በፈረንጆቹ 2020 ከባድ የአየር ሁኔታ ዓለምን ለኪሳራ ዳርጓታል ተባለ

በሕንድ የደረሰ የጎርፍ አደጋ

የፎቶው ባለመብት, BABU

ክርስቲያን ኤይድ የተሰኘው በጎ አድራጎት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሰረት ዓለማችን እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆቹ ዓመት በከፋ የአየር ንብረት ለውጥ መመታቷን አስታወቀ።

ድርጅቱ በ2020 የተከሰቱ እና በዓለማችን ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ያስከተሉ አስር ጉልህ ክስተቶችን መርጧል።

ከእነዚህ መካከል ስድስቱ በእስያ የተከሰቱ ሲሆኑ በቻይናና በሕንድ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከ40 ቢሊዮን ዶላር በላይ ውድመት አስከትሏል ሲል ያትታል።

በአሜሪካ የተከሰተው ከባድ አውሎ ንፋስ እና ሰደድ እሳት ደግሞ ወደ 60 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ አድርሷል።

ዓለም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እግር ተወርች ተይዞ መላወሻ ባጣበት ወቅት የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖበት ነበር ይላል ሪፖርቱ።

ክርስቲያን ኤይድ አስር ከባድ አውሎ ነፋሶችን፣ ሰደድ እሳቶችንና ጎርፎችን በመጥቀስ በአጠቃላይ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ውድመት አስከትለዋል ብሏል።

አክሎም ከእነዚህ መካከል ዘጠኙ 5 ቢሊዮን ዶላር ውድመት አድርሰዋል ሲል ያክላል።

በሕንድ ለወራት በዘለቀው እና ከባድ ዝናብ ባስከተለው ከባድ ጎርፍ ከ2000 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ ሚሊዮኖች ደግሞ ቀያቸውን ጥለው ተሰድደዋል።

የመድን ዋስትና የተገባለት ንብረት ላይ የደረሰው ኪሳራ ብቻ ሲገመትም 10 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል ተብሏል።

ቻይና በጎርፍ አደጋ ብቻ ከፍተኛ የሆነ የምጣኔ ሃብት ቀውስ ገጥሟታል። በእርግጥ በሰው ሕይወት ላይ የደረሰው አደጋ ከሕንድ ጋር ሲነጣጸር አነስተኛ ቢሆንም፣ ከሰኔ እስከ ጥቅምት ወር ድረስ 32 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራን ያስተናገደችው በጎርፍ የተነሳ ነው።

እነዚህ አደጋዎች ቀስ በቀስ ተከስተው ውድመት ያደረሱ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ በድንገት ተከስተው ከፍተኛ ጥፋት ያደረሱም ነበሩ።

ለዚህ ተጠቃሹ በግንቦት ወር የቤንጋል የባሕር ዳርቻን የመታው ሳይክሎን አምፋን ሲሆን፣ በጥቂት ቀናት ብቻ 13 ቢሊየን ዶላር የተገመተ ንብረት አውድሟል።

በአፍሪካ ቀንድ የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአየር ንብረት ለውጥ በትሩን ካሳረፈባቸው አህጉራት መካከል አፍሪካ አንዷ ናት። በአህጉሪቷ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ 8.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሰብልን አውድሟል።

የተባበሩት መንግሥታት የበረሃ አንበጣ ወረርሽኙን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ያያዘው ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍሪካ ቀንድ እና በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰቱ ከባድ ዝናቦች ለበረሃ አንበጣው መከሰትና መስፋፋት ምክንያት ሆነዋል ብሏል።

አውሮፓም በ2020 ሲያራ የተሰኘ አውሎ ነፋስ ክፉኛ ጎድቷታል። ይህ አውሎነፋስ አየርላንድ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እንዲሁም በርካታ አገራትን ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ አጥቅቷል።

ይህ ከባድ አውሎ ነፋስ የ14 ሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ 2.7 ቢሊዮን ዶላር የተገመተ ንብረት አውድሟል።

ክርስቲያን ኤይድ በሪፖርቱ ላይ በገንዘብ ተገምተው የተቀመጡት ቁጥሮች የመድን ዋስትና በተገባላቸው ንብረቶች ላይ የደረሱ ኪሳራዎች ብቻ ዝቅ ተደርጎ ተሰልተው ነው ብሏል። ስለዚህ የጉዳቱ መጠን ከዚህ ከፍ ሊል የሚችልበት እድል ሰፊ ነው።

በሀብት የደረጁ አገራት ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣ ንብረት ስላላቸው በተፈጥሮ አደጋዎቹም የሚደርስባቸው ጉዳት በዚያው ልክ ከፍ ያለ ይሆናል ሲል አስቀምጦታል።

በእንደዚህ ዓይነት የተፈጥሮ አደጋዎች ወቅት የገንዘብ ኪሳራ ብቻ የጉዳቱን መጠን አያሳይም።

በአሜሪካ በርካታ ስፍራዎች የሰደድ እሳት ተከስቶ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ለምሳሌ በደቡብ ሱዳን የደረሰው የጎርፍ አደጋ የ138 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ የዚህ ዓመት የምርት ዘመንን ሰብል ሙሉ በሙሉ አውድሞታል። ስለዚህ ኪሳራው በገንዘብ ተሰልቶ የሚቀመጥ አለመሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል።

ተመራማሪዎች እንደሚሉት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ የመጣ እና ቀጣይነት ያለውም ነው ብለዋል።

ከቀናት በኋላ በሚጀምረው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመትም የአየር ንብረት ተጽዕኖው ይቀጥላል ተብሎ የተገመተ ሲሆን፤ ነገር ግን ከ2020 በተለየ የፖለቲካ መሪዎች የከባቢ አየር ሙቀት መጨመርን ለመዋጋት የተሻለ እርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ ተስፋ ተደርጓል።

የጆ ባይደን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆኖ መመረጥ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት እና አረንጓዴ እጸዋት እንዲያገግሙ ያሳረፈው በጎ ተጽዕኖ እንዲሁም የመብት ተሟጋቾች ውትወታ አገራት የዓለማችንን ሙቀት ለመቀነስ እና ወደ ተሻለ ነገ ለሚደረገው ጉዞ የሚጠቅመውን ይወስናሉ ለሚለው ተስፋን ፈንጥቋል።