ትራምፕ ለአሜሪካውያን 2 ሺህ ዶላር እንዲሰጥ ያቀረቡት ሃሳብ ውድቅ ሆነ

ትራምፕ ለአሜሪካዊያን 2 ሺህ ዶላር ይሰጣቸው ሲሉ ያቀረቡት ሃሳብ ውድቅ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩናይትድ ስቴትስ ሴኔት የሪፐብሊካኖች መሪ የሆኑት ሚች ማክኮኔል ትራምፕ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ኪሳቸው ለተጎዳ አሜሪካዊያን የሚሰጠው ገንዘብ ከፍ ይበል ሲሉ ያቀረቡትን ሃሳብ ውድቅ አደረጉ።

ከሌላው ጊዜ በተቃራኒ ኮንግረሽናል ዴሞክራቶችና አንዳንድ ሪፐብሊካን የትራምፕን ሃሳብ ደግፈው ድምፅ ሰጥተዋል።

የአሜሪካ ሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ለአሜሪካዊያን በነብስ ወከፍ 2 ሺህ ዶላር ይሰጣቸው ብሎ አፅድቋል።

ነገር በሪፐብሊካኖች የበላይነት የተያዘው የአሜሪካ የላይኛው ምክር [ሴኔት] ሃሳቡን ውድቅ አድርጎታል።

የምክር ቤቱ የሪፐብሊካኖች መሪ ድጎማውን ወደ 2 ሺህ ከፍ ማድረግ 'ሌላ ዕዳ ውስጥ ነው የሚዘፍቀን' ብለዋል።

ትራምፕ የአሜሪካ ምጣኔ ሃብት እንዲነቃቃ አያይዘው የጠየቁትም ገንዘብ ውድቅ ሆኖባቸዋል።

ኮንግረሱ ከዚህ ቀደም በኮሮናቫይረስ ምክንያት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አሜሪካዊያን በነብስ ወከፍ 600 ዶላር እንዲሰጣቸው ወስኗል።

ነገር ግን ፕሬዝደንት ትራምፕ ድጋፉ 2 ሺህ ዶላር ካልሆነ አልፈርምም ብለው ካንገራገሩ በኋላ ባለፈው እሁድ ፊርማቸውን አሳርፈዋል።

ፕሬዝደንቱ ፊርማቸውን ያሳርፉ እንጂ ድጎማው ከለፍ ማለት አለበት የሚለውን ጥያቄያቸውን አላቋረጡም ነበር።

ለወትሮም ከፕሬዝደንቱ ጋር ዓይንና ናጫ የሆኑት ዴሞክራት የሕዝብ እንደራሴዎች የትራምፕን ሃሳብ ደግፈው ድጎማው ወደ 2 ሺህ እንዲያድግ ሲሉ በአብላጫ ድምፅ አፅድቀው ነበር።

ቢሆንም ትራምፕን ደግፈው በመናገር የሚታወቁት የላይኛው ምክር ቤት የሪፐብሊካኖች መሪ ሚች በዚህ ሃሳብ አልስማማም ሲሉ ተደምጠዋል።

አሜሪካ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ3250 ሺህ በላይ ደርሷል።

ከቀናት በፊት በተከበረው የፈረንጆቹ ገና እና በመጭው አዲስ ዓመት ሳቢያ ይህ ቁጥር የበለጠ ሊያሻቅብ ይችላል የሚል ፍራቻ አለ።

አልፎም እጅግ በፍጥነት እየተላለፈ ነው የተባለለት አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ አሜሪካ ገብቷል።

የዚህን ዝርያ መጀመሪያ ወደ አሜሪካ መግባት ይፋ ያደረገችው የኮሎራዶ ግዛት ናት። ካሊፎርኒያ ደግሞ ቫይረሱ እዚህም ታይቷል ብላለች።

ሰውዬው ለምን ድጎማ ከፍ እንዲል አልፈለጉም?

የኬንታኪ ሴናተር የሆኑት ሚች የዴሞክራቶችን ሃሳብ ውድቅ አድርገው አሜሪካዊያን 2 ሺህ ዶላር ሳይሆን 600 ዶላር ይሰጣቸው ብለዋል።

"ምክረ ሃሳቡ ሴኔቱን አልፎ ይፀድቃል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው" ብለዋል ሚች።

በሕዝብ ተወካዮችና በሴኔቶች ፊት ንግግር ያደረጉት ሚች "ሰኔቱ በፍጥነት ገንዘብ ተበድሮ ይህን ድጎማ በማፅደቅ ለዴሞክራቶችና ለሃብታም ጓደኞቻቸው አይሰጥም" ብለዋል።

በምትኩ ፕሬዝደንት ትራምፕ የጠየቋቸው ሌሎች ሃሳቦች እንዲፀድቁ የጠየቁት ሚች ከዴሚክራቶች መረረ ያለ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

አንደኛው ሃሳብ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን የሕግ ከለላ መንፈግ ሲሆን ሌላኛው ትራምፕ ምርጫው ተጭበርብሯል ሲሉ ያቀረቡት ያልተረጋገጠ ክስን የሚያጣራ ቡድን ማቋቋም ነው።

ድጎማው ከፍ ይበል ሲሉ ድምፃቸውን የሰጡት 'ሊበራሉ' ሴናተር በርኒ ሳንደርስ "እኛ እየጠየቅን ያለነው ድምፅ እንድናገኝ ብቻ ነው። ምንድን ነው ችግሩ?" ሲሉ ተደምጠዋል።

በሴኔቱ የዴሞክራቶች መሪ የሆኑት ቻክ ሹመር "መሪ ማክኮኔል ለአሜሪካውያን የ2 ሺህ ዶላር ቼክ ይሰጣቸው ብለን ያቀረብነውን ሃሳብ ሲገድሉብን እያየን ነው። ይህን ብር በርካታ ሚሊዮን አሜሪካውያን እጅግ ይፈልጉታል" ብለዋል።

የሕዝብ እንደራሴዎችን አፈ ጉባዔዋ ናንሲ ፔሎሲ ደግሞ "እኚህ ሪፐብሊካኖች ሕዝቡ ሲያዝኑ እያዩ ዝም ማለት ይችሉበታል" ሲሉ አማረዋል።

አንዳንድ ቀንደኛ የሚባሉ ሪፐብሊካኖችም የትራምፕን ሃሳብ ደግፈው ድጎማው ወደ 2 ሺህ ዶላር ከፍ እንዲል ጠይቀዋል።

የአሜሪካ መንግሥት ለኤጎቼ ይሁን ያለው ድጎማ አንድ ጊዜ ከሚከፈል 600 ዶላር በተጨማሪ ለሥራ አጦች የሚሰጥና የቤት ኪራይ መክፈል ለተሳናቸው የሚሆን ነው።