፣ 360 ወታደራዊ ታዛቢዎችና አታሼዎች፣ 3772 የፖሊስ አማካሪዎች እና 2660 የፖሊስ ዩኒቶች ይገኙበታል።
ዳርፉር ለምን የጦርነት ቀጠና ሆነች?
ዳርፉር የ80 ጎሳዎች መገኛ ስትሆን ነዋሪዎቹም አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ናቸው። አማጺያኑ የሚመጡት ደግሞ ከሶስት ማህበረሰቦች ነው።
አካባቢው የአየር ጸባዩም ሆነ ተፈጥሮአዊ አቀማመጡ ለእንቅስቃሴ ምቹ ስላልሆነ ብዙ አማጺያን ይመርጡታል። ለዓመታት አካባቢው ግጭት ርቆት አያውቅም። ሁሌም ነዋሪዎች የጦርነት አካባቢውን ጥለው ይሰደዳሉ።
ምንም እንኳን የዳርፉር ቀደምት ነዋሪዎች (ፉር እና ሌሎች ጎሳወፐች) ከአረብ ማህበረሰቦች ጋር ለበርካታ ዓመታት ያለምንም ችግር ተስማምተው የኖሩ ቢሆንም የተፈጥሮ ሀብት እያጠረ ሲመጣ ግን ግጭቶች መከሰት ጀመሩ። እንደውም ይህን ተከትሎ ግጭቱ መልኩን ቀይሮ የዘር ግጭት ሆነ።
ዳርፉር ከድሮውም ከሌሎች የሱዳን አካባቢዎች በጣም የራቀና ምቹ ያልሆነ ስፍራ ነው። በደህናው ጊዜ እንኳን መንግሥት፣ እንደ ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች እንደልቡ መድረስ የማይችለው በዳርፉር ብቻ ነው።
አብዛኛዎቹ የዳርፉር ነዋሪዎች ሙስሊሞች ሲሆኑ በሱዳናዊነታቸው ጠንካራ እምነት እንዳላቸው ይገለጻል። ነገር ግን አንዳንድ የተገፉ ብሄሮች ከሱዳን ይልቅ ከጎረቤት አገር ቻድ ካሉ ብሄሮች ጋር ራሳቸውን ያቆራኛሉ።
2003 ላይ ሁለት የታጠቁ ቡድኖች ዳርፉር ውስጥ የሱዳን መንግሥት ላይ ጦርነት አወጁ። ሁለቱ ቡድኖች የሱዳን ነጻ አውጪ ኃይል (SLA) እና ፍትህ እና እኩልነት እንቅስቃሴ (JEM) ሲሆኑ፣ ጦርነቱን የጀመሩት አንዳንድ ከተሞች፣ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እና ንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ነው።
በወቅቱ በጥቃቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች የተገደሉ ሲሆን፣ 80 የፖሊስ ጣቢያዎችም ወድመዋል። ይህን ተከትሎም የአካባቢው መዋቅር ሙሉ በሙኡ በመቋረጡ ሌሎች ቡድኖችም እንደልባቸው መንቀሳቀስ እንዲችል እድሉን አመቻቸ።
በዳርፉር የሚገኙት አማጺያን አብዛኛዎቹ የምንዋጋው በሱዳን መንግሥት በሚደርስብን መገለል ነው ይላሉ። አካባቢው አንዳይለማ ሆን ተብሎ በመንግሥት አሻጥር ተሰርቶብናል የሚሉት አማጺያኑ እንደ አማራጭ የወሰዱት ጦርነትን ነው።
የተነሳውን ተቃውሞና አመጽ ለመቆጣጠርም ካርቱም አርብቶ አደር አረቦችን በማስታጠቅ እርምጃ ወሰደች። እነዚህ የታጠቁ አርብቶ አደሮችም 'ጃንጃዊድ' በመባል የሚታወቁ ሲሆን የሱዳን መንግሥት ጠቀም ያለ ገንዘብ ይከፍላቸውም ነበር።
የሱዳን ዳርፉር ግጭት
- ሚያዝያ 2003 ላይ የዳርፉር ግጭት ተጀመረ
- ሐምሌ 2007 የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ሰላም አስከባሪ በቦታው እንዲሰማራ ወሰነ
- መጋቢት 2009 ላይ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር በዳርፉር የጦር ወንጀል ፈጽመዋል በማለት የእስር ትዕዛዝ አወጣ
- ሚያዝያ 2019 የሱዳን ወታደሮች ፕሬዝዳንት አልበሽርን ከስልጣን አባረሩ
- የካቲት 2020 ላይ መንግሥት ፕሬዝዳንት አልበሽር በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተስማማ
- ነሐሴ 2020 የሱዳን መንግሥት ከአምስት አማጺ ቡድኖች ጋር የሰላም ስምምነት ደረሰ
ባሳለፍነው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ ደግሞ የሱዳን በቀድሞ ፕሬዝዳንቷ ኦማር አል በሺር በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ዳርፉር ላይ የተፈፀመውን ወንጀል መመርመር ተጀምሯል።
ከአስር ዓመት በፊት የዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት በዳርፉር ለተፈፀመው የዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀልና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በበሺር ላይ የእስር ማዘዣ ቆርጦባቸው ነበር።
30 ዓመት በስልጣን ላይ የቆዩት የሱዳን የቀድሞ ፕሬዝዳንት አል በሺር በሀገሪቱ በተቀሰቀሰ ሕዝባዊ ተቃውሞ የተነሳ ከስልጣን መውረዳቸው ይታወሳል።
ሱዳን በአሁኑ ሰአት ከወታደራዊ መሪዎችና የተቃውሞ እንቅስቃሴውን ይመሩ ከነበሩ አካላት በተውጣጣ የሽግግር መንግሥት እየተመራች ትገኛለች።
አል በሺር ከስልጣን ከወረዱ በኋላ የአለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቢያነ ሕግጋት በሺር በዳርፉር ለተፈፀመው ወንጀል ችሎት ፊት ቀርበው ጉዳያቸው እንዲታይ ጠይቀው ነበር።
በዳርፉር ሰላም ለማስከበር የተሰማራው ኃይል ከዚህ በኋላ በሱዳን እንደማይቀጥል የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ማስታወቁን ተከትሎ የንጹሃን ዜጎች ደኅንነት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል እየተገለጸ ነው።
በደቡብ ሱዳን ይደረስበታል የተባለው የሰላም ስምምነት ለ17 ዓመታት የዜጎችን ሕይወት ሲያመሳቅል የቆየው ጦርነት እንዲያበቃና በርካታ ዳርፉራውያን ወደ ቀድሞ ቀያቸው እንዲመለሱ ሊያደርግ እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።
በዳርፉር ጦርነት ምክንያት እስካሁን ድረስ ባለፉት 17 ዓመታት 300 ሺህ ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን 2.5 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገድደዋል።
የሱዳን መንግሥት ደግሞ የሰላም አስከባሪ ኃይሉ መሄድን ተከትሎ በቦታው ተክቶ ሊሰራ የሚችል ቡድን ለማቋቋምና ንጹሀን ዜጎችን ለመጠበቅ በዝግጅት ላይ እንደሆነ አስታውቋል።













