ግሬታ፡ የአየር ንብረት ለውጥ እንደ ኮሮናቫይረስ ሊያሳስበን ይገባል

ግሬታ ተንበርግ

ታዳጊዋ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ግሬታ ተንበርግ፤ ዓለም ኮሮናቫይረስ ካደረሰው ጥቃት ትምህርት ወስዶ፤ ለወረርሽኙ የሰጠውን ትኩረት ለአየር ንብረት ለውጥም መስጠት እንዳለበት ተናግራለች።

ስዊድናዊቷ የመብት ተሟጋች ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተገቢው ትኩረት ሊቸረው ይገባል ብላለች።

ማኅብረሰቡ የአየር ንብረት ለውጥን እንዲሁም ጥቁሮች ላይ የሚደርሰውን ኢ-ፍትሐዊነት አይቶ እንዳላየ የሚያልፍበት ጊዜ እንዳለፈ ታምናለች።

ታዳጊዋ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ በመጣሉ፤ ቤቷ ሆና ለማሰላሰል ጊዜ እንዳገኘች ትናገራለች።

ግሬታ በ16 ዓመቷ ትምህርት አቋርጣ ነበር ወደ አየር ንብረት ለውጥ ንቅናቄ የገባችው።

መስከረም ላይ የተባበሩት መንግሥታት በኒው ዮርክ ባዘጋጀው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ላይ ለመታደም ግሬታ አትላንቲክን በመርከብ ማቋረጧ ይታወሳል።

የተለያዩ አገራት መሪዎች አብረዋት ፎቶ ሲነሱ ነበር። የጀርመኗ መራሔተ መንግሥት አንግላ መርከል፤ አብረው የተነሱትን ፎቶ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መለጠፍ ይችሉ እንደሆነ ጠይቀዋት እንደነበርም ታስታውሳለች።

ግሬታ የዓለም ኃያላን አገራት ተግባር ብዙም አይዋጥላትም። “የነሱ ትውልድ በቀጣይ የሚመጡ ትውልዶችን ተስፋ በማጨለሙ ጥፋተኛነት እየተሰማቸው ይሆናል” ትላለች።

ታዳጊዋ በተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ላይ ያደረገችውን ንግግር ብዙዎች ያስታውሱታል። መሪዎቹን “በባዶ ቃላችሁ ልጅነቴን ሰረቃችሁኝ፤ ህልሜን ገደላችሁት” ስትል ነበር የወቀሰቻቸው።

“ሰዎች እየሞቱ ነው። እናንተ ግን ስለ ገንዘብና ዘላቂ የምጣኔ ኃብት እድገት ታወራላችሁ። እንዴት እንዲህ ታደርጋላችሁ?” ስትል መሪዎቹን ኮንናለች።

የዛን ጉባኤ ያህል ተደማጭነት የምታገኝበት መድረክ እንደማታገኝ በማሰብ የተሰማትን ሁሉ ለመናገር መወሰኗን ለቢቢሲ ተናግራለች።

ከጉባኤው ወጥታ ወዳረፈበችበት ሆቴል ስትሄድ ሰዎች ንግግሯን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ሲያደምጡ ብታይም ብዙም ደስተኛ አላደረጋትም።

አሁንም ለአየር ንብረት ለውጥ መሰጠት ያለበት ትኩረት ያህል እንዳልተቸረውም ትናገራለች።

“ሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ራሱ ስለ አየር ንብረት የሚያውቁት በጣም ትንሽ ነው። እውቀታቸው ከምታስቡት በላይ በጣም ውስን ነው” ትላለች።

የካርበን ልቀትን መቀነስ የሚቻለው አኗኗራችን በመለወጥ እንደሆነ ታስረዳለች። ሆኖም ግን መሪዎች ልቀትን ለመቀነስ እንዳልቆረጡ ታክላለች። “ልቀትን ከመቀነስ ይልቅ ሪፖርት ማድረግ አቁመው ወደ ሌላ ቦታ ያዛውራሉ።”

ዩናይትድ ኪንግደም፣ ስዊድን እና ሌሎች አገሮች የባህርና የአየር ጉዞ የሚያስከትለውን ልቀት እንዲሁም በሌሎች አገሮች በከፈቷቸው ፋብሪካዎች ያለውን ልቀትም እንደማይመዘግቡ ትናገራለች።

“አረንጓዴ፣ ዘላቂነት፣ ለአካባቢ ተስማሚ፣ ዜሮ ልቀት የሚሉት ቃላት በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ይውላሉ። ነገር ግን ትርጉማቸውን አጥተዋል።”

ግሬታ እንደምትለው፤ ዓለም ከኮሮናቫይረስ መማር ያለበት በአደጋ ጊዜ መተባበር እንደሚያዋጣ ነው። ፓለቲከኞች ሳይንቲስቶችን መስማትም አለባቸው።

በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ስለሚሞቱ ሰዎች ለማውራት መንገድ እንደሚከፈት ታዳጊዋ ተስፋ ታደርጋለች። ሆኖም ግን የሙቀት መጨመርን መቆጣጠር ይቻል ይሆን? የሚለው ላይ ጥያቄ አላት።

“አገራት ቃል በገቡት መሠረት የካርን ልቀትን ቢቀንሱ እንኳን የዓለም ሙቀት ከ3 እስከ 4 ዲግሪ መጨመሩ አይቀርም። የአየር ንብረት ለውጥ ቀውሱ አሁን ባለው የፖለቲካና ምጣኔ ኃብት አካሄድ አይገታም።”

የመብት ተሟጋቿ በኃብት የናጠጠችው አሜሪካ ውስጥ ባየችው የካርበን ልቀት የበዛበት አኗኗር ደንግጣለች። የንፋስና የፀሐይ ኃይል የሚጠቀሙ መሣሪያዎች ጥቂት ናቸው።

በቅርቡ ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ መገደሉን ተከትሎ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ ተስፋ ሰጥቷታል። “ሰዎች ድምጻቸውን እያሰሙ ነው። ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉም አይተዋል” ትላለች።

ያየችው ነገር ተስፋ እንደሰጣትም “የሰው ልጅ ገና አልወደቀም” በማለት ትናገራለች።

ግሬታ አዲስ የራድዮ ዘጋቢ መሰናዶ ጀምራለች። ስለ አየር ንብረት ለውጥ ውይይት ይካሄድበታል።

ዘጋቢ መሰናዶውን የምታገባድደው እንዲህ በማለት ነው. . .

“ከተፈጥሮ ጋር መደራደር አይቻልም። የፊዚክስ ሕግጋት አይቀለበሱም። የተቻለንን እያረግን ነው ማለት በቂ አይደለም። ከዛም በላይ ይጠበቅብናል። ኃላፊነቱ የእናንተም የኔም ነው።”