በዳርፉር ግጭት በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ተፈላጊው የጃንጃዊድ ሚሊሻ መሪ እጁን ሰጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዳርፉሩ ግጭት በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ይፈለግ የነበረው የጃንጃዊድ ሚሊሻ መሪ እጁን መስጠቱ ተነገረ።
ፍርድ ቤቱ እንዳለው የጦር ወንጀልን ጨምሮ በሌሎች ወንጀሎች ይፈለግ የነበረው አሊ ሙሐመድ አሊ አብደ-አል-ራሃማን በገዛ ፍቃዱ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ውስጥ እጁን ሰጥቷል።
አሊ ኩሻይብ በሚለው መጠሪያው በስፋት የሚታወቀው አሊ ሙሐመድ አሊ አብደ-አል-ራሃማን፤ የጦር ወንጀልን ጨምሮ፣ በግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና ሰዎችን በማሰቀየት 50 ክሶች ተመስርቶበታል።
በግለሰቡ ላይ የእስር ትዕዛዝ የወጣው ከ13 ዓመት በፊት ነበር።
የተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባቼሌት የቀድሞ የጃንጃዊድ ሚሊሻ መሪ ነው ተብሎ ክስ የተመሰረተበት አሊ ኩሻይብ በቁጥጥር ሥር መዋሉ "ጉልህ የሆነ እርምጃ ነው" ብለዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዋችም የግለሰቡ መያዝ በዳርፉ ግጭት ለተጎዱት ንጹሃን እና ቤተቦቻቸው ፍትሕ ያመጣል ብሏል።
ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዳለው አሊ ኩሻይብ እጁን እንዲሰጥ የመካከለኛው የአፍሪካ ሪፐብሊክ፣ የቻድ፣ የፈረንሳይ፣ የኔዘርላንድስ መንግሥታት እና የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይል "ትብብር እና እርዳታ" አድርገዋል።
ከአሊ ኩሻይብ በተጨማሪ በዳርፉ ግጭት እጃቸው አለበት የሚባሉ አራት ሱዳናውያን በፍርድ ቤቱ ይፈለጋሉ። ከእነዚሀም መካከል የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝድንት ኦማር አል-በሽር ይገኙበታል።
ከአልበሽር በተጨማሪ የቀድሞ የሱዳን የመከላከያ ሚንስትር አብዱልራሄም ሞሐመድ ሁሴን እና የቀድሞ የደቡብ ኮርዶፋን ግዛት አስተዳዳሪ አህመድ ሃሩን ተጠቃሽ ናቸው።
ከእነዚህ መካከል ሱዳን የቀድሞውን ፕሬዝደንት ኦማር አል-በሽርን ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አሳልፌ እሰጣለሁ ማለቷ ይታወሳል። በተመሳሳይ የቀድሞ ፕሬዝደንት እአአ 2003 ላይ በዳርፉር ተከስቶ የነበረውን ግጭት ተከትሎ በዘር ማጥፋት፣ በጦር ወንጆሎችና በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ክሶች ቀርቦባቸዋል።
የጃንጃዊድ ሚሊሻዎች በምዕራብ ሱዳን እና በምሥራቅ ቻድ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ናቸው። ጃንጃዊድ የሚለው ቃል "ታጣቂ ፈረሰኛ" የሚል ትርጓሜ የሚሰጠው ሲሆን፤ በዳርፉር በነበረው ግጭት፤ ጃንጃዊድ ሚሊሻዎች ለወቅቱ ፕሬዝደንት ኦማ አል-በሽር በክፍያ ይዋጉ እንደነበረ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው በዳርፉር በነበረው ጦርነት በትንሹ የሞቱት ሰዎች 300 ሺህ እንደሚሆኑ እና ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎችም መፈናቀላቸውን አስታውቋል።












